Saturday, 07 December 2013 11:17

በዱባይ፣ በምትሰራበት ቤት ከ12 አመት ታዳጊ ያረገዘች ታሰረች

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(10 votes)

ዱባይ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት የተቀጠረች ኢትዮጵያዊት፣ የ12 አመት እድሜ ካለው የአሰሪዎቿ ልጅ ጋር በመፈፀመችው ወሲብ አርግዛለች በሚል የተከሰሰች ሲሆን፣ ሁለቱም የ6 ወር እስር እንደተፈረደባቸው አጅማን የተሰኘ የዜና ተቋም ዘገበ፡፡ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈፀም በተባበሩት የአረብ ኢሜሬቶች ህግ ያስጠይቃል በሚል የተከሰሰችው ኢትዮጵያዊት፣ የተፈረደባትን የእስር ቅጣት ስትጨርስ ወደ አገሯ ትባረር እንደሆነ የተዘገበ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያዊቷ እርግዝና ሊታወቅ የቻለው በአጋጣሚ መሆኑን ዘገባው ገልፆ፣ ልጃቸውንና የቤት ሰራተኛቸውን ቤት ውስጥ ትተው የወጡ ወላጆች ድንገት ሲመለሱ ጉድ እንደጠበቃቸው ያወሳል፡፡ የ12 አመቱ ልጃቸው፣ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ከ28 አመቷ ኢትዮጵያዊት ጋር ወሲብ እየፈፀመ ደርሰው የተመለከቱ ወላጆች ዝም አላሉም፡፡ ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈፀመ ጉዳይ እንዳልሆነ ያረጋገጡት ግን፣ ኢትዮጵያዊቷ በሆስፒታል ምርመራ እርጉዝ መሆኗ ከታወቀ በኋላ ነው ብሏል ዘገባው፡፡ ፖሊስ በታዳጊውና በቤት ሰራተኛዋ ላይ ክስ ካቀረበ በኋላ፣ ፍ/ቤት በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የስድስት ወራት እስር ፈርዶባቸዋል፡፡ የታዳጊው ጠበቃ፣ ደንበኛዬ ከ18 አመት በታች ስለሆነ ክሱ ተሻሽሎ ቅጣቱ ሊቃለልለት ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ ከቤተሰቡ አባላት ጋር ፀብ ስለነበራት ተንኮል ሰርታለች በማለት መከራከሪያ ያቀረበው ይሄው ጠበቃ፤ ያረገዘችው ከሌላ ሰው ስለሆነ ወደ አገሯ እንዳትባረር ሰግታ ነው በታዳጊው ላይ ሸር የሰራችው በማለት ለማሳመን ሞክሯል፡፡ ጠበቃው በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባይቀናውም በይግባኝ ልጁን ነፃ እንዳስለቀቀ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

Read 8087 times