Saturday, 30 November 2013 11:06

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ከተቃዋሚዎች ጋር ተወያዩ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(7 votes)

በአወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም ምርጫ የታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት አና ጐሜዝን ጨምሮ “ለአፍሪካ ፣ ካሪቢያን፣ ፓስፊክና

የአውሮፓ ህብረት” የጋራ ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ሰሞኑን ከተቃዋሚ ፓርቲ

መሪዎች ጋር  ተወያዩ፡፡
ፓርቲያቸውን ወክለው በውይይቱ እንደተካፈሉ የተናገሩት የኢዴፓ ማዕከላሚ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌው፤

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት የኢትዮጵያ  የዲሞክራሲና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ምን አዲስ ነገር አለ? የወደፊቱ

አቅጣጫ ምን ይሆናል? በማለት ጥያቄ እንደሰነዘሩ ገልፀዋል፡፡ የፓለቲካ ምህዳሩ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊጠናከሩ

የሚችሉበት እድል ከጊዜ ወደ ጊዜ መጥበቡን ተናግሬያለሁ የሚሉት አቶ ልደቱ፣ የሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሂደት

እንደሚያሳስበንና የአውሮፓ ህብረት እርዳታ የፓለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባቸው

አስረድቻለሁ ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ለአገራችን እርዳታ መስጠቱን እንደማንቃወም፣ የእኛን ችግር እነሱ እንዲፈቱ

እንደማንጠብቅ ገልፀንላቸዋል ያሉት አቶ ልደቱ፤  ከዲሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ ማድረግ

የሚገባችሁን ወደኋላ ትታችኋል፤ እርዳታ ሰጪ እንደመሆናችሁ ማድረግ ያለባችሁን ነገር ዘንግታችኋል የሚል አስተያየት

ሰጥቻለሁ ብለዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው፣ የፓለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን፣ የሠላማዊ ትግል ተስፋ

መዳፈኑንና ህገ መንግስቱ እየተከበረ አለመሆኑን እንዳስረዱ ጠቅሰው፤ በነፃው ፕሬስ ህግ፣ ተሻሽሎ በወጣው የፓርቲ

ህግ፣ በፀረ ሽብርተኛ አዋጁ ዙሪያ እንደተወያዩበት ተናግረዋል። በ2002 ዓ.ም. ምርጫ በዝርፊያና በንጥቂያ ኢህአዴግ  

99.6 በመቶ ድምፅ አግኝቶ ማለፉን በመጥቀስ፤ 2007ዓ.ም. የሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ አጣብቂኝ እንደሆነብን

ለአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት አስረድቻለሁ ብለዋል - አቶ አስራት፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝቡን ሰብስበን ማነጋገር፣ ሠላማዊ ሰልፍ  ማድርግ እንዳልቻልንም፣ የመንግስትን ጫና በማሳየት

ገለፃ አድርጌያለሁ በማለት አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት አባላት ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትም

ጋር ቀደም ብለው ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት አና ጎሜዝ፣ አገሪቱ በኢኮኖሚ ማደጓለ እንደሚገልፅና ልማቱ ግን  

ህዝቡን ከድህነት ያላወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም. ለሚደረገው አገራዊ ምርጫም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አና ጐሜዝ ገልፀው፤ ታዛቢዎችን ከመላክ

በተጨማሪ በየሁኔታው እና በየወቅቱ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ መድረክ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በውይይቱ ላይ ተካፋይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡

Read 4727 times