Monday, 25 November 2013 11:15

ቅፅበታዊ አፕሊኬሽኖች ይዞ የመጣው ቴክኖ ስማርት ፎን

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(23 votes)

አፍሪካ ውስጥ በዓመት 4ሚ. ሞባይሎችና መለዋወጫዎች ይሸጣሉ
ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ መገጣጠም የጀመረው ቴክኖ ሞባይል ሰሞኑን ደግሞ ዓለም በአሁኑ ወቅት የሚጠቀምበትን ዓይነት ስማርት ፎን ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቷ ገጣጥሞ ገበያ ላይ አውሏል፡፡
ቴክኖ ስማርት ፎን በርካታ አፕሊኬሽኖች (መገልገያ) እንዳሉትና ፓልም ቻትና ፍላሽ ሼር ልዩ መገለጫው እንደሆነ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡ ፓልም ቻት (Palm chat) ቅፅበታዊ ድምፅና መልዕክት መለዋወጫ ነው፡፡ ይህ ዘዴ ስማርት ፎንና ሌላ ዓይነት ሞባይል የያዙ ሁለት ሰዎች፣ የድምፅና የዳታ መልዕክት በቅፅበት በዓለም ዙሪያ የሚለዋወጡበት መገልገያ ነው፡፡ “ፍላሽ ሼር (flash share) ደግሞ ቴክኖ ስማርት ፎን ይዘው ጐን ለጐን የተቀመጡ ወይም በቅርብ ርቀት ያሉ ሰዎች፣ መደበኛውን የዕለት ተዕለት ኔትዎርክ ሳይጠቀሙ፣ በአንድ ተች ብቻ፣ 20 ሜጋ ፋይል ዶክመንትም ሆነ ምስል ከአምስት ሰኮንዶች ባነሰ ጊዜ (በቅፅበት ማለት ይቻላል) አንዱ ከሌላው መጋራት የሚያስችል መገልገያ ነው” ብሏል የቴክኖ ግሩፕ ኃ.የተ.የግ.ማ ባለአክሲዮንና በኢትዮጵያ የማኅበሩ ምክትል ኃላፊ አቶ ሌቪ ግርማ፡፡
አዲሱን ዘመናዊ ስማርት ፎንና መገጣጠሚያው በአሁኑ ወቅት ያለበትን ደረጃ እንዲነግረኝ ከአቶ ሌቪ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡ ለመሆኑ ይህን ስማርት ፎን በኢትዮጵያ ለመገጣጠም ምን አነሳሳችሁ? በማለት ወደ ውይይታችን ገባን፡፡
በአሁኑ ወቅት፣ ዓለምም ሆነ አፍሪካ ከመደበኛ ሞባይሎች አልፈው በርካታ መገልገያ ወዳላቸው ስማርት ፎኖች ተሸጋግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከመደበኛው ሞባይሎች አልፈው ብዙ መገልገያ ያላቸውን ስማርት ፎኖች እየተጠቀሙ ነው። ስማርት ፎኖችን የመጠቀም ከፍተኛ ፍላጐትና አቅሙም አላቸው፡፡
ይህን የሕዝቡን በርካታ መገልገያ ያላቸው ስማርት ፎኖች የመጠቀም ፍላጐቱን ለማርካት፣ እንደየሰው አቅም ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ዋጋና በርካታ መገልገያ  ያላቸውን በጣም ብዙ ዓይነት ስማርት ፎኖችን በተመጣጣኝ ዋጋ ገጣጥመን አቅርበናል፡፡
ቴክኖ ስማርት ፎን፤ እንደ አፕልና ጋላክሲ ካሉ ስማርት ፎኖች ጋር ሲነፃፀር ምን ተመሳሳይነትና ልዩነት አለው?
በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ሦስት የስማርት ፎን ደረጃ አለ፡፡ በአንድሮይድ ኦፐሬቲንግ ሶፍትዌር የሚጠቀሙ አሉ፡፡ ተፎካካሪዎቻችንም የሚጠቀሙት አንድሮይድ ሶፍትዌር ነው፡፡ ሁለተኛው አፕል የሚጠቀመው አይ ኦ ኤ (IOM) ኦፐሬቲንግ ሶፍትዌር ነው፡፡ ሦስተኛው ማይክሮሶፍት የሚጠቀምበት ዊንዶው ኦፐሬቲንግ ሶፍትዌር ነው። የስማርት ፎን ኢንዱስትሪ የሚጠቀመው፣ በእነኚህ ሶፍትዌሮች ነው፡፡ በሦስቱም ደረጃዎች ኦፐሬቲንግና አፕሊኬሽን ሲስተም አለ፡፡ ሦስቱም ሶፍትዌሮች ናቸው፡፡ እኛም በምንገጣጥማቸው ስማርት ፎኖች እየተጠቀምን ያለው አንድሮይድ ሶፍትዌርን ነው፡፡
በሌሎች ስማርት ፎኖች የሚገኙ መገልገያዎች በሙሉ፣ በእኛም አሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእኛ ስማርት ፎኖች ሀገር በቀል መገልገያዎች አላቸው፤ ለምሳሌ “ጉርሻ” የተባለ ጨዋታ፡፡
ሀገራዊ አፕሊኬሽን ይኖረዋል ሲባል ምን ማለት ነው?
ከተለያዩ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት እየተነጋገርን ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ጋዜጣውን በዌብሳይት ከመፈለግ ይልቅ፣ በምናዘጋጀው መገልገያ በቀላሉ በስማርት ፎን ማግኘት ይቻላል፡፡ ሶፍትዌር ከሚሠሩ በርካታ ድርጅቶችም ጋር ለመስራት እየተነጋገርን ነው፡፡ ይህን የምናደርገው፣ ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት የሚጠቀመውን ዓለም አቀፍ መገልገያዎችን በመጠቀም ነው፡፡ ወደፊት ግን የድርጅቶችን ፋይል በሀገር ውስጥ ቋንቋ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው ያለምነው፡፡
ቴክኖ ስማርት ፎን በምን ቋንቋ ነው የሚሠራው?
ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ በሦስት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግሪኛ ቋንቋዎች ይሰራል፡፡ በርካታ መገልገያዎች ስላላቸው፣ ብዙ ሰው በማያውቀው ቋንቋ መጠቀም ይፈራል፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ በሌሎችም ቋንቋዎች፣ ለምሳሌ የሱማሊኛ፣ የአፋርኛ፣ የሲዳምኛ፣…ቋንቋዎች ለመጨመር አቅደናል፡፡ በእነዚህ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሌሎችም ቋንቋዎች እንጨምራለን፡፡
በአሁኑ ወቅት ስንት ዓይነት ስማርት ፎን ለገበያ አቅርባችኋል?   
አሁን ለጊዜው ያቀረብነው አምስት ዓይነት ነው። በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ደንበኞቻችን እንደየ ፍላጐታቸው የተለያየ አማራጭ እንዲኖራቸው፣ የተለያየ መገልገያ ባላቸው ስማርት ፎኖች ገበያውን እናጥለቀልቀዋለን፡፡
ዋጋቸው እንዴት ነው? የውጪዎቹ ውድ ይመስሉኛል፡፡ የእናንተም እንደዚያው ነው?
አይደለም፡፡ የደንበኞቻችንን አቅም ያገናዘቡ ናቸው፡፡ አሁን ያቀረብነው ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ አቅም ላላቸው ደንበኞች ነው፡፡ ትልቁ ዋጋ 8ሺ ብር ነው፡፡ 2600፣ 2900፣ 3000፣ 3250 ብር…የሚሸጡም አሉ፡፡
የስማርት ፎን መለዋወጫና ጥገና ማዕከል አላችሁ?
