Print this page
Monday, 23 December 2013 09:22

የ2013 የአለማችን ሃያላን ጥቁር ሴቶች ከአስራ አንዱ ሃያላን ሴቶች ሶስቱ አፍሪካውያን ናቸው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በተሰማሩበት መስክ ጉልህ ስራ ሰርተዋል፣ የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል፣ ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርገዋል፣ ሃያልነታቸውንም አስመስክረዋል ያላቸውን የአለማችን ሴቶች በየአመቱ የሚመርጠው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም የ2013ን የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ በመላ አለም ከሚገኙ የተለያዩ አገራት ከመረጣቸው 100 የአመቱ ሃያላን ሴቶች መካከል፣ የቀለም ልዩነት ሳይበግራቸው ጉልህ ስራ ሰርተዋል፣ የጥቁር ሴቶች የስኬታማነት ተምሳሌት ሆነዋል ብሎ በዝርዝሩ ውስጥ ያካተታቸው ጥቁር ሴቶች አስራ አንድ ብቻ ናቸው፡፡ ከአስራ አንዱ ጥቁር ሃያላን ሴቶች መካከልም፣ ከአፍሪካ አህጉር የተመረጡት ሶስት ብቻ ናቸው፡፡
ፖለቲከኞችን፣ የኩባንያ ስራ አስኪያጆችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎችን፣ የመንግስት ባለስልጣናትንና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ሴቶችን የያዘው የፎርብስ የአመቱ ምርጥ ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ከጥቁር ሴቶች መካከል በቀዳሚነት ያስቀመጠው ቀዳማዊ እመቤት ሚሼል ኦባማን ነው፡፡
ፎርብስ ሚሼል ኦባማን የመረጠው፣ በቀዳማዊ እመቤትነቷ በመጠቀም ህጻናትን ከመጠን በላይ ከሆነ ክብደት ለመታደግና ጤናማ አኗኗርና አመጋገብን ለማስፋፋት በምታደርገው ጥረት ነው፡፡ ሚሼል ከባራክ ኦባማ ጋር ሲነጻጸር በአሜሪካውያን ዘንድ የበለጠ ተወዳጅነት እንዳላቸው የገለጸው የፎርብስ መረጃ፣ ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ 67 በመቶ የሚሆነው ከባራክ ኦባማ ይልቅ ለሚሼል ጥሩ አመለካከት እንዳለው ያሳያል፡፡
በሃያላኑ ጥቁር ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው ሌላዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ደግሞ ኦፕራ ዊንፍሬይ ናት፡፡ ለ25 አመታት ስትመራው በነበረው ኦፕራ ሾው የተባለ ፕሮግራም አለማቀፍ ዝናን ያተረፈችው ኦፕራ፣ በሃብት መጠን ቀዳሚዋ አፍሪካ አሜሪካዊት መሆኗንም ፎርብስ ጠቅሷል፡፡ አዲስ ያቀዋቀዋመችው ዘ ኦፕራ ዊንፍሬይ ኔትዎርክ የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፈው አመት ብቻ 83 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ተመልካች ቤተሰቦችን ለማግኘት በቅቷል። ኦፕራ በበጎ አድራጎት ስራ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠራ የአለማችን ለጋስ ሴቶች አንዷ ስትሆን፣ እስከ አሁን ድረስ ከ400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ስራ አበርክታለች፡፡
የዜሮክስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነችው አሜሪካዊቷ ኡርሱላ በርንስ፣ ኩባንያውን ከማተሚያ መሳሪያ አምራችነት፣ ጠቅላላ አገልግሎቶችን ወደሚሰጥ ግዙፍ ኩባንያነት አሳድጋለች በሚል ነው በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 በተለማማጅ ሰራተኛነት ዜሮክስ ኩባንያን የተቀላቀለችው ኡርሱላ በርንስ፣ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን መመረቋን ተከትሎ በቀጣዩ አመት የኩባንያው መደበኛ ሰራተኛ ሆና ተቀጥራለች። በስራዋ ውጤታማ በመሆኗ እ.ኤ.አ በ2000 የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርጋ ተሹማለች፡፡ ይህቺው ታታሪ ሰራተኛ እ.ኤ.አ በ2009 የዜሮክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሆነች በኋላም፣ የበለጠ ውጤታማ ስራ በማከናወኗና ኩባንያውን ወደተሻለ ትርፋማነት በማሸጋገሯ ነው፣ ፎርብስ ከሃያላኑ ጎራ የቀላቀላት፡፡
