Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:17

በአስቸኳይ የሚቋቋመው ገለልተኛ መ/ቤት - “የእውነት ሚኒስቴር” (Ministry of Truth)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለፖለቲከኞችና ለባለስልጣናት “የሐቅ ክኒን” ይዘጋጅላቸዋል
እናንተ … እንደ አበሻ ግን ብረት የሆነ ህዝብ አለ እንዴ? በፍፁም! እውነቴን ነው የምላችሁ የትም አለም ላይ አታገኙም፡፡ እዚህችው ጥንታዊቷ አቢሲኒያ ውስጥ ብቻ ነው የዚህ ዓይነት ድንቅ ህዝብ ያለው፡፡ ለኑሮ ውድነት የማይበገር ብረት ህዝብ - አበሻ! ለነዳጅ ዋጋ መናር እጁን የማይሰጥ ብርቱ ህዝብ - አበሻ! ለግሽበት የማይረታ ጠንካራ ህዝብ- አበሻ! ለዋሾና ሙሰኛ ፖለቲከኞች የማይንበረከክ ድንቅ ህዝብ - አበሻ! ለድርቅና ለረሃብ የማይሸነፍ ኩሩ ህዝብ - አበሻ! በመልካም አስተዳደር እጦትና በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሳያጉረመርም የነገን ብሩህ ቀን በተስፋ የሚጠባበቅ ተስፈኛ ህዝብ - አበሻ! በ11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የዓለም ቁንጮ ሆነሃል ሲባል የማይሞቀው የማይበርደው የተረጋጋ ህዝብ - አበሻ!

የሚያሳዝነው ግን ለዚህ ሁሉ ፅናቱና ብረትነቱ አንድም ጊዜ ለሽልማት አልታጨም፡፡ ኧረ ያሰበውም የለም፡፡ ግን ቢሸለምም ባይሸለምም ግድ የለውም - ብረቱ አበሻ! ለምን ብትሉ … ተፈጥሮው ነዋ! ሰው በህይወት በመኖሩ ብቻ ይሸለማል እንዴ? በፍፁም ግን የአበሻ የብረትነቱ ምስጢር ምን ይሆን?  
ከመጽሐፍ ቅዱሱ ኢዮብ የበለጠ ትዕግስት የተቸረው ህዝብ ስለሆነ ነው አበሻ እንዲህ ብረት የሆነው፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄን ብረትነቱን የሚገዳደር ፈተና ገጥሞታል፡፡ ፓርቲዎች፣ ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎች፣ ምሁራን ወዘተ ይሄን ጠንካራ ባህርዩን እየተፈታተኑት ነው - በውሸት፡፡ በርግጥ በየትኛውም የመንግስት ዘመን ቢሆን ሳይዋሽ የኖረበትን ጊዜ አያስታውስም፡፡ ከዛሬ ነገ ጉዳዩ ይሻሻላል ብሎ ቢጠብቅም እየባሰበት መጣ እንጂ አልተሻለም፡፡ ስለዚህ እውነቴን መልሱ እያለ ነው - በጩኸት ሳይሆን በዝምታ!
የዛሬውን በዓይነቱ ለየት ያለ አስቸኳይ ፕሮፖዛል ያረቀቅኩት የአበሻን ህዝብ እውነት ለማስመለስ ነው፡፡ አዎ አዲሱ ፕሮፖዛል “የእውነት ሚኒስቴር” በአስቸኳይ እንዲቋቋም የሚመክር ነው፡፡ ለምን “የእውነት ሚኒስቴር” መ/ቤት አስፈለገ የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እጠብቃለሁ - በተለይ እውነት ከራቀው የፖለቲካው ጐራ፡፡ ኧረ የሚቆጣም አይጠፋም፡፡ “ውሸታም ናችሁ እያለን ነው” ብለው የሚወነጅሉኝም ይኖራሉ፡፡ እውነት ለመናገር ግን የእውነት ሚ/ር ይቋቋም በማለቴ ብቻ የሚደነፉ ካሉ እነሱ እውነትን ክፉኛ የሚፈሩ ናቸው፡ የሚ/ር መ/ቤቱም የሚቋቋመው እንዲህ ያሉት ወገኖች አገርንና መጪውን ትውልድ በውሸት እንዳይበርዙት ለመከላከልና ለመጠበቅ ነው፡፡ “ውሸት በኛ ይብቃ!” ብለን ሃቀኛ ትውልድ ለመፍጠርም ጭምር ነው መ/ቤቱ የሚቋቋመው፡፡ ባይገርማችሁ ይሄ ፕሮፖዛል ለገዢው ፓርቲ ወይም ደግሞ ለተቃዋሚዎች አሊያም ለዳያስፖራ ታልሞ የተረቀቀ አይደለም፡፡ ለአገር ነው - ለዚህ ብረት ለሆነ ህዝብ - ለአበሻ! አዎ የእውነት ሚ/ር የሚቋቋመው ለኩሩውና ለ”ሁሉን ቻዩ” የአበሻ ህዝብ ነው!!
