Sunday, 24 November 2013 17:28

የስደተኞች ስቃይ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት እንዳይውል ሚኒስትሩ ጠየቁ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(12 votes)

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በደረሰው ስቃይ ዙሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ድክመት መተቸታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሐኖም በበኩላቸው፤ ዜጐቻችንን ለማዳንና ወደ አገር ቤት ለመመለስ እየተረባረብን ነው በማለት ጉዳዩ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት ተናገሩ፡፡
ህገወጥ ደላሎች እንደ አሸን በመፍላታቸውና ኤጀንሲዎች በመበራከታቸው በርካታ ዜጐች ለስቃይና ለእንግልት መዳረጋቸውን የገለፁት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ በሳኡዲ የተከሰተውን ችግር በሚመለከት መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በስደተኛ ዜጐቻችን ላይ በደረሰው ስቃይ የሳኡዲና የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ናቸው በማለት የሰጡት አስተያየት ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ በሰፊው መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ “መንግስት፤ ህገወጥ ናችሁ የተባሉ ዜጐቻችን ህጋዊ ተቀባይነት እንዲያገኙ፣ አልያም ወደ አገር እንዲመለሱና ህገወጥ ስደትን ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡” ብለዋል ዶ/ር ቴዎድሮስ። ዜጐችን ለማገዝ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጉዳዩን በፖለቲካ አጀንዳነት መጠቀም ተገቢ አይደለም ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ የወረደ፣ የረከሰ አካሄድ የኢትዮጵያዊነት ምልክት አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡
በተለያየ አቅጣጫ የገቡና ለሃጂና ኡምራ ሄደው እዚያ የቀሩ፣ ለበርካታ ዓመታት ቁጥራቸው እየተበራከተ ዛሬ እስከ 80 ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን በሳኡዲ እንደሚኖሩ የገለፁት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ከ38 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ህጋዊ ፈቃድ የላችሁም የተባሉትን በሚመለከት አስቸኳይ በጀት በመመደብ በቀን ከ4ሺ በላይ ዜጐች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በርካታ ዜጐች ላይ ጉዳት እንደደረሰና እስካሁን በተረጋገጠው መረጃ 3 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ “የሚሞቱና ጉዳት የሚደርስባቸውን ዜጎች በተመለከተ ከሳኡዲ ተወካይ ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፤ የህግ አማራጮችም ሊታዩ ይችላሉ፡፡” ብለዋል፡፡
መንግስት ጠንከር ያለ እርምጃ አልወሰደም በሚል የሚቀርበውንም ትችት በተመለከተ ተጠይቀው፣ መንግስት ትክክለኛውንና ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ ይቀጥላል ብለዋል።

Read 2990 times