ለምንገጥማቸው ሞባይሎች መለዋወጫ የምናመርተው እዚሁ ነው፡፡ ጥገናን በተመለከተ ለስማርት ፎን፣ ለጊዜው በአዲስ አበባ በሁለት ቦታ እየሠራን ነው፡፡ ፒያሳ ቸርችል ጐዳና በሀሮን ሕንፃና መገናኛ አካባቢ በዘፍመሽ ሕንፃ፡፡ እስካሁን በክፍለ ሀገር ከተሞች ሀዋሳ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ ጐንደር፣ ጅማ የጥገና ማዕከላት አሉን፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ደግሞ በአዳማ፣ በድሬዳዋ፣ በመቀሌና በሆሳዕና እንከፍታለን፡፡
ሌላው ደግሞ፣ በዚህ ዓመት ቤቱ ሙሉውን፣ ግማሽ፣ ሩብ የቴክኖ ሞባይል ሊሆን ይችላል እንጂ፣ ደንበኞቻችን የስማርት ፎን መገልገያውን አውቀው፣ ሞክረው፣ አማርጠው የሚገዙባቸው 100 ሱቆች ለመክፈት አቅደናል፡፡ እኔ በግሌ፣ ደንበኞቻችን መጥተው አይተው፣ መገልገያውን ሞክረውና ተለማምደው የሚገዙበትን፣ ከኤድናሞል አጠገብ በሚገኘው መድኃኒዓለም ሕንፃ ላይ ብራቦኮም የተባለ የመጀመሪያውን ሱቅ ከፍቻለሁ፡፡
እዚህ የሚገጣጠሙትን ሞባይሎች ወደውጭ አገራት ለመላክ ዕቅድ አላችሁ?
አዎ! ምርቶቻችንን ወደውጭ አገራት ለመላክ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ምርቶቻችንን ከሚቀበሉ አገራት ደንበኞቻችን ጋር ተስማምተን ጨርሰናል፡፡ የሚቀረን ስምምነት ከባንክ ጋር ብቻ ነው፡፡
ወደየት አገር ለመላክ ነው ያሰባችሁት?
ቴክኖ ቀደም ሲልም አፍሪካ ውስጥ ግዙፍ የገበያ ድርሻ አለው፡፡ ቴክኖ፣ አፍሪካ ውስጥ በዓመት አራት ሚሊዮን ሞባይሎችና መለዋወጫዎች ይሸጣል፡፡ ስለዚህ በገበያ በኩል ችግር አይገጥመንም፡፡ ጥያቄው እዚህ አገር መገጣጠም ያለበት ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ትልቁ ጠቀሜታዋ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ የአህጉሪቱን በርካታ አገሮች ስለሚያካልል፣ ዕቃዎችን በቀላሉ ያደርስልናል፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ኢትዮጵያ፣ ከሌላ የአፍሪካ አገር የበለጠ በጣም ተጠቃሚ ናት፡፡ ከባንክ ጋር የምናደርገውን ስምምነት ከቋጨን፣ ኤክስፖርት ማድረጋችን ተረጋገጠ ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅማችሁ ምን ያህል ነው? በቀን፣ በወር፣ በዓመት ምን ያህል ትገጣጥማላችሁ? በገበያ ውስጥ ያላችሁ ድርሻ ምን ያህል ነው?
በተለያዩ ምክንያቶች፣ እኛ አንደኛ ነን፣ ሁለተኛ ነን፣ ማለት አንችልም፡፡ ማንም ሰው ቢሆን የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይዝ እንደዚያ ማለት አይችልም፡፡ ነገር ግን ቀዳሚ ነን ማለት የምንችል ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በወር 200ሺህ ሞባይሎች እንገጣጥማለን። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባይኖርብን ከዚህ እጥፍ እንደርስ ነበር፡፡ ወሳኙ ነገር፣ የገበያው ፍላጐት ሳይሆን፣ የውጭ ምንዛሪ መኖር ነው፡፡
የቴክኖ ስኬት ምስጢር ምንድነው?
