Saturday, 03 December 2011 08:30

የዳንኤል ክብረት ምልከታ እና የአለቃ ገብረሐና ህልውና

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(2 votes)

ጥናቱ፣ ፎክሎርን ተጠቅሞ ከልደት እስከ ሞት ያለውን ያለቃን ሕይወት ዘክሯል
“የብዙዎቹ ኢትዮጵያዊያን ታላላቅ ሰዎች ጥፋት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ነው…”
“አዲስ አበባ እንኳ ለስንቱ የመንገድ ስም ስትሠጥ ለእርሳቸው ነፍጋቸዋለች”

ፈር መያዣ - ከሁለት ሣምንት በፊት በሚዩዚክ ሜይዴይ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ለውይይት ቀርቦ ነበር፡፡ “አለቃ ገብረሃና ተረት ናቸው እውነት?” የሚለውን የመወያያ ጽሑፍ ያቀረበው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሲሆን፣ በአዳራሹ ብዙ ታዳሚ ተገኝቶ ሞቅ ያለ ውይይት መደረጉ ይታወቃል፡፡
በቃላዊው ታሪክ ላይ ተመስርቶ ከትውልድ ትውልድ እንደ ጅረት የሚፈሰው የአለቃ ገብረሃና ሕይወት፣ በብዙዎች ኢትዮጵያዊያን ተረቶች ዘንድ አፍ ማሟሻ በመሆኑ፣ አለቃ ምናባዊ የተረት ገፀባህሪ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ እንደ ዳንኤል ክብረት ባሉ አርቆ አስተዋይ፣ አንብቦ አደር ሰው እጅ ሲገቡ ደግሞ፣ ሕያውነታቸው ብቻ አይደለም የሚዘከረው፤ በተለያዩ መረጃዎችና ማስረጃዎች ገቢራዊነታቸውም ይፀናል፡፡

ከቃላዊው ሀብት ውስጥ፣ በየጊዜው እየተለዋወጠ ከሚቀነቀነው ሰብዕናቸውና ገድላቸው ስር የደፈረሰው ስርክርክ ታሪካቸውን በብልሃት እያጠነፈፉ በማስረጃ ማስደገፍ ይገባል፡፡ ያለ ማስረጃ የሚነበነቡ ያለአዋቂዎች ዝርክርክ ታሪኮችንም በወጉ መመርመር ተገቢ ነው፤ የፎክሉር ሳይንስም ይህንን ይጠይቃል፡ ማስረጃዎችን ዋቢ እያደረጉ እንደ አለቃ ያሉ ዘመናቸውን የቀደሙ ሊቃውንትን የዛሬውን ትውልድ በሚያነቃ መንገድ ለመዘከር የሚተጉ ብልሆች ናቸው፤ ዳንኤል ክብረትም፣ በሰከነ መንፈስ ይህንኑ አካያሄድ ነው የተከተለው፡፡ 
“አለቃ ገብረሃና ተረት ናቸው እውነት?” የሚለውን ጥናታዊ ጽሑፍ በዳንኤል ብሎግ (“ጡማር”) ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ የአለቃ ገብረሃና ታሪክ፣ በ”የዳንኤል ዕይታዎች” ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የቀረበ ይመስለኛል፡፡ ዳንኤል በፈጠረው መነቃቃትና ትጋት፣ የአለቃን ሕይወት የሚዘክረውን ጥናት በወፍ በረር ለመቃኘት መሞከር የዚህ መጣጥፍ ዋና አላማ ነው፡፡
የጥናቱ ወፍ በረራዊ ቅኝት - ከዳንኤል ጥናት ሁለት አብይ ክፍሎችን ማውጣት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ክፍል፣ የጥናቱ ርዕስ የሆነው፣ “አለቃ ገብረሐና ተረት ናቸው እውነት?” የሚለው ነው፡ በዚህ ክፍል፣ “ታሪክ” በሚል “የጥናቱ መግቢያ” መሰል ንዑስ ርዕስ ሥር፣ የአለቃ የሕይወት ታሪክ ተጨምቆ ቀርቧል፡፡ እኛም፣ ከታላቁ ሊቅ ጋር ለመተዋወቅ እንዲረዳን፣ ታሪካቸውን የበለጠ ጨምቀን እንደሚከተለው ለማቅረብ እንሞክር፡፡
