Saturday, 14 December 2013 10:50

“የኔልሰን ማንዴላን የነፃነት ትግል መርሆዎች የትግል አጋዥ አድርገን እንጠቀምባቸዋለን” ኢዴፓ

Written by  ናፎቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የታላቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህልፈተ ህይወት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፤ የማንዴላን የነፃነት ትግል እንዲሁም የሰብአዊነትና ዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ለፍትሀዊ የትግል ስልት አጋዥ መርህ አድርጐ እንደሚጠቀምባቸው ገለፀ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ፤ በሰላማዊ ትግል አፓርታይድን ታግሎ በማሸነፍ በዘር ከፋፍሎ ሲገዛቸው የነበረውን ሥርዓት አስወግዶ፣ የጥቁር መሪ ፋና ወጊ በመሆን አለምን ማስደመሙንና ህልፈቱም እንዳሳዘነው ፓርቲው በአፅንኦት ገልጿል፡፡

“የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግልና ተጋድሎ ሲታሰብ፤ ከኔልሰን ማንዴላ የህይወት ታሪክ ተለይቶ የሚታይ አይደለም” ያለው ኢዴፓ መግለጫ፤ ታላቁ መሪ ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ የሰላም፣ የአንድነትና የመቻቻል ፖለቲካን የመሰረተ ከመሆኑም በተጨማሪ ጥቁርና ነጭን ያስተሳሰረ ፓርቲና መንግስት በመመስረት፣ አለምን ያስደመመ ታላቅ ታጋይ እንደነበረ አውስቶ፤ በውሻና በአውሬ እያሳደደ በጥይት ይገድላቸው የነበረውን ዘረኛ መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመግታት ብቀላን ያቆመ፣ በአፍሪካ የእርቅ፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህልን የመሰረተ ታላቅ መሪ ነው ሲል ፓርቲው አሞካሽቷል፡፡

ማንዴላ ከነፃነትም በኋላ የተከተላቸው የዴሞክራሲ ምስረታ ሂደቶችና የዜጐች መብት አከባበር መርህ፤ በአለም ላይ ለሚኖሩ መሪዎችና ባለስልጣናት ትልቅ አስተማሪ መሆኑን የገለፀው ኢዴፓ፤ ህዝብን በግድ በመግዛት ሀገር ማስተዳደር የማይቻል መሆኑንም በግልፅ አሳይቷል ብሏል፤ በመግለጫው፡፡ በሚከተላቸው የነፃነት የትግል ጐዳናዎች፣ የማንዴላን የመቻቻል፣ የይቅር ባይነት እና የፅናት መርሆዎች፤ የትግል አጋዥ መርህ አድርጐ እንደሚጠቀምባቸው የጠቆመው ኢዴፓ፤ በኔልሰን ማንዴላ ህልፈተ - ህይወት በጥልቅ ማዘኑን ገልፆ፤ ለመላው የደቡብ አፍሪካ ህዝብ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ተመኝቷል፡፡

Read 1891 times