Saturday, 14 December 2013 11:59

“የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

       በፍጥነት ሚሊየነሮች በመፍጠር ‘ድፍን አፍሪካን ቀደምን’ ምናምን ነገር ተባለ አይደል! ይሁና…እንግዲህ ምን ይደረግ! ነገርዬውማ… “ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” ሲባል እንደከረመው ይሄም ‘ማስፈንደቁ’ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አለ አይደል… በብዙ አሥርት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያጡ የነጡ ሰዎች በሞሉባት ሀገር፣ ሽቅብ ከመውጣት ቁልቁል መውረድ እጅግ በጣም በቀለለበት ዘመን…ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሚሊየነር አለ ተብሎ…ዓለም ድንቃ፣ ድንቅ መዝገብ ላይ አስፍሩን አይነት ነገር ቀሺም ነው፡፡ እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሁሉም ነገር ከገንዘብ ጋር እየሆነላችሁ ነው፡፡ ‘ፈረንካ’ ከኦክሲጅንም በበለጠ ‘ለህይወት አስፈላጊ’ የሆነበት አገር እየሆነላችሁ ነው፡፡

ያለ ‘ፈረንካ’ የሚሆን ነገር እየጠፋ ነው፡፡ እኔ የምለው…“ለነፍስ ይሆነኛል…” ምናምን ተብሎ የሚሠራ ነገር ጠፋ ማለት ነው! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ነፍሳችንን ‘ሉሲፈር’ በወለድ አግድ የያዘብን ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ከላይ እስከታች ነገረ ሥራችን ከሉሲፈር ጋር… ‘ውል ባፈርስ ያፍርሰኝ’ አይነት ነገር የተፈራረምን ያስመስልብናላ! እናማ ዘንድሮ…‘የስድሳ አራት ሺህ ብሩ ጥያቄ’ …አለ አይደል… “ምን ያህል ያውቃል?” ሳይሆን “ምን ያህል አለው?” ነው፡፡ ጠቅላላ…ከቤተሰብ ጀምሮ የግንኙነቶች ሁሉ ማስተሳሰሪያ ክሮች ሦስት ብቻ ሆነዋል – ገንዘብ፣ ገንዘብና ገንዘብ ብቻ! ስለ ገንዘብ ፍቅራችን ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ‘አንድ፣ ሁለት ለማለት’ ቡና ቤት ሲገባ አንድ ጓደኛው ብቻውን መጠጥ ይዞ ቆዝሞ ያገኘዋል፡፡ “ፊትህ በጣም ነው የተለዋወጠው፡፡ ምን ሆነሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “እናቴ ሰኔ ላይ ሞተች” ይላል ሰውየው፡፡

“ለሀዘኔ ጊዜ እንዲሆነኝና እሷንም እንዳስታውስበት 10‚000 ዶላር ትታልኝ ነበር፡፡” “አሳዛኝ ነገር ነው፡፡” “ሐምሌ ላይ ደግሞ፣” ሲል ጓደኝየው ቀጠለ፣ “አባቴ አረፈ፡፡ ሆኖም እሱም 50‚000 ዶላር ትቶልኝ ነው ያለፈው፡፡” “በሁለት ወራት ሁለቱንም ወላጆች ማጣት በጣም ከባድ ነው፡፡ ብትቆዝምም አይገርምም፡፡” “ያለፈው ወር ደግሞ አክስቴ አረፈች፡፡ እሷም 15‚000 ዶላር ትታልኝ ነበር፡፡” “ሦስት የቅርብ ዘመዶች በሦስት ወር… በጣም ያሳዝናል!” ይሄን ጊዜ ሰውዬ ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ… “በዚህ ወር ግን ድርቅ ብሏል፡፡ አንድ እንኳን የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” ይኸውላችሁ…ዘመናችን እንዲህ… “የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” አይነት ሊሆን እየተቃረበ ነው። የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ ገንዘብ እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ነገር “ከሌለህ የለህም…” እየሆነ ነው። ሁሉም ነገር “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ…” ነው፡፡ እናላችሁ… ስንት ሚሊየነሮች እንደተፈጠሩ ከምናውቅ ይልቅ ስንቶች ‘ከታች ወደላይ’ ወጡ የሚለውን መስማት እንፈልጋለን፡፡