“የአባታቸው ስም አንዳንዶች ደስታ ተገኝ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ገብረማርያም ነው ይላሉ” በማለት፣ ጥናቱ “በምናልባት” አንዱ ዓለማዊ ሌላው የክርስትና ስማቸው ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ እናታቸው ደግሞ፣ “መልካሜ ለማ” እንደሚባሉ የጽሑፍ ማስረጃ ተጣቅሷል፡፡ በታህሳስ 10፣ 1978 እትሙ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የእናታቸውን ስም “ሣህሊቱ ተክሌ” እንደሚለው ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ የዳንኤል ጥናት ባይጠቁመንም ተጨማሪ ጥናት ሊደረግ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠት የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡
አለቃ የተወለዱት ከዛሬ 190 ዓመት በፊት በዚሁ ወር (ማለቴ በህዳር) በ1814 ዓ.ም ነበር፡፡ የትውልድ ቦታቸውም በዛሬው ክለላ በደቡብ ጐንደር ዞን፣ በፎገራ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ናበጋ ጊዮርጊስ አካባቢ እንደነበረ ተገልጿል፡፡
በትውልድ መንደራቸው ትምህርታቸውን “ሀ” ያሉት አለቃ፣ ቅኔ ለመማር ወደ ጐጃም ዘልቀው እንደነበር ይነገራል፤ “ከዚያም ጐንደር ከተማ ተመልሰው ከመምህር ወልደ አብ ወልደማርያም ፀዋትወ ዜማ፣ ከባሕታዊ ገብረ አምላክ አቋቋም፣ ከዐቃቤ ስብሐት ገብረ መድኅን ትርጓሜ መፃሕፍትን እንዲሁም ድጓን” እንደተማሩ ጥናቱ ዘርዝሯል፡፡
አለቃ ገብረሐና ቀልደኝነታቸው ከልጅነታቸው የጀመረ ይመስላል፡፡ ብዙ ሊቃውንትን ያፈሩት የአለቃ ገብረሐና አስተማሪ መምህር ወልደአብ፣ የቦሩ ሜዳውን፣ መምህር አካለ ወልድን “አንተ በውቀት ተጠራ” ሲሏቸው፣ አለቃን ደግሞ፣ “አንተ በቀልድህ…” እንዳሏቸው በፎክሎራዊ ጥናት የተገኘ የሚመስል መረጃ ቀርቧል፡፡
አለቃ ገብረሐና በሊቅነታቸው የተነሳ በ26 ዓመታቸው ጐንደር ላይ በሊቀ ካህንነት ተሹመው እንደነበር፣ በሹመታቸው 7 ዓመታት ስለማገልገላቸው፣ በፍትሐ ነገስት ሊቅነታቸው የተነሳ በዳኝነት ይሰየሙ እንደነበር፣ ቀልድ አዋቂነታቸው ገኖ መውጣት የጀመረው በዚህ ጊዜ እንደነበር፣ በቀልድ አዋቂነታቸው የተነሳም የትንሹ ራስ አሊ አጫዋች እንደነበሩ፣ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር በቤተመንግስት ሲገናኙ፣ አፄው፣ “ገብረሐና ፍትሐ ነገስቱን ፃፍ፣ ፍርድ ስጥ፣ ገንዘብም ያውልህ፣ ቀልድህን ግን ተወኝ” ብለው እንደተናገሯቸው፣ ከአንቶኒዮ ዲ አባዲ ጋር ደብዳቤ ይፃፃፍ የነበረው የዋድላዋ ደብተራ አሰጋኸኝ ጥር 6 ቀን 1858 ዓ.ም፣ “አለቃ ገብረሐናን ንጉሱ መቱዋቸው፣ በሽመል፡፡ ወደ ትግሬ፣ ወደ ላስታ ተሰደዱ፡፡ እጅግ ተዋረዱ…” የሚል ደብዳቤ ስለመፃፉ ጥናቱ አትቷል፡፡
