Saturday, 21 December 2013 12:20

በጉምሩክ የተላኩ እቃዎች እየጠፉ ነው ተባለ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(7 votes)

ሀቢባ ከማል ትባላለች፤ በዱባይ ሀገር ለአስር አመታት ስትኖር አንድም ቀን ወደ አገሯ አልተመለሰችም፡፡ በቅርቡ ግን ሙሉ በሙሉ ጠቅልላ አገሯ ላይ ለመኖርና ጋብቻ ለመመስረት  አስባ ዕቃዎቿን እየሸከፈች ወደ አገሯ መላክ ጀመረች፡፡ ሀቢባ ይጠቅመኛል ያለችውንና በዱባይ ስትገለገልባቸው የነበሩትን ዕቃዎቿን የላከችው በወንድሟ እና በፍቅረኛዋ ስም እንደነበር ገልፃ፤ በፍቅረኛዋ ስም የተላከው እቃ ቢደርስም በወንድሟ ስም የተላከው እቃ አዲስ አበባ እንደገባ ተደውሎ ከተነገራት በኋላ “ጠፍቷል” መባሉን ትናገራለች፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ችግሩን ጉምሩክ ለኃላፊዎች መንገሯን የምትግልፀው ሃቢባ፤ መፍትሄ ግን አላገኘሁም ትላለች፡፡ እቃዎቹ መዋቢያዎችና በቀላሉ የሚበላሹ መገልገያዎች እንደሆኑ ገልፃ፤ የጠፉትን ንብረቶች ለማሟላትም ከዚህ አገር እየገዛች መሆኑንና ለኪሳራ መዳረጓን ትናገራለች፡፡
ሌላዋ ቅሬታ አቅራቢ ትዕግስት ሀለፎም በበኩሏ፤ ለአባታቸው የደም መለኪያና መድሃኒቶችን እህቷ በጉምሩክ በኩል እንደላከችላት ገልፃ፤ እቃው ደርሷል ተብላ ከተጠራች በኋላ ግን ማግኘት አለመቻሏንና ለስምንት ወራት መመላለሷን ትናገራለች፡፡ ጉዳዩን ለጉምሩክ ሃላፊዎች መናገሯንም ጠቅሳ፤ በካሜራ ስለሚታይ ምንም ዕቃ እንደማይጠፋና ማንም ሰራተኛ እንደማይነካ እንደተገለፀላትና እስካሁን ግን እቃዋን እንዳላገኘች ተናግራለች፡፡
ከእቃዎች መጥፋት በተጨማሪ ያለ አግባብ ቀረጥ እንደሚጫንባቸውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡ ለስምንት አመታት በባህሬን ስትገለገልባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን ይዛ የመጣችው ሙሉ በሙሉ አገሯ ላይ ለመኖር በማሰብ እንደሆነ የተናገረችው አሰለፈች አማረ፤ ላመጣኋቸው እቃዎች 41 ሺህ ብር ቀረጥ ክፈይ ስባል ደነገጥኩ ትላለች፡፡ ምክንያቱን ስጠይቅ የሚያስረዳኝ አላገኘሁም ያለችው አሰለፈች፤ “እቃውን የገዛሁበት ዋጋ ቢደመር የዚህን ያህል አያወጣም፤ ስለዚህ ውሰዱት” ብዬ ትቼላቸዋለሁ ብላለች፡፡ ባለፈው ሰኞ ችግሮቻቸው እንደሚፈቱ እና ካሜራ ስለተገጠመ ምንም ዓይነት ስርቆት እንደማይካሄድ በጉምሩክ ሃላፊዎች እንደተገለፀላቸው የተናገሩት ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ እስካሁን ግን እቃቸውን እንዳልተረከቡ ጠቁመዋል፡፡

Read 3361 times