Saturday, 30 November 2013 10:49

በኩዌት ያነጋገርኳቸው ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(3 votes)
  • የአገሩን ከፍተኛ ሙቀት መቋቋም አቅቷቸው ይሰቃያሉ
  • የመንገድ አጠቃቀም ባለማወቅ ለመኪና አደጋ ይዳረጋሉ
  • ድብደባና የሰሩበትን ደሞዝ መከልከል የተለመደ ነው  


በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ወደ ኩዌት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች  በሁለቱ መንግስታት መካከል የስራ ስምምነት

በመኖሩ የሚገጥማቸው ፈተና ከሌሎች የአረብ አገራት በንፅፅር የተሻለ ነው ሊባል ይችላል። ሆኖም ችግርና መከራው

አይቀርላቸውም። በመጀመርያ ደረጃ ከዚህ ሲሄዱ ስለኩዌት  አጠቃላይ ሁኔታ ምንም መረጃ ሳይኖራቸው ነው፡፡ በስራ

ላይ ስለሚያጋጥሙ አለመግባባቶች፣ አደጋ ቢደርስ ስለሚከፈል ካሳ፣ ኮንትራት ስለሚፈርስበት ሁኔታ ወዘተ … ምንም

የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ወደ ሌሎች የአረብ አገራት እንደሚጓዙት ሁሉ እነዚህም በቂ የሙያ ስልጠና እንዲሁም

የስነልቦና ዝግጅትም የላቸውም፡፡  ከዚህ የሚልኳቸው ኤጀንሲዎች ደግሞ ጥቅማቸውን ብቻ ነው የሚያስቡት፡፡ በመሃል

እነዚህ ለአገሩ ባዳ ለህዝቡ እንግዳ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መከራቸውን ይበላሉ፡፡
ባለፈው ሰሞን በኩዌት የተዘጋጀውን ሶስተኛውን የአፍሪካ አረብ ጉባኤ ለመዘገብ ወደዚያው አምርቼ በነበረ ጊዜ እዚያ

ስላሉ ኢትዮጵያውያን በመጠኑ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ አንዳንድ የሚያሳዝኑና የሚያስገርሙ ነገሮችም ሰምቻለሁ፡፡ አንዲት

በቤት ሰራተኝነት የተቀጠረች ኢትዮጵያዊት፣ ገና አገሩን ሳትላመድ በፊት አሰሪዎቿ ሲወጡ እየጠበቀች ግቢ ውስጥ

ትፀዳዳ ነበር፡፡ በሁኔታው ግራ የተጋቡት አሰሪዎቿ፤ ነገሩን ተከታትለው ይደርሱበትና ለምን  መፀዳጃ ቤት

እንደማትጠቀም ሲጠይቋት “እንዴት እዚህ ንፁህ ነገር ላይ እፀዳዳለሁ” ብላ እንደመለሰችላቸው ተነግሮኛል፡፡ ከኢትዮጵያ

ቀዝቃዛ አካባቢዎች በተለይ ከባሌ የሚሄዱ ሴቶች ደግሞ ስለኩዌት ከፍተኛ የአየር ሙቀት ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ

እየሄዱ፣ አየሩን መቋቋም አቅቷቸው ይሰቃያሉ፡፡ በመንገድ አጠቃቀም ችግር የተነሳም በመኪና አደጋ አካላቸው

ይጐድላል፡፡ ህይወታቸውን የሚያጡም አሉ፡፡
 በህጋዊ መንገድ ወደ ኩዌት ከሄዱ በኋላ የተለያዩ ችግሮች የገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ያሉበት  መጠለያ የሚገኘው

ጃብሪያ በተባለ ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ መጠለያው በኩዌት መንግስት እና በኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር የተከፈተ ሲሆን

በአሁኑ ሰአት መጠለያውን የሚያስተዳድሩት ግለሰብ በትውልድ ፍልስጤማዊ በዜግነት ዮርዳኖስ ናቸው፡፡ በመጠለያው

ውስጥ ከአስራ አምስት የማያንሱ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን አግኝቻለሁ። የመጠለያው ሃላፊ እንደሚሉት ቁጥራቸው

በየጊዜው ይለዋወጣል፡፡ አዲስ ገቢዎች ይመጣሉ። የገቡት ደግሞ ወይ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ አሊያም  እዚያው ስራ

