Sunday, 24 November 2013 17:31

የሳውዲ ልኡሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጐበኙ

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(1 Vote)

የሳውዲ ልኡሎችና ባለስልጣናት በአገሪቱ ዋና ከተማ ሪሃድ የሚገኙ 18ሺ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሰሞኑን እንደጐበኙ ተገለፀ፡፡
በሪያድ ከተማ በ“ፕሪስት ኖር ኢስት ሪሃድ ዩኒቨርሲቲ” ጊዜያዊ መጠለያ ተሰጥቷቸው የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን የጐበኙት ልኡል ካህሊድ ቢን ባንዳር አብድልላዚዝና ወንድማቸው ልኡል ተርኪ ቢን አቡድሃል ቢን አብዱል አዚዝ ሲሆኑ ልኡሎቹ ኢትዮጵያውያኑ በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከልኡሎቹ ጋር በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የሳውዲ መንግስት ባለስልጣናት እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ሰአት በስደተኞች ላይ የሚደርሰው እንግልትና ስቃይ ከመጀመሪያዎቹ ቀናት ረገብ እያለ መምጣቱን የጠቆሙ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን፤ ለዚህም ምክንያቱ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን “የወገኖቻችን ጥቃት ይቁም” በማለት በየአገራቱ በሚገኙ የሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ጫና በመፍጠራቸው ሳይሆን እንደማይቀር ዘግበዋል፡፡
በሳኡዲ በሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን እንግልትና ስቃይ በተመለከተ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ ማብራሪያ እንዲሰጠን ብንጠይቅም፣ ማተምያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ ከኤምባሲው ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡  

Read 2420 times