Saturday, 14 December 2013 01:38

ሚኒባስ ታክሲዎች ኤርፖርት እንዳይገቡ ተከለከሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

• “ታክሲዎች ወደ ውስጥ የማይገቡት አቤቱታ ስለበዛ ነው”

• ከሳውዲ ተመላሾች በታክሲ ላይ ስርቆት ተቸግረዋል ተባለ

ወደ አሮጌው ጉምሩክ እየገቡ ከሳውዲ ተመላሽ ዜጎችን ሲያስተናግዱ የነበሩ ሚኒባስ ታክሲዎች፤ ከስደት ተመላሾች ባቀረቡት አቤቱታ ወደ ውስጥ እንዳይገቡ መታገዳቸው ተገለፀ፡፡ ሚኒባሶቹ ኤርፖርትም ሆነ የድሮው ጉምሩክ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የገለፁት የጉምሩክ ፖሊሶች፤ አንዳንድ የሳኡዲ ተመላሾች በታክሲዎች በሚፈፀሙ ስርቆቶች እንደተቸገሩ አቤቱታ በማቅረባቸው፣ መንግስት የመደባቸው ኮድ 3 ሚኒባሶች ብቻ ገብተው እንዲጭኑ መወሰኑንና ሚኒባስ ታክሲዎቹ ውጭ ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ “ከኤርፖርት አውቶቢስ ተራ” የሚል ታፔላ የለጠፈው የታክሲ ሹፌሩ ዳንኤል ይፍሩ፤ ስራቸውን የሚሰሩት በማህበር ተደራጅተውና በታፔላ በመሆኑ ሌቦችን ለመቆጣጠር አመቺ እንደሆነ ገልፆ፤ ብቻ “ሁሉንም ገብታችሁ አትጫኑ” ተብሎ መከልከሉ ተገቢ እንዳልሆነና ተመላሾችን ለከፋ እንዳሉት የሚያጋልጥ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ሌላው የዚሁ መስመር ሹፌር አድማሱ ሰጠኝ በበኩሉ፤ ከሶስት ቀን በፊት ተሳፋሪ ረስታ የወረደችውን ሻንጣ ለማህበሩ በማስረከብ ለባለቤቷ መሰጠቱን አስታውሶ፤ ከዚህ በፊትም እቃ ጥላ የወረደች የሳኡዲ ተመላሽ ለተቆጣጣሪ የማህበር አባላት ተናግራ፣ በተሳፈረችበት ሰዓት መሰረት ዕቃዋ ተገኝቷል ብሏል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ስራችን በህጉ መሰረት የሚከናወን በመሆኑ ነው ያለው አድማሱ፤ እንደውም ከግቢው ውጪ የሚጭኑ ታክሲዎች ሌብነትን ያስፋፋሉ ብሏል፡፡ ከሳውዲ የተመለሱ ዜጎች በበኩላቸው፤ ታክሲዎች ወደ ውስጥ ባለመግባታቸው ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

Read 1136 times