ይጀምራሉ፡፡ በመጠለያው ውስጥ ካገኘኋቸው ሴቶች መካከል ጥቂቶቹን ያነጋገርኳቸው ሲሆን ስማቸውና ምስላቸው

እንዲወጣ ስላልፈቀዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ብቻ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

“አሰሪዬ ትደበድበኝ ነበር”
የመጣሁት ከደቡብ ወሎ ደሴ ካራጉቱ አካባቢ ነው፡፡ ከአገሬ ከመጣሁ ስምንት ወሬ ነው፡፡ እድሜዬ ሀያ  ነው፡፡ እዚህ

መጠለያ የመጣሁት ከአሰሪዎች ጋር ስላልተስማማሁ ነው፡፡ መጀመሪያ የገባሁበት ቤት አሰሪዬ ትደበድበኝ ስለነበር

ቀየርኩ። ተመልሼ የገባሁበትም ቤት ተመሳሳይ ችግር አጋጠመኝ። ታስፈራራኛለች፡፡ “ስራ አትስሪ ከኔ ጋር ቁጭ በይ፤

ሌሎች ሰራተኞች ይሰራሉ” ትለኝና መልሳ ለምን አልሰራሽም ብላ ትመታኛለች። አንድ ቀን ስትመታኝ ጆሮዬን በጣም

ስላመመኝ ወጥቼ ጠፋሁ። ተመልሼ ሁለት ወር ሰራሁ እና ደሞዜን አልሰጠኝ አለች፡፡ ለምን አትሰጭኝም ስላት  

አስወጥታ በር ዘጋችብኝ። ሌላ ቦታ አስራ አምስት ቀን ሰራሁና “ከኤምባሲ ትፈለጊያለሽ” ተብዬ እዚህ መጣሁ፡፡ አሁን

የምፈልገው የቀረብኝ የአራት ወር ደሞዜ ተሰጥቶኝ ሌላ ስራ መግባት ነው፡፡
         
“ልጄ ሳይሞትብኝ ልድረስ ብዬ ወጣሁ”
አገሬ ወግዲ ወረዳ ጫቃታ ቀበሌ ነው፡፡ ባለትዳር እና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ነኝ፡፡ እዚህ ከመጣሁ ሁለት አመት

ጨርሻለሁ፡፡ ከአገሬ በሴትየዋ ስልክ ደውለው “አባቴ ሞተ” ብለው ነገሩኝ፡፡ “ልሂድ” ስላቸው “ቆይ ትሄጃለሽ” ብለው

አሰነበቱኝ፡፡ ከዛ ደግሞ “ልጅሽ ታሟል ድረሽ” ተባለና ተደወለ፡፡ “እባካችሁ ለስምንት ቀን ፍቀዱልኝ፤ ሄጄ ልምጣ፤

አባቴ እዚህ ሆኜ ሳላየው ሞተ፡፡ ልጄም ሳይሞትብኝ ልሂድ” ብላቸው፤ አሁን አትሄጂም አሉኝ፡፡ እኔ እሄዳለሁ አልኩ፡፡

በመሀል መስራት ስላልቻልኩ የሰውየው እናት እዚህ አመጣችኝ፡፡ እኔ መሳፈርና መሄድ ነው የምፈልገው፡፡ አባቴም

ሞተብኝ፡፡ መልሶ ልጄ ሳይሞትብኝ ልድረስ ብዬ ወጣሁ፡፡ እኔ ፍላጎቴ ለመሳፈር ብቻ ነው፡፡ አሰሪዎቼ በጣም ደህና

ሰዎች ናቸው፡፡ ሰላመኛ ናቸው፡፡ እኔ ልጄን አይቼ ነው የምመለሰው፡፡ አባቴ ሞቶ ልጄ ቢደገም እንዴት ብዬ እቆማለሁ፡፡
“ልሂድ ስላቸው የኛስ ኪሳራ ይሉኛል”         
አገሬ ከገፈርሳ በላይ ያለ ገጠር ነው፡፡ የሶስት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ከአገሬ  ከመጣሁ አንድ አመት ጨርሻለሁ፡፡ እዚህ ጤና