ሌላዋ የፎርብስ የአመቱ ሀያል ሴት አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ ናት፡፡ ፎርብስ እንዳለው፣ ቢዮንሴ በሙዚቃ ስራዎቿ ከምታገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ በተጨማሪ፣ ሀውስ ኦፍ ዴሪዮን በሚል ስያሜ ባቋቋመችው የአልባሳት አምራች ኩባንያዋም ከፍተኛ ትርፍ ማካበቷን ቀጥላለች፡፡
ከፔፕሲ ጋር የፈጸመችው የማስታወቂያና የኮንሰርት ስምምነት 50 ሚሊዮን ዶላር ያሳፈሳት ቢዮንሴ፣ የምንጊዜም ምርጥ ሽያጭ ካስመዘገቡ የአለማችን ታዋቂ ድምጻውያን ተርታ የምትመደብ ሲሆን 17 የግራሚ ሽልማቶችንም ተቀብላለች፡፡ ከወራት በፊት በተዘጋጀ የሱፐር ቦውል የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ያቀረበችው የ15 ደቂቃ ሙዚቃዋን በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ104 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች እንደተመለከቱት የሚጠቅሰው የፎርብስ መረጃ፣ ድምጻዊቷ በአለም ዙሪያ ያላትን ተቀባይነት የበለጠ እያሳደገች መምጣቷ በሃያልነት እንዳስመረጣት ይናገራል፡፡
የታዋቂው ዎልማርት ኩባንያና ከአሜሪካ ታላላቅ የንግድ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የሳምስ ክለብ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን የሰራችው ሮዛሊንድ ብሪዌርም ሌላዋ የፎርብስ የአመቱ ሀያል ጥቁር ሴት ናት፡፡ ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የሳምስ መሪ ሆና የተመረጠችው ብሪዌር፣ ለኩባንያው ትርፋማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ይነገራል። እ.ኤ.አ በ2006 ዎልማርትን በመቀላቀል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና ያከናወነቻቸው ስራዎቿ ኩባንያውን ማሳደግ፣ የእሷን ጥንካሬም ማስመስከር የቻሉ በመሆናቸው በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ መካተቷን ፎርብስ ተናግሯል፡፡
አፍሪካን የጥቁር ሃያላን ሴቶች እናት አድርገው ካስጠቀሷት ሶስት የአመቱ የፎርብስ ሃያላን ሴቶች መካከል፣ የማላዊ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ አንዷ ናት። የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን ወደ መሪነት የመጣችው ጆይስ ባንዳ፣ የመጀመሪያዎቹን የስልጣን አመታት ከአለማቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ በማሰባሰብና አገሪቱን ከሚፈታተናት የዋጋ ግሽበት ጋር በመታገል ነበር ያሳለፈቻቸው፡፡
ጆይስ ባንዳ ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢዋ 40 በመቶ ያህሉን ከውጭ እርዳታ የምታገኘውን ይህቺን ድሃ አፍሪካዊት ሀገር ከገንዘብ ዕጦት ለመታደግ፣ በአለም ዙሪያ እየተንቀሳቀሰች የገንዘብ ተቋማትን በማሳመን ስራ ተጠምዳ እንደኖረች ፎርብስ ተናግሯል፡፡ ባንዳ ያለፉት መንግስታት አያደርጉ አድርገዋት የሄዷትን ማላዊ እንድታገግምና ራሷን ችላ እንድትቆም ለማስቻል እያደረገችው የምትገኘው ተጠቃሽ ጥረት የፎርብስን ሚዛን በመድፋቱ ከሃያላኑ ጎራ ተቀላቅላለች፡፡
የአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንትና እ.ኤ.አ የ2011 የኖቬል የሰላም ተሸላሚዋ ሊይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የአፍሪካን ሴቶች ሃያልነት ያስመሰከረች ሌላኛዋ የፎርብስ ምርጥ ናት። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርቷን የተከታተለችው ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የላይቤሪያን የእርስ በርስ ግጭት በሰላማዊ ድርድርና መግባባት ለመቋጨት ከመቻሏ በተጨማሪ፣ አለማቀፍ አበዳሪዎች የዕዳ ስረዛ እንዲያደርጉ በማግባባት ረገድ የሰራቻቸው ስራዎችም ጠንካራና ስኬታማ ሴትነቷን ያስመሰክራሉ ብሏል ፎርብስ፡፡