ይሄን ያነበበ አንድ የገዢው ፓርቲ ካድሬ “ በዚህ አገር ውሸት የለም” በሚል ማስተባበያ የእውነት ሚኒስቴር መቋቋሙ ፋይዳ የለውም ብሎ ሊከራከር ይችላል፡፡ ግን ሙስና እስኪያንገሸግሸን የተበራከተው ለምንድነው? እውነት ስለራቀች እኮ ነው! የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ለምን በዛ? በእውነት እጦት የተነሳ ነው፡ የ97 ምርጫ የፖለቲካ ቀውስ የተከሰተው እኮ እውነት “የለሁበትም” ብላ ባዕድ አገር በመሰደዷ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በምርጫ ውጤት ሲካካዱ እውነት አፍራ “ከደሙ ንፁህ ነኝ” አለችና ተሰወረች፡፡ እስካሁንም ወደ አገሯ አልተመለሰችም፡፡ ዳያስፖራም ሆና ሊሆን ይችላል፡፡ የእውነት ሚኒስቴር ሲቋቋም ግን ወደ አገሯ ትመለሳለች ተብሎ ይታመናል ይላል-ፕሮፖዛሌ፡፡
በነገራችን ላይ የዚህን ፕሮፖዛል መነሻ ሃሳብ ያገኘሁት ከእንግሊዛዊው ፖለቲካዊ ስላቆች ፀሃፊ፣ ከጆርጅ ኦርዌል “1984” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ በደራሲው መጽሐፍ ላይ የእውነት ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የፍቅር ማኒስቴር ወዘተ … የሚሉ መ/ቤቶች ይጠቀሳሉ፡ የእውነት ሚኒስቴር ዋና ስራው ዜናና መረጃ ማቅረብ፣ ማዝናናት፣ ማስተማርና ሥነጥበብን ማስፋፋት ነው (ስላቅ መሆኑን ልብ ይሏል) ከዚህ አንፃር በእኛ አገር የሚኒስቴር መ/ቤቱን ዋና ዋና ሥራዎች በመስራት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ይመስለኛል፡፡ ግን ፕሮፖዛሌ ድርጅቱ የእውነት ሚ/ር ለመሆን መስፈርቱን አያሟላም በሚል የኢቴቪን መ/ቤት ውድቅ አድርጐታል፡፡ ለነገሩ እንኳን የእኔ ፕሮፖዛል ቀርቶ ፖለቲካዊ ልሳን ሆኜ እያገለገልኩት ነው የሚለው ኢህአዴግና መንግስትም ቢሆኑ በእኔ ሃሳብ መቶ በመቶ እንደሚስማሙ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ ወደ ጆርጅ ኦርዌል መፅሃፍ ስመልሳችሁ “የሰላም ሚ/ር” ዋናው ስራው ከጦርነት ጉዳዮች ጋር የተገናኘ ነው፡፡ “የፍቅር ሚ/ር” ደግሞ ህግና ሥርዓት ያስጠብቃል፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳዮች የሚመለከቱት መ/ቤት ስሙ ማን መሰላችሁ? “Ministry of Plenty” ይባላል፡፡
እንደገና ወደ ፕሮፖዛሌ ልውሰዳችሁ፡፡ እስቲ እዚህ ብረት የሆነ ህዝብ ውስጥ የጠፋው ምንድነው ብላችሁ ጠይቁ፡፡ እዚህች ቅድስት አገራችን ላይ መቅኖ የራቀን ለምንድነው? በፓርቲዎች መሃል መነቋቋር ለምን በዛ? መልሱ እውነት በመጥፋቷ ነው የሚል ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስበርስ እንደጠላት የሚፈራረጁት በመሃላቸው የምታስተሳስር ቀጭን የእውነት ክር በመበጠሷ ነው፡፡
በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለተፈጠረው የህዝብ አመጽ ዋና ሰበቡ የኑሮ ውድነት አይደለም የሚለው ፕሮፖዛሌ፤ ዋናው የአመፁ ምክንያት በህዝቡና በመንግስታቸው መካከል የነበረችው ቀጭን የእውነት ገመድ በመበጠሷ ነው ይላል፡፡ የኑሮ ውድነት ከገመዷ መበጠስ በኋላ የመጣ ችግር ነው፡፡ ዋናው ችግር ሳይሆን ችግሩ ያስከተለው ውጤቱ እንደማለት፡፡
ተቃዋሚዎች ዛሬ አሉ ስንል ነገ የሚከስሙብን የአያት የቅድመ አያት እርግማን ስላለባቸው አይደለም፡ ችግራቸው የሐቅ እጥረት (deficiency of truth) ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ንፍቀ ክበቡ ዘወትር በቀውስ የሚናጠው ለምንድነው? እውነት ከፖለቲከኞቻችን መዝገበ ቃላት ላይ ተፍቃ በመውጣቷ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች አያሌ ፖለቲካዊ ደዌዎቻችንን ለመፈወስ ታልሞ ነው የእውነት ሚ/ር በአስቸኳይ እንዲቋቋም የሚመክረው ፕሮፖዛል የተረቀቀው፡፡
