Saturday, 21 December 2013 12:17

ጦጢት ለራሷ ሳትገረዝ፣ የሌላውን ዐይን ትይዛለች

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሌባ ወደ አንድ አሮጊት ቤት ገብቶ ሊሰርቅ አካባቢውን በትክክል ለማጥናት ፈልጐ አንዴ በግራ፣ አንዴ በቀኝ፣ ይሄዳል፡፡ አንዴ በፊት ለፊት፣ አንዴ በጓሮ ይዞራል፡፡ በመጨረሻ ማንም እንደሌለና ማንም እንዳላየው ካረጋገጠ በኋላ ወደ ቤት ዘው ይላል፡፡
ዘወር ዘወር ብሎ ሲያይ፤ ጠባብ አፍ ያለው ማሠሮ ውስጥ እህል አለ፡፡ እጁን ወደማሰሮው ሰደደ። የቻለውን ጨብጦ እጁን ለማውጣት ሲሞክር አልወጣም አለው፡፡ ትንቅንቁን ቀጠለ፡፡ የጨበጠውን እህል ሊተው አልፈለገም፡፡ እንደጨበጠ ላውጣህ ቢለው ደግሞ ጠባቡ የእንስራው አፍ አላሳልፍ አለው፡፡ እንዲሁ ሲታገል ይቆያል፡፡
በሌላ በኩል፤ አሮጊቷ ወንዝ ወርዳ ውሃዋን ቀድታ ስትመለስ፤ መንገድ ላይ ያገኘችውን ሰው ሁሉ ሰላም ትላለች፡፡
ለመጀመሪያው፤
“እንዴት ዋላችሁ?” ትላለች፡፡
“ደህና” ይላል ያገኘችው ሰው፡፡
“ሠፈር ደህና?”
“ደህና”
“አዝመራ ደህና?”
“አዬ ዘንድሮስ እንጃ ዝናቡ ደህና አልሰጠም!”
“እንበሶች፣ ላሞች ደህና?”
“አዬ ኧረ እንጃ! በሽታው ከፍቷል“
“ሰዉስ ደህና ነው?”
“አዬ ሰዉስ ድህነቱን አልቻለውም፡፡”
“የእኔ ቤትስ ደህና ነው?”
“ኧረ አላወቅንም - የወጣም ሲገባ አላየን፤ የገባም ሲወጣ አላየን” ይላል ሰውዬው፡፡
“ደህና፤ ሁሉን ለደግ ያርገው ይሄን ዓመት!” ብላ መንገዷን ቀጠለች፡፡
ቤት ስትደርስ፤ ያን ሌባ ሳታስተውል፣ የቀዳችውን የቀርበታ ውሃ አስቀምጣ እፎይ አለች፡፡
ከዚያም፤
“አዬ! ይሄ ገደ - ቢስ ዓመት!” አለች፡፡
ይሄን ጊዜ ያ ሌባ፤
“ገደ - ቢሱን ዓመት ተይውና፤ ነይ የእኔን እጅ ከማሠሮው አውጪልኝ!” አላት፡፡
*   *   *
በተረቱ፤ ስለዓመቱ ማማረር ትተሽ ነይ ይልቅ ሥራ ሥሪ፤ ነው ምፀታዊ ትርጉሙ፡፡ ስላቁ ደግሞ የሰው ቤት እየዘረፈ፣ እንደመልካም ነገር ይሄ ያንቺ እንሥራ የሚያጠፋውን ጥፋት ተመልክተሽ ነይ እጄን አላቂኝ ነው! የእኔን ሌብነት አታስቢው ነው፡፡ እያደር ሙስና ወደ ዐይን አውጣ ሙስና ሲቀየር እንዲህ ፈጣጣ ይሆናል፡፡ “እግሮችህ እንዳይሰረቁብህ መሮጥ የማስፈለጉ ነገር፤ በአሁኑ ጊዜ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል” ይላል ቤርቶልት ብሬሽት፡፡ በሀገራችን ይቆማል፣ ከቀን ቀን ይሻለዋል ሲባል የነበረ በሽታ ዛሬም ያው ሙስና ነው፡፡ ወይ የካንሠሩ ሥር አልታወቀም፣ ወይ ጋንግሪኑን ለመቁረጥ አልተቻለም፡፡
የሌብነት ቦቃ እንደሌለው የሚያስረዱን የጥንቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቲዮዶር ሩዝቬልት፤ “ቢሮ በመስረቅና፣ ቦርሳ በመስረቅ መካከል ልዩነት ፈጥሮ “ጉድ! ጉድ!” ማለት ላይ ባለ አገር! ህዝብ ሙሉ በሙሉ ሰልጥኗል ለማለት አይቻልም” ይሉናል፡፡ በዐቢይ ሌባና በንዑሥ ሌባ መካከል ስናማርጥና ዋናውን ሥረ- ሙስና ሳናገኝ፣ በላይ በላዩ አዳዲስ ሌባ እንደምንጨምርበት ልብ - እንበል፡፡ ነባሩ እየደበዘዘ አሊያም እየተለመደ፤ አዲሱ የወረት ሞሳኝ፤ “ቀንደኛ” ተብሎ ሆይ ሆይ መባሉ፤ ዋናው ደዌ ሥሩ ሳይነቀል እንዲቀር ያደርገዋል!