ፎርብስ የአመቱ ሃያል ሴት ብሎ የጠቀሳት ሌላዋ አፍሪካዊት፣ የናይጀሪያ የፋይናንስ ሚንስትርና የኢኮኖሚ አስተባባሪ ሚንስትር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ናት፡፡ ኢዌላ በአለም ባንክ የነበራትን የማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ስራ ለቅቃ፣ እ.ኤ.አ ከ2011 በሚንስትርነት ከተሸመች በኋላ ተጠቃሽ ስራ መስራቷን የጠቀሰው የፎርብስ መረጃ፣ በቀጣዩ አመት የአገሪቱ ኢኮኖሚ 6.5 በመቶ እድገት እንዲያሳይ የእሷ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2006 በአገሯ ናይጀሪያ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆና ትሰራ የነበረው ኢዌላ፣ አበዳሪዎች የናይጀሪያን 18 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንዲሰርዙ በማስቻል ረገድ ተጠቃሽ ስራ መስራቷ ይነገራል፡፡
ከፎርብስ የአመቱ ሃያላን ጥቁር ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችዋ ሌላኛዋ ትጉህ ደግሞ፣ እ.ኤ.አ በ2012 የአለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሆና የተመረጠችው አሜሪካዊቷ ኤርታሪን ኮሲን ናት።
ድርጅቱ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 78 የተለያዩ አገራት ከርሃብ፣ የምግብ ዋስትናና የምግብ እጥረት ጋር  በተያያዘ የሚሰራውን ሰፊ ስራ በአግባቡ የመምራትና በስሯ የሚገኙ ከ15ሺህ በላይ ሰራተኞችን በወጉ የማስተዳደር ታላቅ ሃላፊነት የተጣለባት ኮሲን፣ ውጤታማ ስራ ማከናወኗን ፎርብስ ይመሰክራል፡፡ የመጀመሪያውን አመት በምዕራብ አፍሪካ በድርቅ፣ በሶሪያ ደግሞ በእርስበርስ ጦርነት ሳቢያ የተከሰተውን ርሃብ ለማሰወገድ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ያሳለፈችው ኮሲን፣ በቀጣይም ከምግብ እርዳታ ወደ ራስን ማስቻል የሚደረገውን ሽግግር በመምራት ተጠቃሽ ስራ ማከናወኗን ፎርብስ ዘግቧል፡፡
በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ ለመቀላቀል የቻለችው ሌላዋ አሜሪካዊት፣ የኬር ዩኤስኤ ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሄለን ጋይሌ ናት፡፡ እ.ኤ.አ በ2006  የኬር ዩኤስኤ ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና የተሸመችው ሄለን፣ በ87 የአለም አገራት ድህነትን ለመዋጋት የሚከናወኑ ስራዎችን በአግባቡ መምራቷ ይነገርላታል፡፡
በቻድ፣ ኒጀር፣ ማላዊና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከ750 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ የምግብና የንጹህ የውሃ መጠጥ አቅርቦት ስራዎችን አከናውናለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 ሮበርት ውድ ጆንሰን ፋውንዴሽን የተባለው የአሜሪካ ትልቁ የጤና ክብካቤ ተቋም ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና የተመረጠችው ሪዛ ላቪዞ ሙርኒ፣ ሌላኛዋ የፎርብስ የአመቱ ሃያል ጥቁር ሴት ናት፡፡ ፋውንዴሽኑን ለአመታት በስኬታማነት መምራቷ የሚነገርላት ሙርኒ፣ ተቋሙን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት እንዲሁም የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊ ናት፡፡

Read 8037 times
Administrator

Latest from Administrator