Saturday, 07 December 2013 11:13

ሰማያዊ ፓርቲ በጃንሜዳ የፓናል ውይይት እንዳላደርግ ተከለከልኩ አለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“የተመረጠው ቦታ ለፀጥታ ጥበቃ አመቺ ባለመሆኑ እውቅና ለመስጠት እንቸገራለን”
አዲስ አበባ መስተዳድር
-    ኢ/ር ይልቃል በጄኔቭ ከአይኦኤም፤ ከአይኤልኦ እና ከሂውማን ራይትስ ዎች ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ

ሰማያዊ ፓርቲ አፄ ምኒልክ ያረፉበትን መቶኛ አመት ለማክበር ካዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ውስጥ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና

የፓናል ውይይቱን ታህሳስ ስድስት ቀን በጃንሜዳ ለማድረግ ቢያቅድም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍና

ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል እውቅና እንደከለከለው ፓርቲው አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በበኩሉ፤ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና የፓናል

ውይይት ለማካሄድ የተመረጠው ቦታ ለፀጥታ ጥበቃ አመቺ ባለመሆኑ በፓርቲው የተጠየቀውን እውቅና ለመስጠት

እንደሚቸገር በፃፈው ደብዳቤ ለፓርቲው አሳውቋል፡፡
ፓርቲው በበኩሉ፤ በጃንሜዳ የምናካሂደው የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና የፓናል ውይይት በመሆኑ ብዙ እንቅስቃሴ

የለውም፣ ጃንሜዳም ቢሆን ለፀጥታ አስጊ ቦታ አይደለም፤ ስለዚህ መስተዳድሩ እውቅና ላለመስጠት ያቀረበው ምክንያት

የህግ ድጋፍ የለውም በመሆኑም፤ ፕሮግራሙን በጃንሜዳ አካሂዳለሁ ሲል ለመስተዳድሩ ደብዳቤ ፅፏል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ብርሀኑ ተክለ ያሬድ፣ መስተዳድሩ እውቀና የከለከለበትን ምክንያት ለምን ፓርቲያቸው

እንዳልተቀበለው ሲያስረዱ፣ ከዚህ በፊት መስተዳድሩ ቦታውን ለሰላማዊ ሰልፍ መፍቀዱን አስታውሰው፣ አሁን ለፓናል

ውይይት እውቅና መከልከሉ ጽ/ቤቱ በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ የዜጐችን የመሰብሰብ መብት የሚገድብ በመሆኑ

ፓርቲያቸው እንደማይቀበለውና ፕሮግራሙን በዕለቱ በቦታው እንደሚያካሂድ፤ ይህንንም ለመስተዳድሩ በደብዳቤ

ማሳወቁን አቶ ብርሀኑ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ባለፈው አርብ ወደ ጀርመን አቅንተው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤

ከትላንት በስቲያ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተገኙ ሲሆን ከአለም የስደተኞች ድርጅት (IOM)፣ ከአለም የስራ ድርጅት (ILO)

እና ከሂውማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል፤ በጄኔቫ የሚገኙ የፓርቲው

ደጋፊዎች ከትላንት በስቲያ ከሶስቱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በተለይም በወቅቱ የኢትዮጵያውያን ስደተኞችና የሳኡዲ

መንግስት ድርጊት ላይ በሰፊው እንደተወያዩ የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አይኦኤም ወደ ኢትዮጵያ ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን የመጠለያ፣ የልብስና ወደ ቤተሰቦቻቸው መጓጓዣ

ጭምር ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑ፣ ከአይኦኤም ጋር ቀይ መስቀልና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች እየተባበሩ እንደሆነ

ለስደተኞቹ ማጓጓዣ የሳኡዲ መንግስት አውሮፕላኖችን ስለመመደቡና እስካሁንም አይኦኤም አምስት ሚሊዮን ዶላር

ስለማውጣቱ፣ የድርጅቶቹ ከፍተኛ አመራሮች ለኢ/ር ይልቃል ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡ አይኦኤም በቀጣይ 13 ሚሊዮን

ዶላር ለኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መመደቡን ለሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የገለፁላቸው ሲሆን ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ

ስለሚመለሱትና እስካሁን ስለተመለሱት ስደተኞች አይኦኤም፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የሳኡዲ መንግስት ትክክለኛው

መረጃ እንደሌላቸው ሶስቱ አለም አቀፍ ድርጅቶች ለኢ/ሩ መግለፃቸው ተጠቁሟል፡፡  

Read 1057 times