Monday, 23 December 2013 10:13

“የአውሮፓን ፊደላት አጠቃቀምና አመጣጥ ለማወቅም ግእዝ ያስፈልጋል” ጋብሬላ ኤፍ .ሲልታ

Written by  በሰሎሞን አበበ ቸኮል saache43@yahoo.com Solomon.abebe.395@facebook .com
Rate this item
(2 votes)

ከጥንተ ሲናዊው የፊንቃውያኑ ፊደል ተገኝቷል፤ ከፊንቃውያኑ ካድመስ የተባለው ሰዋቸው ግሪኮች ፊደላቸውን ሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል (ኤትሩስካኖች) የተባሉ በሮም ሰሜናዊ ክፍል የሰፈሩ ነገዶች ነበሩ። እነሱም “ኤትሩስካን” የተባለ ፊደል ነበራቸው። ከግሪክ እና ወይም ከኤትሩስካን የላቲን ፊደል ተወልዷል፣ ከላቲን ደግሞ የዛሬዎቹ አውሮጳውያን ቋንቋዎች ለሁሉ መጻፊያ የሆነው ሮማዊ የጽሕፈት ሥርዓት ተገኘ፡፡

ከግእዝ የመጡትን የአማርኛ ፊደላት ለመነካካት ሰበብ የሚደረገውን የሞክሼ ፊደላትን ነገር  እንድናነሳ ግድ እየኾነ “እንደገና ፊደል እንደገና” በማለት ከዚህ በፊት አንድ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር። “ለመሆኑ እነዚህን ሞክሼ ፊደላት የተመለከቱ የፊደል መነካካቱን ጥያቄ (እነሱ ማሻሻል ይሉታል) በምን ምን ምክንያት ነው የሚጠይቁት” በማለት አንድ በአንድ እያነሳሁ የተመለከትኹበት ነበር፡፡
እነዚያ ሞክሼ ፊደላት ቢነካኩ (ቢጐድሉ) የሚያጐድሉብንን ለማስከተል ረዘም ያለ ጽሑፍ፣ በተለይም ሥነ ልሳን ፊደላትን የድምጽ ምልክቶች አድርጐ ብቻ ለምን እንደሚመለከታቸው በመጠየቅ፣ ጽሕፈት ከትእምርተ ድምፅነት ሌላ በርከት ያሉ ውክልናዎች ወይም ይዘቶችና አገልግሎቶች እንዳሉት በመጠቋቆም፣ ፊደላቱን ማጉደል እነዚያን ማሳጣት መሆኑን የሚገልጸውን አንድ ክፍል እያዘጋጀሁ ሳለ፣ የበፊቱን ካነበቡ ሰዎች የተለያዩ መልእክቶች በኢሜል አድራሻዬ ይመጡ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ተጨማሪ የሚፈልጉ፣ አንዳንዱ “ፖስት” እና “ትዊት” አድርገው የሚሉ ነበሩ፡፡
ሁለት አንባቢዎች ግን በፊደላቱ ላይ የተሠሩ ሥራዎችን አባሪ ያደረጉባቸውን መልእክቶች ነበር የላኩልኝ፡፡ አንደኛው የዶክተር አየለ በከሬን “ኢትዮፒክ” የተባለውን መጽሐፍ እንዳለ ነበር የላከልኝ፡፡ “መጽሐፉን ባጋጣሚ አግኝቸው ላንተም ይጠቅማል በማለት…” ብሎ ላከልኝ (ምስጋናዬን ለአቤል እዚህም ላይ ደግሜ አቀርባለሁ)፡፡ የዶክተር አየለን መጽሐፍ የሚዳሰስ ጽሑፍ፣ ከእርሳቸው ጋር የተደረገ ቃለምልልስ፣ እንዲኹም ያን መጽሐፍ ለመጻፍ ምክንያት የኾናቸውን ከግእዝ የተወሰደውን የአርመኖችን ፊደል የተመለከቱ ሥራዎችን በመጠኑ በመተርጐም በዚችው አዲስ አድማስ ያቀረብኩት ከመኾኑም በላይ፣ በ2005 ዓ.ም መጽሐፉን በአማርኛ እንዲተረጐም ሰጥተውኝ ሰርቼ አስረክቤአቸዋለኹ፡፡