ኢህአዴግ 20 ዓመት ሙሉ ተመኝቶ ተመኝቶ እውን ያልሆነለት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመፍጠር ዓላማ ያልተሳካው ለምንድነው? ተቃዋሚዎችና ገዢው ፓርቲ የአንድ አገር ልጆች የማይመስሉት ምን ዓይነት እርግማን ቢወርድብን ነው? ሙስና ከመቀነስ ይልቅ ለምን እየጨመረ መጣ? ለሁሉም ችግሮች መንስኤው የእውነት መጥፋት ነው ይላል - ፕሮፖዛሉ፡፡ ስለዚህ ምን ይሁን? በአስቸኳይ የሚቋቋመው ገለልተኛ መ/ቤት መልስ አለው፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ካድሬዎች፣ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ዜጐች ሁሉ በዓመት አንዴ የሚውጡት የሃቅ ክኒን (Tablet truth) ይዘጋጅላቸዋል ይላል-ፕሮፖዛሉ፡፡ ክኒኑ የሚዘጋጀው ደግሞ አዲስ በሚቋቋመው የእውነት ሚ/ር አማካኝነት ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ ችግሮቻችን መፍትሄ ያገኛሉ የሚለው ፕሮፖዛሌ፤ እውነትም ከስደት ትመለሳለች ብሎ ያምናል፡፡
የዛሬ ወጌን ለማጠናቀቅ አንድ ጥያቄ ላቅርብላችሁ፡፡ አንድ የዓለም መሪ ለመምረጥ ወሳኝ ሰዓት ላይ እንገኛለን ብላችሁ አስቡ፡፡ የእናንተ ድምጽ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ድምጽ ካልሰጣችሁ ምርጫው አይካሄድም፡፡ ለምን ቢባል … በዓለማችን ላይ የሰፈነው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለናንተ ድምጽ ዓለም መሪውን እንዲመርጥ አይፈቅድም፡፡
ለመሪነት የሚወዳደሩት ሦስት እጩዎች ባህርያት እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡ ቀልባችሁ የወደደውን መምረጥ ትችላላችሁ፡፡ ግን አስተውላችሁ፡፡
እጩ - ኤ
ከመሰሪ ፖለቲከኞች ጋር ግንኙነት አለው፤ ኮከብ ቆጣሪዎችን ያማክራል፤ ሁለት ውሽሞች ነበሩት፤ ሲጋራ በላይ በላይ ይለኩሳል፤ በቀን ከ8-10 መለኪያ ማርቲኒ ይጠጣል፡፡
እጩ - ቢ
ሁለት ጊዜ ከሥልጣን ተባሯል፤ እስከ ቀትር ይተኛል፤ የኮሌጅ ተማሪ ሳለ ሃሺሽ ይጠቀም ነበር፤ በየምሽቱ ሩብ (1/4ኛ) ጠርሙስ ውስኪ ይጨልጣል፡፡
እጩ - ሲ
በማዕረግ የተንቆጠቆጠ የጦር ሜዳ ጀግና ነው፡፡ አትክልት በሊታ (Vegetarian) ሲሆን ሲጋራ አያጨስም፡፡ አልፎ አልፎ ነው ቢራ የሚጠጣው፡፡ በሚስቱ ላይ ሄዶ አያውቅም፡፡ እና የትኛውን እጩ መረጣችሁ? ከፈለጋችሁ የእጩዎቹን ባህርያት ደግማችሁ አንብቡት፡፡ ከዚያም በቅጡ አስባችሁ ወስኑ፡፡ ለምን መሰላችሁ? እናንተ የመረጣችሁት (ድምጽ የሰጣችሁት) እጩ 99.9 በመቶ የዓለም መሪ የመሆን ዕድል አለው፡፡ እኔ የምለው በ2002 ዓ.ም በተደረገው አገራዊ ምርጫ ኢህአዴግ በስንት ፐርሰንት ነው ያሸነፈው? (ለሌላ እንዳይመስላችሁ - የታሪክ እውቀቴን ለማበልፀግ ፈልጌ ነው) እስካሁን ከሦስቱ እጩዎች አንዱን እንደመረጣችሁ በመገመት ውጤቱን ይፋ ላድርግላችሁና እንሰነባበት፡፡
እጩ ኤ - የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራንክሊን ዲ. ሩስቬልት
እጩ ቢ- የብሪቲሽ ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርቺል
እጩ ሲ- የጀርመን አምባገነን መሪ የነበረው አዶልፍ ሂትለር
አያችሁ አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ሸዋጅ ጥያቄዎች ለአዕምሮ ጤንነት በጣም አስፈላጊ ናቸው - በሳይንስ ባይረጋገጥም፡፡ ሰናይ ሰንበት!!

 

Read 4350 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:22