Saturday, 14 December 2013 11:02

በሽብር የተከሠሡ የአቶ ጁነዲን ሣዶ ባለቤትና 10 ሰዎች በነፃ ተሠናበቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(19 votes)
  • በአቃቤ ህግ ማስረጃ ቀርቦባቸዋል የተባሉ18 ተከሳሾች መከላከያ እንዲሰሙ ተበይኗል

“ድምፃችን ይሰማ” ከተሰኘው እንቅስቃሴና በአወሊያ ት/ቤት መነሻነት ከተፈጠረው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በ28 ሰዎች ላይ ላይ የቀረበው የሽብር ክስ፣ በዝግ ችሎት የምስክሮች ቃል ሲደመጥ የከረመ ሲሆን፣ ሀሙስ እለት በተሰየመው ችሎት የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድን ጨምሮ 10 ተከሳሾች በነፃ እንዲሠናበቱ፣ 18 ተከሳሾች ደግሞ እንዲከላከሉ ተበየነ፡፡ በክስ መዝገቡ የተካተቱት፣ “አልበር ዴቬሎፕመንት ከኦፕሬሽን አሶሴሽን” እና “ነማኢ የበጐ አድራጐት ማህበር” የተሠኙት ሁለት ድርጀቶችም ከክሱ ነፃ ሆነዋል፡፡ ተከሣሾቹ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለወንጀል አድማ ተስማምተው በህገ መንግስት የተደነገገውን የእምነት ነፃነት ጥሰዋል በማለት ክስ ያቀረበው አቃቤ ህግ፤ ከራሣቸው አክራሪ አስተምህሮ ውጭ ሌላ እምነት እንዳይኖር በማለት የሽብር ተግባር ውስጥ ተሣትፈዋል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት ለማቋቋምም ወደ ተለያዩ የአረብ ሃገራት ሄደው ስልጠና ወስደዋል የሚለው አቃቤ ህግ፣ ተከሣሾቹ አላማቸውን ለማሣካት “የሃይማኖት አስተማሪዎች” እና “የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በሚል ተደራጅተው ተንቀሣቅሰዋል በማለት ማስረጃ ይሆኑኛል ያላቸውን ምስክሮች አቅርቧል፡፡ ፍ/ቤቱ፣ የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ቃላቸው በዝግ ችሎት እንዳደመጠ ገልፆ፣ ከትናንት በስቲያ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል መሃመድ፣ ያሲን ኑሩ፣ ከሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼህ መከተ ሙሄ፣ ሣቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ አቡበከር አለሙ፣ ሙኒር ሁሴን፣ ሼህ ሠኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም ላይ ቀደም ሲል የተመሰረተው ክስ፣ የሽብር ተግባር ፈፅመዋል የሚል እንደነበረ ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፣ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው ማስረጃ ግን “የሽብር ተግባርን ለመፈፀም መዘጋጀትን እና መሞከርን” የሚያሳይ ስለሆነ፣ የተከሰሱበት አንቀፅ እንዲሻሻልና መከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ በይኗል፡፡

ሌሎች አራት ተከሳሾች ማለትም፣ ሙራድ ሽኩር፣ ኑር ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመር እና የሱፍ ጌታቸው ደግሞ፤ በሽብር ተግባር በተለያየ መንገድ ስለመሣተፍ በሚለው አንቀፅ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲከላከሉ ፍ/ቤቱ በይኗል፡፡ የቀድሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የአቶ ጂነዲን ሳዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድን ጨምሮ፣ ሃሠን አሊ፣ ሼህ ሱልጣን ሃጂ፣ ሼህ ጀማል ያሲን፣ ሼህ ጣሂር አብዱልቃድር፣ ሃሠን አቢ ሰኢድ፣ አሊ መኪ፣ ሼክ ሃጂ ኢብራሂም፣ ሼህ አብዱራህማን ኡስማን፣ ዶ/ር ከማል ሃጂ እና ሁለቱ ድርጅቶች በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው ማስረጃ ወንጀል መፈፀማቸውን ስለማያስረዳ መከላከል ሣያስፈልጋቸው በነፃ ይሠናበቱ ሲል ፍ/ቤቱ ብይን ሠጥቷል፡፡

ይከላከሉ የተባሉት ተከሳሾች፤ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ከጥር 22 ጀምሮ ለ5 ቀናት ያቅርቡ ሲል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የሚኒስትሩ የአቶ ጁነዲን ሣዶ ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድ ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ከሣውዲ አረቢያ ኤምባሲ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ፣ ግምቱ ከሃምሣ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚገመት የታሠረ ገንዘብ እና በአረብኛ የተፃፉ መፅሃፍት ይዘው ሲወጡ ተገኙ ተብለው ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ይታወሳል፡፡ ለአንድ አመት ከ5 ወራት ያህልም በማረሚያ ቤት ቆይተዋል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን የባለቤታቸውን በቁጥጥር ስር መዋል በተመለከተ በወቅቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ “ባለቤቴን ባልተሟላ መረጃ ፖሊስ አስሮብኛል” ሲሉ መቃወማቸው ይታወሣል፡፡

Read 3879 times