Monday, 23 December 2013 10:10

“The Show must go on” በቃል እና በተግባር

Written by  ቤተማርያም ተሾመ ይልማ
Rate this item
(2 votes)

“መድረክ መቅደስ ነው፤ ካህናቱም ተዋንያኑ” የሼክስፒር ዝነኛ አባባል
የዘወትር የክህነት ሥርአት አይታጐልም፤ ነውር ነው፤ ጫን ሲልም ሃጢያት ነው፡፡ ከህዝብ (ከተደራሲያን) የተለዩ (የተቀደሱ) ካህናት (ተዋንያን) የመለየታቸው ግብ እና ምስጢር በመቅደሱ ዘወትር እንዲያገለግሉ፣ ከእለት ተእለት የኑሮ ውጣ ውረድ ተለይተው ለመረጣቸው ህዝብ ዘወትር እንዲያጥኑ ነው፡፡ በሼክስፒር ሃሣብ ከተስማሙና “መድረክ መቅደስ ነው” ካሉ 24 ሠአት እንዲንተገተግ የታዘዘውን የመቅደሱን ፋና ዘወትር ሊለኩሱ፣ በብርሃኑ ድምቀት እና ሙቀት የመድረኩን ቅድስና ሊያውጁ ይገባል፡፡ ለእነዚህ ከአህዛብ (ተደራሲያን) የተለዩ (የተቀደሱ) ጠቢብ ሌዋውያን፤ መድረክ የሥራ ቦታቸው ብቻ ሣይሆን የመኖሪያ ቤታቸው፣ የማረፊያ ታዛቸው፣ የምግብ ገበታቸው በአጠቃላይ የእለት ከእለት ኑሮአቸው መሃከለኛ ጉዳያቸው ነው፡፡
ይህን ለማለት ያነሣሣኝ ባለፈው እሁድ በመዲናችን ስለተከናወነ አንድ ክስተት ጥቂት ልል ፈልጌ ነው፡፡ በእለቱ ከቀኑ 8፡00 ጥሪ ወደተደረገልኝ የመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ ፊልም ትርጉም ሥራ ምረቃ በአል ላይ ለመገኘት በ6 ኪሎ የስብሠባ ማዕከል ተገኝቻለሁ፡፡ ስነ ስርአቱ በመርሃ ግብሩ መሠረት የተከናወነ ቢሆንም አንድ ትልቅ ክፍተት ነበረበት። የሥራው ባለቤት ማለትም የፊልሙ ዋና ተርጓሚ እና ተራኪ በቦታው አልተገኘም፡፡ በስነስርዓቱ ማብቂያ ላይ የፕሮግራሙ መሪ ወደ መድረክ መጥተው፣ የስራው ባለቤት በስፍራው ያልተገኘው ከዘወትር ሥራው ከብሔራዊ ቲያትር መድረክ ሊለይ ባለመፍቀዱ እንደሆነ ገለፁ፡፡ በዚህ ተደንቀን ሣንጨርስ ሌላ የሚያስደንቅ ነገር ነገሩን፡፡ በእለቱ ተዋናዩ የቀለበስ ስነ ስርአቱን በብሄራዊ ቲያትር እንደሚፈፅም የገለፁት የመድረክ መሪው፤ ለፊልም ምርቃት የተገኘነው ታዳሚዎች በብሔራዊ ቲያትሩ ሠርግ (ቀለበት) ላይ እንድንታደም ግብዣ አቀረቡ፡፡
በቀጥታ ወደ ስፍራው አመራን፡፡ ትርኢቱ ገና ባለመጠናቀቁ ከትያትር ቤቱ ጀርባ ለአፍታ ተቀምጠን ሊፈፀም ጥቂት የቀረውንና በተስፋዬ ገ/ማርያም የተዘጋጀውን “ቶፓዝ” ቲያትር መመልከት ጀመርን። ቲያትሩን ከጀመሩት ተመልካቾች እኩል ውጥረት ውስጥ ስላልሆንን፣ የመድረኩን ዙሪያ ገባ በግርምት እያስተዋልን ነው፡፡ መድረኩ ያው መድረክ ነው፡፡ አበባ በታኝ ህፃናት፣ የሠርግ ፕሮቶኮል አልያም ሌላ ሠርግ ሠርግ የሚሸት ምንም አይነት ድባብ አይታይም፡፡ ወደ ፍፃሜው በተቃረበው የቲያትር ታሪክ ውጥረት ውስጥ ያለው ተመልካች፤ የመጨረሻ ትንፋሹን ሊተነፍስ ሣንባውን በአየር፣ ልቡን በትኩስ ደም ሞልቶ ጫን ጫን ይተነፍሣል፡፡ ቲያትሩ አለቀ። ታዳሚው ተነፈሠ፡፡ ለውብ ተውኔቱ እና ለድንቅ ተዋንያኑ ከመቀመጫው ተነስቶም አጨበጨበ። ወዲያውኑ ከአዳራሹ ጀርባ በድምፅ ማጉያ አንድ ሠው መናገር ጀመረ፡-
“ውድ ተመልካቾች፤ እባካችሁ ለ10 ደቂቃ ታገሱን” ህዝቡ ትንፋሹን ሠበሠበ፡፡ እንደቆመ ወደ መድረኩ በጉጉት አፈጠጠ፡፡ ተናጋሪው ቀጠለ፡-