የምንገጣጥማቸው ዕቃዎች ጥራት ነው። የሞባይሎቻችን ባትሪ ረዥም ዕድሜ አለው። ከዚህም በተጨማሪ፣ በርካታ የጥገና ማዕከላት ስላሉን፣ ለሸጥናቸው ሞባይሎች የ13 ወር (12+1) ዋስትና እንሰጣለን፡፡ ወደፊትም በምርቶቻችን ጥራት እንቀጥላለን፡፡
አሁን ቴክኖ ስንት ሠራተኞች አሉት?
400 ያህል ሠራተኞች አሉን፡፡ ባለፈው ዓመት ጁላይ ላይ 2ኛ ምዕራፍ ስንጀምር፣ የሠራተኞቻችን ቁጥር 100 ነበር፡፡ ከዚያ ጋር ሲነፃፀር፣ በአንድ ዓመት በጣም ብዙ ነው የጨመረው፡፡ እንደ እቅዳችን በዚህ ጊዜ ሊኖረን የሚገባው 300 ያህል ሠራተኞች ነበር፡፡ እኛ ግን ያንን ቁጥር አልፈናል፡፡ በጥቂት ዓመት የሠራተኞቻችን ቁጥር ከ600 እንደሚበልጥ እንጠብቃለን፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከኢትዮ አይ ቲ መንደር 25ሺህ ካ.ሜ ቦታ ወስደን 3ኛ ምዕራፍ የሞባይል መገጣጠም ጀምረናል፡፡ ያንን ቦታ ለፋብሪካና ለቢሮ እንጠቀምበታለን፡፡ ለማስፋፊያ ደግሞ ሌላ 15ሺህ ካ.ሜ ቦታ እየጠየቅን ነው፡፡ በከፍተኛ መጠን ለማምረትና ኤክስፖርት ለማድረግ በአጠቃላይ 40ሺህ ካ.ሜ ቦታ ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡
የስማርት ፎኑ መለያ “የኔም” ነው፡፡ የኔም ማለት Mine (በኢትዮጵያ የተሠራ) ማለት ነው፡፡  
በቴክኖ ስማርት ፎን መጽሐፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርአን ማንበብ ይቻላል፤ ብዙ የኤሌክትሮኒክስ መጽሐፎችም ይዟል፡፡ ላፕቶፕ ሳይጠቀሙ ቢዝነስዎን በፒፒቲ/ኤክሰል/ወርድ/ ፒዲኤፍ ማከናወን ይችላሉ፡፡ መገልገያ ሲስተሙ አንድሮይድ 4.2፣ ማሳያው 5.0 ኤች ዲ ተች ስክሪን፣ ፕሮሰሰሩ 1.2 ኒጋ ኸርዝ ኩዳ ኮር፣ ካሜራ 8.0 ሜጋ ፒክሰል፣ የኋላ ካሜራ ከፍላሽ ጋር 1.2 ሜጋ ፒክስል፣ ሜሞሪ 4. ጂቢተ 1ጂቢ ራም እስከ 32 ጂቢ ውጫዊ ሜሞሪ የሚቀበል፣ መልዕክት አላላክ፣ ኤስ ኤን ኤስ ጂ ሜይል፣ ፌስ ቡክ…ግንኙነት ጂፒ ኤስ፣ ዋይፋይ፣ ብሉቱዝ 3.0፣ ዩኤስ ቢ፣ ጆሮ ማዳመጫ፣ የባትሪ አቅም ቢ ኤል. 3 ኤፍ፣ ሴንሰር ዲ ሴንሰር፣ የብርሃን ሴንሰር፣ ፕሮክሲሚቲ ሴንሰር፣ የጐግል ካርታ፣ ጌም ሶፍት፣ ኤፍ ኤፍ ሬዲዮ፣ ድምፅ መቅረጫ፣…አለው፡፡    

Read 8322 times