Sunday, 24 November 2013 17:26

ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ለመምህራን የገዛውን ቤት ባለማስረከቡ 20ሚ. ብር ከሰረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“ቤቱ የዘገየው በትራንስፎርመር ችግር ነው” ዩኒቨርሲቲው

ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከሁለት ዓመታት በፊት በ156 ሚሊዮን ብር ለመምህራን የገዛቸውን መኖሪያ ቤቶች በወቅቱ ባለማስረከቡ መምህራኑን ከማስቆጣቱ በተጨማሪ ኪሳራ እየደረሰበት ነው፡፡
የዩኒቨርስቲው ስትራቴጂክ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ አባቡ በበኩላቸው፤ በከተማው የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ችግር ስለነበረ እስኪሟላ ድረስ የመኖሪያ ቤቶቹ ርክክብ ዘግይቷል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርስቲው ከሁለት አመት በፊት በአራት ቦታ የኮንዶሚኒየም (የጋራ መኖሪያ) ቤቶችን   ከከተማው አስተዳደር ቢገዛም እንዳላስረከባቸው የገለፁት መምህራን፤ ቤቶቹ ለብልሽት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው ቤቶቹን በአፋጣኝ በማስረከብ እኛን ከቤት ችግር፣ ቤቶቹንም ከብልሽት ሊታደጋቸው ይገባል ብለዋል መምህራኑ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከ1500 በላይ መምህራን እንዳሉትና ለመምህራኑ በየወሩ በአማካይ 600 ብር የቤት ኪራይ አበል እንደሚሰጥ መምህራኑ ጠቅሰው፤ ቤቶቹን ባለማስረከቡ በአመት ወደ 11 ሚሊዮን ብር ገደማ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡  
ዩኒቨርስቲው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ቤቶችን ከከተማ አስተዳደሩ የገዛው ለከተማው ህዝብ ተብሎ ከተገነባው ላይ መሆኑን የገለፁ መምህራን፣ ወይ ህዝቡ አልተጠቀመ ወይ መምህራኑ ከቤት ኪራይ አላረፉ፤ ቤቶቹ ከሁለት አመት በላይ ያለ አገልግሎት እየተሰነጣጠቁና እየተበላሹ ነው ብለዋል፡፡
የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ አባቡ፤ ርክክብ ሳይፈፀም ቤቶቹ ያለ አገልግሎት መቀመጣቸውን ጠቅሰው፣ ከትራንስፎርመር ችግር በተጨማሪ ቤቶቹን ከከተማው አስተዳደር ለመቀበልም ብዙ ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል፡፡ “መጀመሪያ ለቤቶቹ የተጠየቅነው 99 ሚሊዮን ብር ነበር” ያሉት አቶ ሞላ፤ ቤቶች ልማት መስሪያ ቤት “ዋጋውን ስናሰላ ስህተት ፈጽሜያለሁ” በማለት ክፍያውን ወደ 156 ሚሊዮን ብር ለውጦብናል ብለዋል፡፡ “የቤቶቹ ዋጋ በዚህ መጠን ሲጨመርብን ከገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ማስፈቀድና ከቤቶች ልማት መስሪያ ቤት ጋር ሌላ አዲስ ውል መዋዋል ነበረብን፣ ይህም ሂደቱን አጓትቶብናል ብለዋል፤ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ትራንስፎርመሩን በተመለከተ ከከተማው መብራት ሃይል ጋር በመነጋገር ዩኒቨርስቲው ክፍያ መፈፀሙንና የውሃ መስመር ዝርጋታውም መሠራቱን የጠቆሙት አቶ ሞላ አባቡ፤ የቤቶች ልማት በበጀት እጥረት ያላጠናቀቃቸው የማሳረጊያ ስራዎችን ማለትም የበር፣ የመስኮት፣ የወለል፣ የኮርኒስና መሰል ስራዎችን ለማሰራት ዩኒቨርስቲው ጨረታ አውጥቶ በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቤቶቹን መቼ ለመምህራኑ ማስረከብ እንደሚቻል የተጠየቁት አቶ ሞላ፤ በእርግጠኝነት ለመናገር እንደሚያስቸግር ገልፀው፤ ነገር ግን ስራው ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፤ እያንዳንዱ መምህር ምን አይነት ቤት እንደሚረከብ ከነስፋቱ እንዲያውቅ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ሲጠናቀቁ ከ1300 በላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከቤት ችግር እንደሚላቀቁ አቶ ሞላ የገለፁ ሲሆን፤ መምህራኑ በበኩላቸው የትራንስፎርመር እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናቅቀዋል በማለት “ርክክቡ ያለ በቂ ምክንያት መጓተቱን ይናገራሉ፡፡

Read 3994 times