“በእለቱ የተመለከታችሁት ተውኔት፣ መሪ ተዋናይ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ ይህ ተውኔት እየተካሔደ ባለበት ሠአት፣ ተዋናዩ ያዘጋጀው የመፅሃፍ ቅዱስ የዘፍጥረት ታሪክ የአማርኛ ትርጉም ትረካ ፊልም በመመረቅ ላይ ነበር። ነገር ግን እናንተን ተመልካቾቹን እና መድረኩን በማክበር በምረቃው ላይ ሣይገኝ ቀርቷል፡፡ ሌላ ጭብጨባ እና ፉጨት፡፡
በመቀጠልም አርቲስቱ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልእክት እንዳለ ገልፆ እድሉን ለአርቲስቱ ሰጠ፡፡ በተውኔቱ ፍፃሜ ህዝቡን ለማመስገን እና ለመሠናበት ከተደረደሩት አንጋፋ እና ወጣት ተዋንያን መካከል ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ ወደፊት በመውጣት ለህዝቡ ያለውን ክብር በታላቅ ትህትና ከገለፀ በኋላ አንድ ነገር ለማከናወን ህዝቡን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ በሚያከብረው መድረክ እና በሚወደው ህዝብ ፊት ማግባት ቀለበት ማሠር እንደሚፈልግ…
ረጅም ዝምታ … ግራ መጋባት … በስተመጨረሻ ታላቅ ፉጨት እና ጭብጨባ አዳራሹን አናወጠው። አርቲስቱ ተንበርክኮ ወደ መድረኩ ለወጣችው ባለቤቱ፣ ከተወዳጇ አርቱስት ሃረገወይን አሠፋ የተቀበለውን ቀለበት አጠለቀ፡፡ መድረኩ ተናወጠ። በስተመጨረሻ አርቲስቱ ለተወሠኑ ታዳሚዎቹ ያዘጋጀው የእራት ግብዣ፣ በራስ ሆቴል እንዳለ እና የሙሽሮቹ ማረፊያም ታላቁ የነፃነት አባት ኔልሠን ማንዴላ ከአመታት በፊት ባረፉበት ታሪካዊ ክፍል እንደሆነ ሲናገር ሌላ አድናቆት እና ጭብጨባ አስተጋባ፡፡ ከእራት ግብዣው በኋላ ማንዴላ አርፈውበት ከነበረበት ክፍል ፊት ለፊት ከፎቶግራፋቸው ጐን ቆሜአለሁ፡፡ አርቲስቱ እና ባለቤቱ በአፍሪካውያን ልብስ ደምቀው ያረፉበትን ታሪካዊ ክፍል ለታዳሚዎቻቸው ኩራት ማስጐብኘት ጀመሩ፡፡ ከህዝብ ሁካታ እና ጫጫታ አይሎ የሚሠማ የገዛ እራሴን ድምጽ እያደመጥኩ በሃሳብ ተውጫለሁ፡፡ አርቲስቱ ምን እያደረገ ነው? ለአፍታ በሃሳቤ የኋሊት ገሠገስኩ፡፡ ከመድረክ እና ከጥበብ ጋር የተቆራኙት የአርቲስቱ አብይ የህይወት ክስተቶች በየተራ ታወሱኝ፡፡
አርቲስቱ በሚወዳቸው እና በሚጠራባቸው እናቱ ቀብር ዕለት በሚወደው መድረክ እና በሚያከብረው ህዝብ ፊት በስራ ላይ ነበር፡፡
የመጀመሪያ ልጁን አንደኛ አመት ያከበረው “ፊልም ቦይ” የተሰኘ መጽሐፉን ለልጁ በስጦታ በማበርከት ነው፡፡
በአንድ ወቅት ልደቱን ያከበረው ከጐዳና ልጆች ጋር ድሪቶ ለብሶ ለሚሠራው Experimental ቲያትር እየተዘጋጀ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ “The show must goon” (ትያትር አይቋረጥም) በሚል ርእስ የፃፈው ጽሑፉ የታወሰኝ። በዚህ ጽሑፍ አርቲስቱ ለመድረክ እና ለሙያው ሊሰጥ ስለሚገባ ክብር ጠንከር ባሉ ቃላት ተግሣፅ አዘል መልእክት ማስተላለፉ ሲታወሰኝ በብእር ያወጀውን በግብር እያሳየ እንደሆነ ተገነዘብኩ፡፡
ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ ዘርፈ ብዙ አርቲስት ነው፡፡ እጅግ የበዙት ሙያዎቹ ከመድረክ እና ከስክሪን ተርፈው የግሌ በሚለው የእለት ተእለት ህይወቱ ሠርገው ከመግባት አልፈው የየእለት እንቅስቃሴው አካላት ሆነው ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህም ነው በአንድ ወቅት በዚሁ ጋዜጣ “ሮማንቲሲዝም” በሚል ርእስ በፃፈው ጽሑፍ እንደገለፃቸው፣ የሮማንቲክ ገጣሚያት ባይረን እና ሼሊ በተራ የህይወት እንቅስቃሴው ጭምር የህይወት ፍልስፍናውን በመግለጽ ሥራ ላይ የተጠመደው፡፡  
