Saturday, 14 December 2013 11:35

“መድረክ”ሠላማዊ ሠልፍ ተከልክያለሁ፤ አፈናውም በርትቶብኛል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

አመራሩ ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ አስገብተናል ብሏል 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ ባልወጣ ህግ እና የባቡር ፕሮጀክቱን ሠበብ በማድረግ፣ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ያቀዳቸውን ሠላማዊ ሠልፎች እንዳይካሄድ መከልከሉን አስታወቀ፡፡ ፓርቲው፤ የሠላማዊ ተቃውሞን መንገድ መዝጋትና የዜጐችን ህገ-መንግስታዊ መብቶች ማፈን በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡ የመድረኩ አመራሮች በትናንትናው እለት በፓርቲው ፅ/ቤት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ፤ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በኢህአዴግ እየተፈፀሙ ናቸው ያላቸውን ኢ-ሠብአዊና ፀረ ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥሠቶችና ህገ-መንግስቱን የሚፃረሩ ህጎችና አዋጆች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲቀሩ ለመጠየቅ አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ፣ የባቡር ሃዲድ ስራን በማሳበብ መከልከሉን ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ህዳር 8 ቀን 2006 ዓ.ም በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን ግፍ ለመቃወም አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍም “ፀጥታ የሚያስከብር የፖሊስ ሃይል የለኝም” በሚል ሰበብ በመንግስት እንደተከለከለ መድረኩ ገልጿል፡፡ ለ3ኛ ጊዜ ያዘጋጀውና በአገሪቱ አሳሳቢ ናቸው ያላቸውን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመንግስት ለማሳሰብ፣ ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ፣ እውቅና ሰጪው አካል በይፋ ያልወጣና ገና በህትመት ላይ የሆነን ደንብ በመጥቀስ “የጠየቃችሁበት ስፍራ ሰላማዊ ሰልፍ የማይካሄድባቸው ቦታዎች ተብለው የተጠቀሱ በመሆናቸው፣ ለተጠየቀው ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና መስጠት አንችልም” የሚል መልስ እንደሰጠ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

የፓርቲው የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በሰጡት ማብራሪያ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እየታፈነ በመሆኑ፣ ህዝቡ ብሶቱን ማሰማት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ “ሰልፍ በምድር አይቻልም ተብለናል፤ ሰማይ ላይ እናደርግ እንደሆን አናውቅም ያሉት ዶ/ር መረራ፣ በሳውዲ ግፍ ለተፈፀመባቸው ወገኖቻችን እንኳን ብሶታችንን እንዳናሰማ መከልከሉ ኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ግራ እንድንገባ አድርገናል ብለዋል፡፡ የመድረክ አመራር አባል አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው፤ በማይታወቅና ገና ባልፀደቀ ህግ መመሪያ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተው፤ “ይህቺ ሃገር በአሁን ሰዓት በህገ መንግስቱ እየተመራች ነው” ብዬ አላምንም ብለዋል፡፡

መንግስት በነዚህ እርምጃዎቹም ብዙዎችን ከሰላማዊ ትግል እንዲወጡና ወደ ጠመንጃ አማራጭ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ ገ/ማርያም ፤ የሰላማዊ ሰልፉን መከልከል እንዲሁም ሃገሪቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የሚያሳስብ ደብዳቤ ሃሙስ እለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ሰላማዊ ሰልፎቹን ከማገዱም በተጨማሪ የዜጎች እንቅስቃሴ በሙሉ ከራሱ ጋር ብቻ እንዲቆራኝ ለማድረግ 1 ለ 5 የሚባል የስለላ፣የቁጥጥርና የአፈና መዋቅራዊ ወጥመድ መዘርጋቱን የመድረክ አመራሮች ገልፀዋል፡፡ በዚህ መዋቅርም በምርጫ ወቅት የዜጎችን ነፃና ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ መብት ለማፈንና ለመጣስ እንዲሁም የእያንዳንዱን ዜጋ ፖለቲካዊ አቋምና አስተያየት፣ የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን ጭምር ለማፈን እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት “በዚህም ኢህአዴግ የእኛን ድምፅ እያፈነና እንዳንንቀሳቀስ እያደረገ፣ ለራሱ የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳና ዝግጅት ከወዲሁ ጀምሯል” ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ እንዳንቀሳቀስ አድርጎናል ካላችሁ ቀጣዩን ምርጫስ እንዴት ልትወጡት ነው የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው የመድረኩ አመራሮች፤ ምንም እንኳ ጫናው ቢበረታብንም ውስጥ ለውስጥ ስራችንን እየሰራን ነው፤ነገር ግን እንደዚህ ቀደሙ የምርጫው አጃቢዎች ብቻ ሆነን ለመቅረብ አንፈልግም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ፤ የ1ለ5 አደረጃጀት እሳቸው በሚያስተምሩበት ዩኒቨርስቲም መግባቱን አመልክተው፤ ኢህአዴግ አባይ ሣያልቅ ስልጣን አለቅም እያለ ቢሆንም፣ በአንድ ወር ስራ ብቻ በምርጫ ሊሸነፍ የሚችል ፓርቲ ነው ብለዋል።

Read 2492 times