አብዛኛው መነሻ ሐሳብ ከዚሁ ከአየለ በከሬ     “ኢትዮፒክ” የተገኘ የሚመስለውን ሌላውን ግሩም የጥናት ወረቀት አባሪ ተደርጐ የተላከበት ሁለተኛው መልእክት ደግሞ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
“ፍቅሩ ተምትም፣ ሃይ ሰሎሞን፣ የኢትዮጵያው ሥርዓተ ጽሕፈት ወዳጄ አሁን በቅርቡ የግእዝን ጽሕፈት የሚመለከት ድንቅ ወረቀት (የጥናት) አገኘኹ፡፡ ደሴ (በ10፡00 P.M) ስለ ጽሕፈቱ የትመጣ እንዲኹም ከሮማዊው ሥርዓተ ጽሕፈት አኳያ ያለውን ቁብ የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያላገኘኸው ከሆነ እንደሚጥምህ በማሰብ ላክሁልህ።
“ጥናታዊው ወረቀት የግእዝ ጽሕፈት በትእምርተ ሥዕልነቱ፣ በትእምርተ ከፊለቃልነቱ (syllographic)፣ በትእምርተ ፈለክነቱ፣ በስነ ኁልቁነቱ እና በትእምርተ ሐሳብነቱ የሚኖሩትን ረቂቅ እሴቶችና ባሕርያቱን ይገልጻል፡፡
ኾነ ብሎ እነዚህን ፊደላት መለወጡ እነዚህን እና የአባቶቻችንን ጥንታዊ እውቀት፣ ጥበብና ፍልስፍና ወደማሳጣቱ ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ ነገር የበለጠ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ረገድ አንተ የምትለውንም ባነብብ ደስ ይለኛል፡፡ የጽሕፈት ሥርዓታት በጊዜ ሒደት የመለወጣቸውን ነገርስ ትቀበለዋለህ? ከሆነስ እንደነ ዶክተር በዕድሉ ዋቅጅራ ያሉት የሚያቀርቡት ሐሳብ ምን የተለየ ኢምፓክት ያመጣል? አመሰግናለኹ፡፡
ከዚህ መልእክቱ ጋር የላከልኝ ወረቀት “ዩዜጅ ኦፍ ዘ ግእዝ ራይቲንግ ሲስተም ኦፍ ኢትዮፕያ” የሚል፣ ጋብሪኤላ ኤፍ ሴልታ በተባሉ ምሁር የተሠራ ጥናታዊ ወረቀት ነው፡፡
ንጽጽራዊ የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈትን የአውሮፓውያን መጻፊያዎችን ካስገኘው ሮማዊ አልፋ ቤት ጋር በንጽጽር የሚያቀርብ ጥናታዊ ሥራ ነው፡፡ ምልከታው ጥሩ ሆኖ ስለታየኝ፣ ጀምሬው ከነበረው ጋር አዋድጄ ለሁላችንም እንዲሆን ማድረጉን መረጥሁና የጀመርኩትን እንዳለ በመተው ከፍቅሩ ተምትም ወረቀት በጥቂቱ በቀጥታ እያቀረብኹ እና አስፈላጊ በሆነበትም በመግባት አዘጋጀሁት፡፡  እንዲህ ይነበባል፡-
“የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲሁም የሮማዊውን አልፋ ቤቶች የዕድገት ሒደት እናም የአሁኑን አጠቃቀም ለማወቅ የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈትን ማጥናት (ማወቅ) ያስፈልጋል፡፡ እንዲህም ሲባል የዛሬ ዘመኖቹን የምዕራባውያን አልፋ ቤቶች ከጥንታዊዎቹ ሥዕላዊ ፊደላቶች ጋር የሚያገናኘው ድልድይ የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈት ብቻ ነው ማለትም አይደለም”