ፈለቀ የመድረክ መሪ፣ ተዋናይ፣ ገጣሚ፣ ተራኪ እና አዘጋጅ ነው፡፡ በእነዚህ ሙያዎቹ ምስጉን እና በብዙዎቹም በአገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ነው፡፡ በተለይ ከሚታወስባቸው ሥራዎቹ መካከል፡-
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ በ4 ቀን ውስጥ ያዘጋጀው ኦፔራ Experimental play
በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተሠራውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ፊልም ትረካ ከአንጋፋ ተዋንያኑ ፈቃዱ ተክለ ማርያም እና መሠረት መብራቴ ጋር
በ1941 ዓ.ም የታተመውን የተመስገን ገብሬን (የአገራችንን የመጀመሪያ አጭር ልብ ወለድ) “የጉለሌው ሠካራም” ትረካ
በቡርኪናፋሶ የፊልም ፌስቲቫል የተሸለመበት እና በክርስቶስ ሣምራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የሠራው In search of the Devil ፊልም … ከብዙ ሥራዎቹ መካከል እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ፈለቀ ሌላው የሚለይበት ባህሪው በየጊዜው ያገኛቸውን ሽልማቶች በማህበረሰብ ግንባታ ሒደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ብሎ ላመነባቸው አርአያ ግለሰቦች መታሠቢያነት ማበርከቱ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
በጥቅምት 2003 ዓ.ም ያገኘውን የ“ቤስት ፊልም አክተር” ሽልማት በፊልም ስራ ለሚሠማሩ ኢትዮጵያውያን
በ2004 ያገኘውን የ“ምርጥ የመድረክ ተዋናይ” ሽልማት በሙያው ለተሠማሩ አንጋፋ ከያንያን
በ2006 ያገኘውን የ“ምርጥ ፊልም ተዋናይ” ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፊልም ላሣዩት አጤ ምኒልክ እንዲሁም
በኦርማኖ አልሚን ፊልም በትረካ፣ በተርጓሚነት እና አዘጋጅነት ከተበረከቱለት ሽልማቶች ሁለቱን ለብሔራዊ ቲያትር እና ለኔልሰን ማንዴላ ቀብር ሥነ ሥርአት መታሰቢያነት አበርክቷል፡፡
የዚህ  ጽሑፍ አላማ አርቲስቱን በደረቁ ማሞካሸት አይደለም፡፡ በዚህ የጥድፊያ እና የ“ከተፋ” ዘመን ለሙያ መኖር እና ሙያን መኖር እንደሚቻል ከዚህ ወጣት ከያኒ እንድንማር በማሰብ ነው፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንደተባባልነው ሁሉም ሰው የተቀበለው የኔ የሚለው መክሊት አለው፡፡ የሰርክ መስዋእቱን የሚያቀርብበት የራሱ መሠዊያ ባለቤትም ነው፡፡ ለተለየለት ሙያም ቅዱስ አገልጋይ ሌዋዊ ነው፡፡
የስራ ቦታ ቢሮ ብቻ አይደለም፤ ሥራ ህይወት ነው፤ ህይወትም ሥራ ነው፡፡ እንደማይቋረጠው የክህነት ሥራ ሁሉ የተጐናፀፍነውን የክህነት ካባ ቢሮ ሠቅለን አንውጣ፡፡ የትም ለብሰነው በኩራት እንንጐማለል፡፡ ሥራችንን እንኑረው-እንደ ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፡፡  
The show must go on! ትርኢት አይቋረጥም!

Read 1158 times