በሀገራችን፤ በሚገርም ሁኔታ አንዳንዶቹ የሙስና ቧንቧዎች፤ በተለይም ቀጫጭኖቹ ታሽገው፤ ዋናው ቱቦ - አከል ቱባ ቧንቧ ሳይነካ በመቅረቱ፤ “ፈረሱ ከተሰረቀ በኋላ የጋጣውን በር ጥርቅም አድርጐ ዘጋ!” የሚለውን የፈረንጆች ተረት እንኳ በቅጡ ልንተርት እንዳንችል አድርጐናል፡፡ ለምን? ቢባል፤ ማን ጥርቅም አድርጐ ይዝጋው? ነውና ጉዳዩ!
ሼክስፒር፤
“The strongest poison ever known
came from Caesar’s Laurel Crown” ይላል፡፡
“ከቶም ዋንኛው መርዝማ፣ እስከዛሬ እሚታወቀው፣
ቄሣር ካጠለቀው ዘውድ ውስጥ፣ ከወይራ አክሊል የመጣው ነው” እንደማለት ነው፡፡
አናቱን ሳናጣራ እግር - እግሩን ብቻ ብንመነጥር፣ ዞረን እዚያው ክብ ቀለብት፣ እዚያው ክብ ጨዋታ ውስጥ ነው የምንከርመው፡፡ ሙስና የገንዘብና የንብረት ዘረፋ ብቻ እንዳልሆነም አንዘንጋ! የኢፍትሐዊነትና የፖለቲካ ወንጀል ቅይጥ ሙስናም አለና!
አሜሪካዊው ታሪክ ፀሐፊ፤ ዊል ዱራንት፤ እንዲህ ይለናል:-
`ሥልጣኔ ዳርቻ ያለው ወንዝ ነው፡፡ ወንዙ፤ የታሪክ ፀሐፊዎች በመዘገቧቸው አንዳንዴ በነብሰገዳዮች፣ በሌቦች፣ በጯሂ - ሰዎችና በመሳሰሉ፤ ደም የተሞላ ነው፡፡ ልብ መባል ያለበት ግን፤ ከዚህ ወንዝ ዳርቻ ላይ የማይታወቁ ሰዎች አሉ፡፡ ቤት ይሠራሉ፡፡ ፍቅር ይሠራሉ፡፡ ልጆች ያሳድጋሉ። ዘፈን ይዘፍናሉ፡፡ ግጥም ይጽፋሉ፣ እንዲያውም አንዳንዴ ሐውልት ሁሉ ያቆማሉ፡፡ የሥልጣኔ ታሪክ እንግዲህ እባህሩ ዳርቻ ላይ ስለሚሆነው ነገር መሆን ሲገባው፣ ታሪክ ፀሐፊዎች ግን (ተስፋ ቆርጠው ተስፋ እሚያስቆርጡ ሰዎች በመሆናቸው)፤ የባህሩን ዳርቻ ሰዎች ከቁብ ሳይጽፉ ስለ ወንዙ ብቻ ይጽፋሉ፡፡”
አገራችን በኮንትሮባንድ ትተዳደር ይመስል የነጋዴው ትኩረት በስውርና በግልጽ የሚያካሂደው የኮንትሮባንድ ዝውውር መሆኑ ሳያንስ፤ እንደፈረንጆች አባባል፤ ‘ኮንትሮባንድስቶችን የሚያሳድዱት ባለሥልጣኖች ሁሉ ውርሱን መቦጥቦጡን ተያይዘውታል’ ይላል፤ ይባላል”፡፡ ላቲኖች፤ “ዋናው ሌባ፤ ‹ሌባ ያዙ!› እያለ የሚጮኸው ነው ይላሉ” እንደሚባለው ነው፡፡
የእንግሊዙ የፖለቲካ ቀስቃሽና- አማላይ (Lobbyist) ኢያን ግሪር፤ “እንግሊዝ ውስጥ የለንደን ታክሲ እንደምንከራይ ሁሉ የፓርላማ አባልም መከራየት ያስፈልጋል” ይለናል፡፡ (You need to rent an MP just like you rent a London taxi)
ከአናት የመጣ አናት ይመታል፤ ነው ነገሩ! የራሳችንን ዐይን ጉድፍ ሳናወጣ የሌላውን ዓይን እናውጣ ማለት፤ የራሳችንን ፓርቲ ቁስል ሳናክም የሌላውን ቁስል አካሚ መስለን መገኘት፣ የራሳችንን ዓይን ያወጣ ሙስና ሳናይ፣ የሌላው ሙስና ላይ መጮህ፤ “ጦጢት ራሷ ሳትገረዝ፣ የሌላውን ዐይን ትይዛለች” ዓይነት ይሆናልና፤ ልብና ልቦናውን ሰጥቶን ሁሉን በአግባብ የምንይዘበት ጊዜ ያምጣልን! ዕውነተኛ ልደት ለማክበር ያብቃን!!   

Read 6793 times