Saturday, 30 November 2013 10:38

600 % የቤት ኪራይ ጭማሪ የተደረገባቸው ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታ አቀረቡ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ ለበጎ አድራጐት እንዲውል ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ባሠሩት ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ተከራዮች፣ ዓመት ሳይሞላ ሁለት ጊዜ 120 እና 600 ፐርሰንት የሚደርስ የቤት የኪራይ ጭማሪ ተደረገብን ሲሉ አማረሩ፡፡ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ፈንድ፣ ቀጥሎም የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በተባለው ሕንፃ የሚኖሩ ተከራዮች፤ መኝታ ክፍል የሌለው 43 ካ.ሜ ስቱዲዮ 2005 ብር ይከፍሉ የነበረው 600 ፐርሰንት ያህል ጭማሪ ተደርጐባቸው 9.030 ብር፣ 90ካ.ሜ የሆነው ባለ ሁለት መኝታ ክፍል 3.495 ብር የነበረው 20.370 ብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው፣ ቅሬታና በደላቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደብዳቤ ገልፀው ከመበተን እንዲያድኗቸው ጠይቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ባለፈው መጋቢት ወር ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ የወቅቱን ሁኔታ ያላገናዘበ የ120 ፐርሰንት ጭማሪ ተደርጐብን ምንም አማራጭ ስለሌለን፣ ፍትሐዊ ያልሆነውን የኪራይ ጭማሪ ተሸክመን ሳለ፣ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በያዝነው ወር፣ እስከ 600 ፐርሰንት የሚደርስ የኪራይ ጭማሪ ተደረገብን በማለት ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት የተደረገውን ኢ-ፍትሐዊ የቤት ኪራይ ጭማሪ፣ ልጆቻችንን ካስገባንበት ት/ቤቶችና ለመ/ቤቶቻችን ባለው ቅርበት ሳንወድ ብንቀበለውም፣ ድርጅቱ የፈፀመብን በደል አልበቃ ብሎትና የቆመለትን ማኅበራዊ ኃላፊነት በመዘንጋት፣ በቤት ኪራይ ጭማሪው ተስማምተን እንድንኖር፣ ካልሆነም ኅዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ቤቱን እንድንለቅ ውሳኔ ማስተላለፉ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ መንግሥት በውጭ አገራት በደልና እንግልት የተፈፀመባቸውን ዜጐች ወደ አገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረትና ርብርቦሽ እያደረገ፤ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ለማረጋገጥና በዘርፉ የሚታየውን የቤት ችግር ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እየተጋ ባለበት ወቅት፣ ዜጐችን ያለ አግባብ ማፈናቀል፣ በሥርዓቱ ላይ ጥላቻ እንዲያድርብን ከማድረጉም በላይ፣ የተያያዝነውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስለሚቃረን በእንጭጩ መገታት እንዳለበት እናምናለን ብለዋል፡፡ በሕንፃው ውስጥ ከ10 እስከ 36 ዓመታት መኖራቸውንና በራሳቸው የተመዘገበ ቤት እንደሌላቸው የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከ40 እስከ 80 ዕድሜ ውስጥ ያሉ ስለሆነና ቤት ተሯሩጠው ለማግኘት አቅም ስለሌላቸው፣ ከ40 በላይ ሰዎች የሚያስተዳድሩት አባወራዎች ሜዳ ላይ ከመበተናቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብአዊ ውሳኔ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል፡፡ ተከራዮቹ 120 ፐርሰንት በተጨመረባቸው ጊዜ መኝታ ክፍል ለሌለው 43 ካ.ሜ ስቱዲዮ፣ 2005 ብር ይከፍሉ የነበረው በአዲሱ ጭማሪ 9,030 ብር፣ ባለ ሁለት መኝታ 90 ካ.ሜ ክፍል፣ ባለፈው ዓመት ጭማሪ 3,495 ብር፣ በአዲሱ ደግሞ 20,370 ብር እንዲከፍሉ እንደተወሰነባቸው አስረድተዋል፡፡

Read 2539 times