አላገኘሁም፡፡ ሀኪም ቤት ስወሰድ ሀኪሞቹ “የማህፀን ችግር አለብሽ፤ ኦፕራሲዮን ትሆኛለሽ” ይሉኛል፡፡ እኔ ደግሞ የሰው

አገር ሰው ነኝ፡፡ ማንም አጠገቤ የለም፡፡ አባቴ የለ፤ እህትና ወንድሜ የሉ፤ እናቴ የለች፡፡ ፈራሁ። “መሄድ እፈልጋለሁ፤

አገሬ ላይ የምሆነውን እሆናለሁ” ስል የኛስ ኪሳራ ይሉኛል፡፡ ኮንትራትሽ ሁለት አመት ስለሆነ ሁለት አመቱን ጨርሰሽ

መሄድ አለብሽ አሉ፡፡ እኔ ደግሞ እዚህ በበሽታ እሰቃያለሁ፤ ቆሞ መስራት አቃተኝ፡፡ በሽታ አስቸገረኝ እንጂ ስራ

እወዳለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ከአቅሜ በላይ ሆነ፡፡ እዚህ መጠለያ ከገባሁ አንድ ወሬ ነው፡፡ እኔ ከታመምኩ በኋላ ብር

አይሰጡኝም፡፡ እዚህ መጠለያ ከገባሁ በኋላ “አስተዳዳሪው እዚህ ከምትቀመጪ ስራ ብትገቢ” ብሎኝ ሞከርኩ፤ ግን

ምንም አልቻልኩም። አሁን ራሱ ሆስፒታል አድሬ ውዬ መምጣቴ ነው። ለቤተሰቦቼም እስከአሁን ይሄ ገጠመኝ

አላልኩም። እዚህም አገር እህት አለችኝ፤ ስልክ ቁጥሯን የምሰራበት ቤት ጥዬ ስለወጣሁ እስከአሁን አልሰማችም፡፡
 
“ወይ ደህና ህክምና አላገኘሁ ወይ አገሬ አልገባሁ”
የመጣሁት ከአዲስ አበባ ነው፡፡ ስምንት ወሬን እየጨረስኩ ቢሆንም የሰራሁት አራት ወር ብቻ ነው፡፡ ስራ እየሰራሁ ሳለ

በእሳት ተቃጠልኩና ያመጣኝን ኤጀንሲ ስነግረው፣ ምንም ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ሁለቱም እግሬ ተቃጥሏል። ቀኝ

እግሬ በጣም ተጎድቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ካሳ ይገባታል” ሲል እነሱ “በራሷ ጊዜ ነው የተቃጠለችው” አሉ፡፡ “ስራ

ላይ እያለች ስለተቃጠለች ካሳ ያስፈልጋታል” ብሎ ነበር ግን  ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ የሰራሁበት ገንዘብ፣ ፓስፖርቴ እና

ልብሴ ያለው አሰሪዎቼ ቤት ነው። ይህን ማስመጣት የሚችለው ኤጀንሲው ነው፡፡ ግን አከሰርሽኝ በሚል ሊተባበረኝ

አልቻለም፡፡ ወይ ደህና ህክምና አላገኘሁ ወይ አገሬ አልገባሁ፡፡ ክርክር ላይ ነኝ፡፡ እኔ አገሬ መግባት እፈልጋለሁ፡፡

“ባዶ እጄን ወደ አገሬ እመለሳለሁ”
ሰፈሬ ኮተቤ ነው፡፡ ከመጣሁ ሰባት ወር ሆኖኛል። መጀመሪያ የገባሁበት ቤት በጣም ችግር ነበር፡፡ ስራ በጣም ይበዛል፡፡

ምግብ አልተስማማኝም፡፡ ቤት ለመቀየር ስጠይቅ፣ ኤጀንሲው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ አልሰራም ብዬ ቁጭ ስል፣ አሰሪዬ

ዘመዷ ቤት ወስዳ ዘጠነኛ ፎቅ ላይ ለስምንት ቀን በረሀብ እያሰቃየች አቆየችኝ፡፡ ካስወጣችኝ በኋላ ኤጀንሲዬ ጋር

ስደውል “ህግ ያለበት አገር ነው፤ ምንም ላደርግልሽ አልችልም፣ ያለሽ አማራጭ መጥፋት ብቻ ነው” አለችኝ፡፡ ታምሜ

ሆስፒታል ስወሰድ ጠፋሁ፡፡ ኤጀንሲዬ ኤምባሲ አመጣችኝ፡፡ ሴትዮዋ በማግስቱ ዘመዷን ይዛ መጥታ “እነሱ ጋር ስሪ”

ስትለኝ፤ አልፈልግም አልኩ፡፡ “ያከሰረችኝን ትክፈልና ትሂድ” አለች፡፡ “እኔ ምንም የለኝም፤ ንብረቴ ሁሉ አንቺ ጋ ነው”

