Saturday, 07 December 2013 11:41

የማንዴላ ሞት አለምን አሳዝኗል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

“አገራችን ታላቅ ልጇን አጥታለች፣ ህዝባችን አባቱን ተነጥቋል፣ ይህቺ ቀን መምጣቷ እንደማይቀር ብናውቅም የዛሬዋ እለት ይዛው የመጣችው ሃዘን ፍጹም ጥልቅና በምንም ነገር የማይሽር ነው!!” የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮቭ ዙማ፣ ጥቁር ለብሰው በአገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉና መሪር ሃዘን ባጠላበት ፊት፣ በተሰበረ አንደበት ተናገሩ፡፡ ይህ ደቡብ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን መላውን አለም ያስደነገጠ፣ የብዙዎችን ልብ ክፉኛ የሰበረ ትልቅ መርዶ ነው - ብሄራዊ ሃዘን፡፡ ከትናንት በስቲያ እኩለ ሌሊት ገደማ አለም የማዲባን መፈጸም ተረዳ፡፡ የጸረ አፓርታይድ ታጋዩ፣ የመብት ተሟጋቹ፣ የነጻነት ተምሳሌቱ፣ የይቅርታ ምልክቱ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ሮሊህላላ ማንዴላ በተወለዱ በ95 አመታቸው ሃሙስ ሌሊት ተፈጸሙ፡፡ ትራንስኪ ላይ የጀመረው የማንዴላ የህይወት ጉዞ፣ ዘመናትን ከዘለቀ የትግል፣ የፈተና፣ የድል… የክፉና የደግ፣ የዳገትና የቁልቁለት ፍሰት በኋላ፣ ከትናንት በስቲያ ጆሃንስበርግ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተቋጨ፡፡ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ ጤና ከራቃቸው አመታት ተቆጥረዋል። የጤናቸው ጉዳይ አልሆን ብሏቸው ከአደባባይ የራቁትና ቤት መዋል የጀመሩት እ.ኤ.አ በ2004 የመጀመሪያዎቹ ወራት ገደማ ነበር፡፡ ጤና ውሎ ማደር ያቃታቸው ማንዴላ፣ ከዚህ በኋላ ያሉትን አመታት በቤታቸውና በሆስፒታሎች መካከል እየተመላለሱ ነው ያሳለፉት፡፡ የጤናቸው ጉዳይ እየዋል እያደር አሳሳቢ መሆኑን የቀጠለው ማንዴላ፣ እስካለፈው መስከረም የነበሩትን ሶስት ወራት ፕሪቶሪያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ክፉኛ የጸናባቸውን የሳንባ ኢንፌክሽን በመታከም ነበር ያሳለፉት፡፡ ህክምናው ተስፋ እማይሰጥ መሆኑ ታውቆ በመስከረም ወር መጀመሪያ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ማንዴላ፣ ዙሪያቸውን በቤተሰቦቻቸው ተከበው በተኙበት ነው ሃሙስ ምሽት ይህቺን አለም የተሰናበቱት፡፡ የማዲባን ህልፈት በውድቅት ሌሊት የሰሙት ደቡብ አፍሪካውያን፣ በእንቅልፍም ሆነ በእረፍት የሚያሳልፉት ቀሪ ሌሊት አልነበራቸውም፡፡ መሪር ሃዘን ልባቸውን የሰበረው ደቡብ አፍሪካውያን ስለ ማንዴላ እንባቸውን አፈሰሱ፡፡ ከሶዌቶ እስከ ፕሪቶሪያ፣ ከኬፕታውን እስከ ጆሃንስበርግ በመላ አገሪቱ ሃዘን ሆነ፡፡ “ማዲባ!... ማዲባ!... ማዲባ!...” ሁሉም ይህን ስም መጥራት፣ ይህን ሰው ማሰብ ያዘ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ስለ ጀግናቸው ሻማ ለኩሰው አደባባይ ወጡ፡፡ በጥቁሩ ጨለማ ውስጥ ‘የጥቁሩን ብርሃን’ ፎቶግራፎች ይዘው ጎዳናዎችን ሞሏቸው፡፡ “ማንዴላን አላየነውም የታሰረበት ሄደን ማንዴላን አላየነውም!...” እያሉ የክፉ ቀን ዜማቸውን አቀነቀኑ፡፡ የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን መዝሙሮችን ከፍ ባለ ድምጽ ዘመሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሰንደቅ ዓላማ፣ በትግልና በመስዋዕትነት ከፍ ላደረጓት የአርነት ታጋዩዋ ዝቅ ብላ ተውለበለበች፡፡ ሀዘኑ የደቡብ አፍሪካውያን ብቻ አይደለም፡፡ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከጃኮቭ ዙማ አንደበት የተሰማውን መርዶ እየተቀባበሉ አስተጋቡት። የአለም ህዝቦች በሰሙት ነገር ክፉኛ ደነገጡ፣ አብዝተው አዘኑ፡፡ “እሳቸው የሰሩት፣ ከማንኛውም ሰው ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ ስራቸውን ፈጽመው ወደማይቀረው ቤታቸው ቢሄዱም፣ ማንዴላ የዘመናት ሁሉ ሃብት ናቸው” አሉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ ከወደ ኋይት ሃውስ ባሰሙት የሃዘን መግለጫ ንግግራቸው፡፡ በሞታቸው ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው በስሜት ተውጠው የተናገሩት ኦባማ፤ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማዎች በሙሉ እስከ ሰኞ ድረስ ስለማንዴላ ክብር ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የአሜሪካም ብቻ ሳይሆን የፈረንሳይና ሌሎች አውሮፓ አገራት፣ የአውሮፓ ህብረት እና የፊፋ ባንዲራዎችም ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ ተወስኗል፡፡ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ መካከለኛው ምስራቅ በአለም ዙሪያ ያሉ የሌሎች በርካታ መንግስታትም ስለ ማንዴላ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን መግለጽ ይዘዋል፡፡ “እጅግ እጅግ አዝኛለሁ! ለአገሩ በጎ ነገር ለማምጣት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሲሰራ የኖረ ታላቅ ሰው ነው፡፡ የማንዴላን ታላቅነት የምትመሰክረው፣ ሰላም ውላ የምታድረው ደቡብ አፍሪካ ናት!” ብለዋል የእንግሊዟ ንግስት ኤልዛቤጥ መርዶውን እንደሰሙ ከቤኪንግሃም ቤተመንግስት ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ መልዕክት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በበኩላቸው፣ “ለፍትህ የተጋ ታላቅ ሰው፣ ለሰው ልጆች የበጎነት ምሳሌና የመነቃቃት ምንጭ” በማለት ነው ማንዴላን የሚገልጹዋቸው፡፡ “በታሪካችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ተገኝቶ ይመራን ዘንድ ማንዴላን የፈጠረልን አምላክ፣ እኛን ደቡብ አፍሪካውያንን አብዝቶ ይወደናል” ያሉት ደግሞ ታዋቂው ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ናቸው፡፡ ከነገ በስቲያ ሰኞ ጆሃንስበርግ ውስጥ በሚገኘውና 90 ሺህ ሰው በሚይዘው ኤፍ ኤን ቢ ስቴዲየም በሚከናወን ብሃራዊ የሃዘን ስነስርዓት በድምቀት የሚዘከሩት ማንዴላ አስከሬን፣ ለሶስት ቀናት ያህል በመዲናዋ ፕሪቶሪያ በህዝብ ሲታይ ይቆያል፡፡ በመጪው ሳምንት መጨረሻም በብሄራዊ ክብር ታጅቦ በምስራቃዊ ኬፕታውን አቅራቢያ በምትገኘው የዕድገት መንደራቸው ኮኑ ወደሚማስለት መቃብር ይሸኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

Read 2666 times