እንዲህ ‘በቀላሉ’ ሚሊየነር ለመሆን የሚችሉ ካሉ… አለ አይደል… ምነው በቀን ሁለቴ ለመብላት፡ በዓመት አንድ ጨርቅ ለመለወጥ የሚታትሩት እንዳቃታቸው ምክንያቶቹ ቢነገሩን እንመርጣለን፡፡ እነ እንትና…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቀይ የሎተሪ ትኬት እየሸወዳችሁ… “እሰይ፣ እሰይ… እግዜር ይስጥሽ…” እንዳላላችሁ ‘ነገርዬው’ አንደኛውን የቦረና ሠንጋ ዋጋ ሆኖላችሁ አረፈ አይደል! “የፕራይቬታይዜሽን ማመልከቻ ያስገባህ ነው የሚያስመስለው…” ያልከው ወዳጄ… “…ፎር ኤ ላውዚ ፋይቭ–ሚኒትስ!” ካለው ‘ፈረንጅ’ ጋር ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ እንዴ! አይ…ራሱ ‘ፋይቭ’ የተባለውም ‘የፍልሚያ ጊዜ’ አልረዘመም ወይ ብዬ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ… ሚሊየነሮችን በብዛት በማፍራት “አፍሪካን ቀደማችሁ…” የሚሉን አጥኚዎች…‘ስኮች ኦን ዘ ሮክስ’ እየገለበጡ እንዴት እንደሚሳለቁብን አይታያችሁም! (የፈረደበት ፌስቡክ ምናምን ገብታችሁ ስለ እኛና አገራችን የሚቀለዱትን ቀልዶች ብታዩ…የምር ‘ፈረንጆቹ’ ስለ እኛ የሚያስቡትን ታያላችሁ፡፡) እናማ… ወደላይ የወጡትን ሺህ አራት መቶዎችን ብቻ ሳይሆን ወደታች እየወረድን ያለነውን በርካታ ሚሊዮኖች ቁጥር ቢነግሩን አሪፍ ነበር፡፡ እግረ መንገዴን ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙኝማ… ሰውየው ሰባት ልጆች አሉት፡፡ በዚህም በጣም ከመኩራቱ የተነሳ ሚስቱን ሰው በተሰበሰበበት ቦታ እንኳን ሳይቀር… “የሰባት ልጆች እናት!” እያለ ይጠራት ጀመር፡፡