አልኳት፡፡ ሁለት ጊዜ ተመላልሳ ልውሰድሽ አለችኝ፤ አልፈልግም ስላት ፓስፖርቴንና ትኬቴን ይዛ መጣች፤ ስለዚህ ነገ  

ባዶ እጄን ወደ አገሬ እመለሳለሁ፡፡

የደፈረኝ ኢራናዊ አልተገኘም
የመጣሁ ከሀረር ነው፡፡  አንደ አመት ከስድስት ወሬ ነው፡፡ አንድ የማውቃት ኢትዮጵያዊት የተሻለ ስራ አግኝቼልሻለሁ

ብላ ደወለችልኝና ታክሲ ይዛ መጣች፡፡ ቤተሰብ ያለው ሰው ነበር ያናገረችው፤ ሄድኩኝ፡፡ አምስት ልጆችና ሚስት

አለው፡፡ ቅዳሜ፤ ልጆቹ የእረፍት ቀናቸው ነበር፡፡ ቤተሰቡን እንዳለ ሌላ ቦታ ወስዶ ማታ አንድ ሰአት ላይ ለብቻው

ሰክሮ መጣና አስገድዶ ደፈረኝ፡፡ ሴትዮዋ ስታየኝ “ምን ሆነሽ ነው?” ብላ ጠየቀችኝ፤ እንዳልነግራት ፈርቼ “ወድቄ ነው”

አልኳት፡፡ ጠዋት ወጣሁና  ኤጀንቷ ጋር ሄድኩ፡፡ “ለምን እንደዚህ ታደርጊኛለሽ?” ብዬ ስንደባደብ “መቶ ዲናር ከፍሎኝ

ነው” አለችኝ። ፖሊስ ጋ ሄጄ ነገርኩ፡፡ ሁለታችንንም እስር ቤት አስገቡን፡፡ አንድ ወር ቆየን፡፡ እሷ ድርጊቷን ስላመነች

ወደ ኢትዮጵያ አሳፍረዋታል፡፡  እኔን ወደ ኤምባሲ ሂጂ አሉኝ፡፡ ኤምባሲ ሄድኩ፤ ከዛ የማውቃቸው ልጆች ስራ

አስገቡኝ፡፡ እሰከ አራት ወር ደሜ ሳይመጣ ሲቀር፣ እቃዬን ይዤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄድኩኝ፡፡ እዛው ቆይቼ ወለድኩ፡፡

አሁን ሶስት ሳምንት ሆኖኛል ከመጣሁ፡፡ የወለድኩት ከኩዌት ዜጋ አለመሆኑ ስለታወቀ “ልጅሽን ይዘሽ አገርሽ

ትሳፈሪያለሽ” ተብዬ እየተጠባባቅሁ ነው። የደፈረኝ ኢራናዊም አልተገኘም፡፡ የወለድኩትን ልጅ እናሳድግልሽ የሚሉ ሰዎች

በተደጋጋሚ ይመጣሉ። እንዴት አድርጌ ልስጣቸው፡፡ አገሬ ላይ ድንጋይ ተሸክሜም ቢሆን አሳድገዋለሁ፡፡ ከመደፈር

አንስቶ እስከዛሬ ስንት የተሰቃየሁበት ልጄ ነው፡፡ አሁን ሶስት ወር ከአስራ አምስት ቀኑ ነው፡፡
እዚያው መጠለያ ውስጥ ያገኘኋት ሌላ ኢትዮጵያዊት ደግሞ ምንም አትናገርም፡፡ የመጠለያው አስተዳዳሪ “ይቺን

የማትናገር ልጅ እንዴት ለስራ ከኢትዮጵያ ላኳት?” ሲል እኔኑ ጠየቀኝ፡፡ እውነት የማትናገር መስሎኝ በመገረም “ከየት

ነው የመጣሽው?” ብዬ ብጠይቃት እንባዋን ዘረገፈችው፡፡ መጠለያው ውስጥ ከገባች ጀምሮ ከማንም ጋር ተነጋግራ

እንደማታውቅና ምን እንደሆነች ስትጠየቅ ማልቀስ እንደምትጀምር ነገሩኝ፡፡ እኔም ስለያት እያለቀሰች ነበር፡፡ የትም ሆነ

የትም የስደት ነገር ትርፉ ሰቆቃና ለቅሶ ነው - በተለይ ለኢትዮጵያውያን፡፡

Read 4903 times