አለቃ ገብረሐና “ቀለድህን ተወኝ” ሲባሉ ባለማረፋቸው ሳቢያ በአፄ ቴዎድሮስ መደብደባቸው የሚጠበቅ ይመስላል፤” በመጀመሪያ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር የተጋጩት ቴዎድሮስ ለአንድ ቤተክርስቲያን ሁለት ካህንን እና ሦስት ዲያቆን ይበቃል ያሉትን ሐሳብ ባለመቀበላቸው ነው፡፡ የመሰላቸውን ሀሳብ ለዛ ባለው አነጋገር የሚገልጡት አለቃ፤ ዐፄ ቴዎድሮስ የደብረታቦርን መድኃኔዓለም አሠርተው አስተያየት ቢጠይቋቸው የቤተክርስቲያኑን ጠባብነት ለመግለጥ ለሁለት ቀሳውስትና ለሦስት ዲያቆናት መቼ አነሰ” ብለው መናገራቸው ይወሳል፡፡
አለቃ ለንጉሱ ባለሟልም አላረፉም፡፡ ብላታ አድጐን “አድግ” እያሉ በማሸሞር የሚፈጥሩትን አንባ ጓሮ መዳኘት፣ አፄ ቴዎድሮስን ሰልችቷቸው ነበር (“አድግ የሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን “አህያ” የሚል ትርጉም እንዳለው ተጠቁሟል)አንድ ቀን ግን ቴዎድሮስ መላ ዘየዱ፤ ሁለቱን ትግል በማጋጠም የተሸነፈ አርፎ ይቀመጣል በሚል፡፡ “በዚህ ትግልም አለቃ ተሸነፉ፡፡ ንጉሡም እንግዲህ ምን ይበጅህ? ሲሉ ቢጠይቋቸው” አለቃ ፈጣንና ሸርዳጅ መልስ ነበር የሰጡት፤ “ድሮስ ትግል ያህያ ሥራ አይደል” በማለት፡፡ ቴውድሮስ ይህን ሲሰሙ አለቃ ለራሳቸውም እንደማይመለሱ ስለገባቸው፣ ለትግራዩ ጨለቆ ስላሴ አለቃ አድርገው በመሾም ከፊታቸው ዘወር እንዲሉ ማድረጋቸውን ዳንኤል በጥናቱ አውስቷል፡፡
አለቃ ገብረሐና በአፄ ቴዎድሮስ ላይ ካመፁ ካህናት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ አፄ ቴዋድሮስ አይቀጡ ቅጣት ሊቀጧቸው መዛታቸውን የሰሙት ገብረሐና፤ ወደ ጣና ሐይቅ ሬማ መድሐኔዓለም ገዳም ተሰደዱ፡ በዚህ ገዳምም፣ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ ከተባሉ የአቋቋም ሊቅ ጋር ሆነው፤ “በጐንደር አቋቋም ስልት የመቋሚያውን የአካል እንቅስቃሴ ጨምረው ዝማሜውን አዘጋጁት” አለቃም የአፄ ቴዎድሮስን መሞት ከሰሙ በኋላ፣ በ1864 ዓ.ም ዐፄ ዮሐንስ ሲነግሱ ወደ ትግራይ እንዳቀኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡
አለቃ ገብረሐና በአፄ ዮሐንስ አደባባይ ፍትሐ ነገስት ይተረጉሙ እንደነበር፣ በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ አንዳንድ የብራና መፃሕፍት ላይ ስማቸው ሰፍሮ ስለመገኘቱ፣ አፄ ዮሐንስ ሲሞቱ ወደ ናበጋ ጊዮርጊስ እንደተመለሱ፣ ንጉሥ ምኒልክ የእንጦጦ ራጉኤል የአቋቋም መምህር እንዳደረጓቸው፣ ወደ ጐንደር ሄደው የቁላላ ሚካኤሏን ወ/ሮ ማዘንጊያን እንዳገቡና አለቃ ተክሌን፣ በፍታን (ጥሩነሽን) እና ስኑን