እሷ ደግሞ አጠራሩ ስላልተመቻት ብትቃወመውም ሊተዋት አልቻለም፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን ምሽት ድግስ ተጠርተው አብረው ይሄዳሉ። አንድ ሰዓት ያህል ከቆዩ በኋላ ሰውየውም ደክሞት ወደ ቤት መመለስ ይፈልጋል፡፡ እናላችሁ…ቤቱ ውስጥ ያለው ሰዉ ሁሉ እየሰማ ጮክ ብሎ… “የሰባት ልጆች እናት፣ ቤታችን እንሂድ፣” ይላል። (የትኛውን ነገር የት ቦታ መናገርና አለመናገር እንዳለባቸው ከማያውቁ ሰዎች ይሰውራችሁማ!)” ታዲያላችሁ… የበሸቀችው ሚስት ሆዬ በበኩሏ፤ ጮክ ብላ ሰዉ ሁሉ እየሰማ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “እሺ፣ የአራት ልጆች አባት!” ‘ዓሳ ጎርጓሪ…’ ይላችኋል የዚህ አይነቱ ነው፡፡ አሀ…የማይመለከተውን ሦስቱን ልጆች መጨመር የለበትማ! ቂ…ቂ…ቂ… (ስሙኝማ…በሽወዳ የተወለዱ ልጆች “ቁርጥ አባታቸውን” ይመስላሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ! አይ…አንዳንድ ወዳጆቼን የሚመስሉና ‘ሚስቶቻቸውን የማይመለከቱ’ ልጆች ያየሁ ስለመሰለኝ ነው! ታዲያላችሁ…የገንዘብ ፍቅራችን… አለ አይደል… “የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” አይነት እየሆነ ወዳጅነት ሁሉ ዋናው ‘ክራይቴሪያ’ ጥቅም እየሆነ ነው፡፡ በአንድ ስኒ ሻይና በአንድ ያደረ ቦምቦሊኖ ከተማውን ሲያዞር የሚውል ወዳጅ… አለ አይደል… ‘ድሮ’ ቀርቷል፡፡ ጓደኝነት ማለት ምንቸት አብሽ በአንድ ጭልፋ ሁለትና ሦስት ቦታ አውጥቶ ተካፍሎ መብላት ነበር፡፡ ዘንድሮ ጓደኝነት ማለት የምንቸት አብሽ ስዕል ‘ሼር’ መደራረግ የሆነ ይመስላል… “ስሚ ሼር ያደረኩትን የምንቸት አብሽ ስዕል አየሻት!” አይነት ነገር ነው፡፡

(እንትና ስማኝማ…ምን የመሰለች በቅቤ ያበደች ሹሮ አለች፤ ፌስቡክ ገጽህ ላይ ፖስት አድርጌልለሁ…፡፡ ተዝናናባትማ!) ዘንድሮ በሰንበት ሙዝና ብርቱካን ይዞ ሄዶ የአክስትን ልጅ ‘ላይክ’ ከማድረግ ኮምፒዩተር ፊት ተቀምጦ የጄሎን ፌስቡክ ገጽ ‘ላይክ’ ማድረግ…የስልጣኔ ጣሪያን ‘ቀደን ለመውጣት ስለመድረሳችን’ ማሳያ ሆኗል፡፡ “ገንዘብ ቸግሮኝ ነው፣ አንድ መቶ ብር ታበድርኛለህ…” ብሎ ጥያቄ… አለ አይደል…ገና ኤንጂኦ ያልተቋቋመለት ጎጂ ልማድ ሆኗል፡፡ እናማ…“የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” አይነት ነገር ምን ያህል እንደተጠናወተን የሚያሳብቅብን… ከሰማንያ ምናምን ሚሊዮን ሕዝብ መሀል ሦስት ሺህ የማይሞሉ ሚሊየነሮች አሉ ተብሎ… “መታሰቢያ ቀን ይሰየምላቸው…” አይነት ትርጉም ሊሰጡ የተቃረቡ ዘገባዎች ቀሺም ናቸው፡፡ አንዳንዴ ምን እላለሁ መሰላችሁ…ይሄ ሁሉ ማህበራዊ ችግር እያለ፣ በብዙ ነገር መንገድ ስተን እየሄድን እያለ ምነው እኛ የጨነቀንን ያህል ቦሶቻችንን ‘አይኮነስራቸውም’! ልክ ነዋ… “ምነው ሰዋችን ገረጣ…” ምናምን የሚሉ ሀሳቦች አይገባቸውምሳ! በዛ ሰሞን ከብዙ ዓመታት በኋላ ‘አገር ቤት’ ብቅ ያለች ‘ዳያስፖራ’ ምን አለችን መሰላችሁ…“ሰዉ ጠዋት ፊቱን ታጥቦ የሚያደርቀው በወፍጮ ቤት ጆንያ ነው እንዴ!” ይሄን ያህል ‘ነስንሶብናል’ ነው የምላችሁ! “የሚሞት የቅርብ ዘመድ ልጣ!” ከሚል አይነት ገንዘብ ወዳድነት አንድዬ ይሰውረንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4404 times