Saturday, 07 December 2013 11:21

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ሰኞ አዲስ አበባ ይገባሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

• በአገሪቱ ጉብኝት ያደርጋሉ

ባን ኪ.ሙንን ጨምሮ መቀመጫቸውን ሮም ያደረጉ ሶስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ሰኞ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን የሚመራው የልዑካን ቡድን ከሰኞ እስከ ረቡዕ በሚያደርጉት ጉብኝት ሀዋሳ ላይ በተባበሩት መንግስታት በገንዘብ የሚደገፉ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ ይገመግማሉ የተባለ ሲሆን በተለይም በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ህዝቦች በድርጅቶቹ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው በምግብ ዋስትናና በድህነት ቅነሳ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ማጠናከር ላይ ይመክራሉም ተብሏል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ በታንዛኒያ ጉብኝቱን እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን ለጉብኝቱ ኢትዮጵያና ታንዛኒያ የተመረጡበት ምክንያት የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP)፣ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) እና መሰል የመንግስታቱ ድርጅቶች በድህነት ቅነሳና በምግብ ዋስትና ላይ በገንዘብ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች ስላሏቸው እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ ከዲሴምበር ዘጠኝ እስከ ዲሴምበር 11 ቀን 2013 በአዲስ አበባና በሀዋሳ ቆይታ የሚያደርጉት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን እና አጋሮቻቸው ማክሰኞ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል በ11 ሰዓት ለጋዜጠኞች ስለ ጉብኝቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ረቡዕ ወደ ታንዛኒያ እንደሚያቀኑ አዲስ አበባ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

Read 1298 times