Saturday, 14 December 2013 10:46

በአቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መልስ እየተጠበቀ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴና ሠላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)
  • ሶስት የኮንስትራክሽን ባለሃብቶችን ጨምሮ 6 ባለሃብቶች ይከሰሳሉ

ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ በሙስና ተጠርጥረው ከሌሎች ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ጋር በቁጥጥር ስር በዋሉትና፣ በሶስት መዝገቦች ክስ በተመሰረተባቸው፣ በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መልስ እየተጠበቀ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ስድስት ከፍተኛ ባለሀብቶች ክስ እንደሚመሰረትባቸው ምንጮች ገልፀዋል፡፡

የአቶ መላኩ ፈንታን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ ህዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ መላኩ በሚኒስትር ማዕረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን ተከትሎ፣ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የየትኛው ፍ/ቤት ነው በሚለው ላይ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት፣ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስር ላለው የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ትእዛዝ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡

ከፍ/ቤቱ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፤ ህዳር 23 ቀን 2006 በመሰብሰብ ጉዳዩን የተመለከተው የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ፤የደረሰበትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን ለፍ/ቤቱ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ከትላንት በስቲያ የዋለው ችሎት፤ አጣሪ ጉባኤው የደረሰበትን ውሳኔ በመመርመር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገመንግስቱ አንቀፅ 83፣ ምክር ቤቱ በ30 ቀን ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት የሚለውን በማስታወስ፤ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በቀጣይ ቀጠሮ ምላሹን ያሳውቅ ብሏል፡፡ መዝገቡንም ለታህሳስ 22 ቀን 2006 ቀጥሯል፡፡

በተያያዘ ዜና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ሶስት ባለሃብቶችን ጨምሮ፣ ከጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣናት ጋር በተያያዘ 6 ባለሃብቶች እንደሚከሰሱ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከሚያስፈልጋቸው በላይ ለህንፃ ግንባታ የሚውል የኮንስትራክሽን ቁሳቁስ ከውጭ አገር እንዲያስገቡ አስፈቅደዋል የተባሉት ባለ ሃብቶች፤ ከቀረጥ ነፃ ያስገቡትን ቁሳቁስ ለሌላ ሰው በመሸጥ፣ አላግባብ ጥቅም አግኝተዋል ተብለው እንደሚከሰሱ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

ከጉምሩክ ሃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ያለ ሙሉ የቀረጥ ክፍያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ወደ አገር ውስጥ አስገብተዋል ከሚለው ሁለተኛ ክስ በተጨማሪ፣ የሌሎች ባለ ሃብቶችን ጉዳይ በማስፈፀም ጥቅም ለማግኘት ከባለስልጣናት ጋር ተደራድረዋል የሚል ክስ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ ካሁን ቀደም በሙስና ወንጀል የተከሰሱና ክስ የተቋረጠላቸው ሰዎች በምስክርነት እንደሚቀርቡም እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

Read 2153 times