እንደወለዱ፣ ፎቶ መነሳት የሰይጣን ሥራ ነው በሚባልበት በዛ ዘመን ከአፄ ምኒሊክ ጋር ፎቶ እንደተነሱ፣ “ጠላቶቻችሁን አፍቅሩ የምትል አንተ ታድያ ኃጥአንን ለምን በገሃነም ትቀጣለህ” እያሉ ፈጣሪያቸውን በግዕዝ ቅኔ እስከ መሞገት የደረሱ የዘመኑ ፈላስፋ እንደነበሩ፣ በአፄ ምኒልክ ቤተመንግስትም በተለይ ከደጃች ባልቻና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር አንባጓሮ በመፍጠራቸው ከአዲስ አበባ እንዲወጡ እንደተደረጉ ወዘተ. ተብራርቷል፡፡
በኋላም ወደ ትውልድ ቦታቸው ናበጋ ጊዮርጊስ እንደተመለሱና ቅዱሳት መፃሕፍትን ሰብስበው መሳለቂያ፣ መዘባበቻ ስለማድረጋቸው ይቅርታ እንደጠየቁ ሁሉ ጥናቱ ያስረዳል፡፡ “ታሪክ” የሚለው የጥናቱ ንዑስ ክፍል በመጨረሻ፣ በ84 ዓመታቸው የካቲት 24 ቀን 1898 እንዳረፉ ይጠቁማል፡፡
ጥናቱ አለቃ ገብረሃና ተረት ሣይሆኑ በእውን የነበሩ ታላቅ ሊቅ መሆናቸውን ለማጽናት፣ በ6 አጫጭር ንዑስ ክፍሎች 1ኛ. የትውልድ ሀረጋቸውን፣ 2ኛ. የትውልድ አካባቢያቸውን፣ 3ኛ. ቅርሶቻቸውን፣ 4ኛ. ዘመነኛ ምስክሮቻቸውን፣ 5ኛ. “የትምህርት ቤት የዘር ሐረጋቸውን” እና 6ኛ. ፎቶዎቻቸውን ዋቢ አድርጐ ለማስተንተን ሞክሯል፡፡
“የአለቃ ቀልደኝነት ከየት መጣ?” በሚለው ንዑስ ክፍል፣ አጥኒው ዳንኤል የራሡን መላምት እንደሚከተለው ጠቁሟል፤ “… የተሟላ መልስ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ በአንድ በኩል የደብተራ ዘነብ፣ የአለቃ ገብረሐና፣ የዲማው ካሣ ጉዱ በአንድ ተመሣሣይ ዘመን መገኘት፣ ያ ዘመን ሊቃውንቱ በአዲስ መሥመር /አፈንግጦሽ/ የተጓዙበት ዘመን ይሆን? ያሰኘናል፡፡ ደብተራ ዘነበ ያዘጋጁት “መጽሐፈ ጨዋታ” ቅኔውን እንዴት አድርገው እያዋዛ በሚያስረዳ አገላለጥ እንደተጠቀሙበት፣ አለቃ ለማ ኃይሉ ሕልውናውን የመሰከሩለት፣ በኋላም ታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ በ”ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፋቸው የኪነጥበብን መልክ ቀብተው ያቀረቡት ጉዱ ካሣ፤ ቅኔውን ሥርአቱን ለመተቸት እንዴት እንዳዋለው ስናጤን እነዚህ ሰዎች የጎጃምን ቅኔ ሲቀምሱ ማን? ምን? አቀመሣቸው እንድንል ያደርገናል፡፡ ምናልባት አንድ ተመሣሣይ መምህር ገጥሟቸው ይሆን? ያሰኘናል፡፡”
በሌላ በኩል፣ ጥናቱ የአለቃን የትውልድ አካባቢን የፎገራን መልክዓምድራዊና ህብረተሰባዊ ሥብጥር ማንፀሪያ አድርጐ የሣቸውን ቀልድ አዋቂነት ለማስተንተን ሞክሯል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የፎገራ ገበሬዎች አዲዲስ ቴክኖሎጂ ጋር በፍጥነት መላመዳቸውና ሩዝን በተለየ ሁኔታ እያዳቀሉ ውጤታማ መሆናቸውን ካሥተነተነ በኋላ፣ “ይህ ከዘመን አፈንግጦ መጓዝ የሀገሩ ልማድ ይሆን?” በማለት ይጠይቃል፡፡ እዚህ ላይ፣ ከ150 ዓመት በፊት የነበረን የአለቃ ቀልድ አዋቂነት፣ ዛሬ ላይ ባሉ “የፎገራ ገበሬዎች”፤ ከንቃተ ህሊናና ብቃት ለማሣየት የቀረበው መላምት ግን፣ ተጠያቂያዊነቱ ራቅ ያለ፣ በስሱም ቢሆንም ስሜታዊነት የታየበት ይመስላል፡ ደግነቱ ጥናቱ፣ ከመላምቱ ጥያቄ ቀጥሎ፣ “ገና ብዙ የአንትሮፖሎጂ፣ የግብርና እና የታሪክ ምርምር የሚሻው በመሆኑ ከኔ ይልቅ ልሒቅ ለሆኑት እንዲቀጥሉበት አደራ እላለሁ” በማለት የአጥኒውን አርቆ አስተዋይነትና ብልህ ተመራማሪነት አግዝፏል (እኔ ደግሞ በፎክለር ሣይንስ በስፋት ተበጥሮ ሊጠና ይገባል የሚል አስተያየት፣ በትሁትነት ልጨምር እፈልጋለሁ)፡፡
“አለቃ ገብረሐና ሰብዕናና አስተዋፅኦ” በሚለው በሁለተኛ አብይ ክፍል ደግሞ፣ የአለቃን ማንነትና የፈጠራ ባለቤትነት ለማሣየት ተሞክሯል፡፡ ሰብዕናቸውን አስመልክቶ፣ አለቃ የድሆች ጠበቃና ተሟጋች እንደነበሩ በሌላ በኩል፣ለነገስታቱ የማይመለሱ፣ ፈጣሪያቸውን ለመጠየቅ የተነሡ ደፋር ቀልድ አዋቂ እንደነበሩ ተብራርቷል፡፡
ጥናቱ በአለቃ አስተዋጽኦነት ከገለፀው ውስጥ በአለቃ ልጅ ስም የሚታወቀው “የተክሌ ዝማሜ” አንዱ ነው፡፡ አለቃ ከአፄ ቴዎድሮስ ሸሽተው ዘጌ በገቡ ጊዜ በአካባቢው የሚበቅለውን የሸንበቆ ውዝዋዜ ተመልክተው፣ ዝማሜ መፍጠራቸውና በልጃቸዉ በአለቃ ተክሌ የበለጠ ዳብሮ የሚያገለግል ትሩፋታቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ጥናቱ፣ የዶናልድ ሌቪን፣ Wax & Gold: Tradition and Innovation in Ethiopia (1965) የሚል መጽሐፍ ጠቅሶ፣ አለቃ ገብረሐና በሰምና ወርቅ ቅኔያዊ ቀልዳቸው የታወቁ እንደሆኑ በአፅንኦት ገልጿል፡፡
ጥናቱ በመጨረሻም “ምን ይደረግ?” የሚል ተግባር ተኮር ጥያቄ አንስቷል፡፡ “አንድ ኢትዮጵያዊ ደራሲ የብዙዎች ኢትዮጵያዊያን ታላላቅ ሰዎች ጥፋት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ነው እንዳለው እንደ አለቃ ገብረሐና ያሉ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ባይሆኑ ኖሮ ዛሬ አያሌ መታሰቢያዎች በኖሯቸው ነበር፡፡ ይኼው ከተማችን አዲስ አበባ እንኳን ለስንቱ የመንገድ ስም ስትሰጥ ለእርሳቸው ነፍጋቸዋለች” በማለት ቁጭት ፈጣሪ መሪር ጥያቄ ያነሣና፣ ”ቢቻል አምስቱ ነገሮች ካልተቻለ አንዱ ቢደረግላቸው” በማለት ይቋጫል፡ እኔም አጥኚው ዳንኤል ክብረት ያነሣቸውን የይሁንታ ጥያቄዎች በማቅረብ ልሰናበት፤
መንደራቸው፣ ቦታቸው እና መቃብራቸው ቢጠበቅ
በመንደራቸው አጠገብ የሚያልፈው መንገድ በስማቸው ቢሰየምላቸው
በየዓመቱ በአለቃ ገብረሐና ስም የቀልድ [ቀልዶቻችን የሀገራችን መሪር ፍልስፍና ማቀንቀኛችን ናቸው እንዲሉ] ሰሞን፣ ውድድርና ትዕይንት ቢቀርብ
በቀልድ ሰሞን በሚደረገው ውድድር አሸናፊ ለሆነው ሰው ወይንም ቡድን በአለቃ ገብረሐና ስም የተሰየመ ዓመታዊ ሽልማት ማዘጋጀት”

 

Read 5472 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:34