Saturday, 07 December 2013 13:01

እንኳን ለዓመት ጉድ አበቃን!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ዘንድሮም ልክ በዓመቱ፣ እንደአምናና እንደ ሃቻምና
የሐምሌ ጐርፍ ሞላና፣ ይኸው ለዓመት ጉድ
በቃና …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፣ …
ዝግጁው ማዘጋጃ ቤት፣ ዜና መግለጫ ለማውጋት
እንደጥምቀተ ባሕር ወግ፣ የዓመቱን ጐርፍ ለማውሣት
ደረሰ ፍል ውሃ ሜዳ፣ በጋዜጦች አጀብ ብዛት
ለዓመቱ ዜና ገብ ቂጥ፣ “ካሜራ ማን ዙም-ኢን ዙም አውት”
ዘንድሮ ለማወዳደር፣ ከሀቻምናው የዝናብ መዓት
የዓመቱን ፋንፋር ለሕዝቡ፣ በቴሌቪዥን ለመንፋት! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እኛም ለዓመት ጉድ በቃና፤ …
ከተማው በዶፍ ታጠበ፣ ዝናብ ሳይሆን መዓት ጣለ
ዘቀጠ ተብከለከለ
ቤት ንብረት ተግበሰበሰ፣ ገደል መቀመቅ ተጣለ
መኪናው እንደ አሻንጉሊት፣ ከምድር በላይ ተንጣለለ
ተዋጠ ተጥለቀለቀ፣ ጣራና ፎቅ ግቻ አከለ
ወረደ መዓት ወረደ
ሰማይ ቁልቁል ተቀደደ
እንደ ኦሪት ውሃ ጥፋት፣ አራዳ በማጥ ተናደ
የቤት እንስሳው ንብረቱ፣ ስንቱ አስከሬን ተወሰደ
ከእንጦጦ ፍልውሃ ሜዳ፣ ቄራ እንጦሮጦስ ወረደ
አጠበው ምድሩን ጠረገው፣ ዛፍ ግንዱን እየማገደ
ፎቁን ተሸክሞት ሄደ! …
አቤት ጉድ እየተባለ፣ እንዲያው ብቻ በደፈና
አዲስ አበባ ያለ ዕቅድ፣ ከዓመት ዓመት በጥገና
የዘለቄታ መፍትሔው፣ በአስተማማኝ ሳይጠና
በማዘጋጃ ቤት ዲስኩር፣ የተናደው ፎቅ ላይ ቀና
ለአዲስ ጥናት በአዲስ እቅድ፣ላይ ነን እኮ እየተባለ
ጋዜጣም ምሱን ሸለለ
ቴሌቪዥን ተቀበለ
ሬዲዮም ተንበለበለ
ዘንድሮም ልክ በዓመቱ፣ አዲሳባ ጉድ ተባለ!
ዝነኛው የአቃቂ ውሃም፣ ከጊንፊሌ ጋር ፏለለ
ስንቱን ሰው በልቶ ቤት ነዶ
ለዓመት ምሱ ሕዝቡን ማግዶ
እንደ ቅድመ ታሪክ ዘንዶ
ደሞ ለዓመት ያብቃን ብሎ፣ ተንጐማሎ እየኮራ
እየተወሳለተ ዝናው፣ በጋዜጣ በካሜራ
እያስገመገመ ሄደ፣ እንደሞላ እንደ ተፈራ! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እኛም ለዓመት ጉድ በቃና፤ …
ዝግጁው ማዘጋጃ ቤት፣ ዜና መግለጫ ለማውጋት
ደረሰ ላጋር ቁልቁለት፣ በጋዜጦች አጀብ ብዛት፣
ካሜራ ማን ዙም-ኢን ዙም አውት! ራዲዮ ማይክሮፎንክን አጉላ
ፊንፊኔም ጥማድ ቀበና አቃቂም ድምር ቡልቡላ
የዓመት መዓቱን ወረደ ሞላ ፈላ ሰው ተበላ!
የቀበሌ አዋጅ እምቢልታ
የእሳት አደጋ ኡኡታ
አስከሬን ጠፋ ዕድር ውጡ፣ ዋይታ ጡሩምባ ቱልቱላ
የእግዜር ቁጣ የእግዜር ዱላ! …
እንደ አምልኮ ጣኦት ልማድ፣ እንደ ባሕሎች አሸክላ
ለአዲሳባ ውሃ ግብር፣ የሰው ልጅ እየተቀላ
ክረምት በመጣ ቁጥር፣ ዓማን ዘራፍ ይባላላ! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እንኳን ለዓመት ጉድ በቃና!
ጸጋዬ ገብረ መድኅን

 

Read 3726 times