ሁለቱም የጽሕፈት ሥርዓቶች፤ ሥራቸውን የጥንቱ ግብፃዊ ሂየሮግሊፍ በማድረግ፣ ከዚህ እንደተገኙ ለመቁጠር፣ ጥንተ ሲናዊ ጽሕፈት ያነሳል። እዚህ ላይ “ፕሮቶሺናዊ” የሚባለው ከግእዙ ጋር አንድ ሆኖ መገኘቱ በመታወቁ፣ ይህም ከግብፃዊው ሂየሮግሊፍ እንደተገኘ በመቁጠር፤ ሮማዊው ደግሞ ከጥንተሲናው በፊንቃውያን፣ በግሪክ፣ በላቲን በኩል የተገኘ በመሆኑ ይኸንኑ በመያዝ ነው እንዲህ የተገለፀው፡፡ በእርግጥም የሮማዊውን ጽሕፈት እስከ ጥንተሲናዊው ድረስ ወደ ላይ ሐረጉን መቁጠር ይቻላል፡፡ ወይም ከጥንተ ሲናዊ ጀምሮ በመውረድ እንደምን ሆኖ ከሲናው የመጀመሪያ ጽሕፈት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ፣ በጽሑፉም እንደቀረበው፣ ማየት እንችላለን፡፡
ከጥንተ ሲናዊው የፊንቃውያኑ ፊደል ተገኝቷል፤ ከፊንቃውያኑ ካድመስ የተባለው ሰዋቸው ግሪኮች ፊደላቸውን ሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል (ኤትሩስካኖች) የተባሉ በሮም ሰሜናዊ ክፍል የሰፈሩ ነገዶች ነበሩ፡፡ እነሱም “ኤትሩስካን” የተባለ ፊደል ነበራቸው፡፡ ከግሪክ እና ወይም ከኤትሩስካን የላቲን ፊደል ተወልዷል፣ ከላቲን ደግሞ የዛሬዎቹ አውሮጳውያን ቋንቋዎች ለሁሉ መጻፊያ የሆነው ሮማዊ የጽሕፈት ሥርዓት ተገኘ፡፡
በሌላ በኩል፤ በተለይ ከኤፍራጥስ-ጢግረስ ወንዞች በስተግራ ለሚገኙ አብዛኞቹ ጽሕፈታት አባት ተደርጐ የሚቆጠረው ጥንተ ሲናዊው ራሱ ከግእዝ ፊደላት ጋር ያለው መመሳሰል በግልጽ የሚታይና በዶክተር አየለ ቢከሬ የምርምር ሥራም የተረጋገጠ በመሆኑ፣ በዚህ ጥናት ደግሞ ግእዝ በቀጥታ “ከሂዩሮግሊፍ ወረቀት” ስለሚል የሁለቱም ሥር ሂየሮግሊፍ ድረስ የሚሄድ አድርጐ ያቀርባቸዋል፡፡ ጥያቄ የሚኖረው ጥንተ ሲናዊው ግእዝና የሂየሮግሊፍ ልጆች መኾናቸው ላይ ይሆናል፡፡
ለዚህ ድምዳሜ የሚያበቃ አንድ ነጥብ ቢኖር፣ ሂየሮግሊፍ የተባለው የጥንት ግብፃውያን መጻፊያ በ3000 ቅ.ል አካባቢ ላይ ይጻፍበት እንደነበር የአርኬዎሎጂ ማስረጃ መኖሩ፣ ለጥንተ ሲናው ደግሞ፣ ይኼው ጽሑፍም ሆነ በአመዛኙ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛው ዋቤ የሆነው የዶክተር አየለ በከሬም መጽሐፍ የጠቆሙት የአርኪዎሎጂ ግኝት የ1500 አመት ቅ.ል የተገመተ በመሆኑ፣ በታሪክ ዘመን መቀዳደማቸውን በዋነኝነት የያዘ፣ በተጨማሪም የሁለቱ ጽሑፎች መገኛ ቦታ አንድ እንደሆነ ለመግለጽ የተሞከረበት ዓይነቱ አንድ ሆኖ ቢገኝ እንኳ ብዙም አያወላዳም፡፡
በዘመን ቅደም ተከተል ከተሔደ፣ ይህ ጽሑፍ የሳተው አንድ ሌላ ጽሕፈትም በዚሁ አካባቢ ከሂየሮግሊፍ ያነሰ፣ ከጥንተ ሲናው የበለጠ ዕድሜ የተሰጠው መግባት ሊኖርበት ነው፡፡ ይህም “ሂየሬቲክ” የተባለው ጽሑፍ ነው፡፡ ለሂየሬቲኩ ከሂየሮግሊፍ አንድና ሁለት መቶ ዘመን አነስ ያለ ዕድሜ የተሰጠው የአርኬዎሎጂ ማስረጃ አለው። ስለዚህ ሂየሮግሊፉ ሂየራቲኩን ሂየራቲኩ ጥንተ ሲናዊውን አስገኘ ማለት ነበረበት፡፡
በመሠረቱ የዘመን መቀዳደሙ ጉዳይ የከርሠ ምድሩ ማስረጃ መገኘት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከጥንተ ሲናዊው እንደወረደ የሚገለጽ አንድ የመካከለኛው ምሥራቅ ጽሕፈት ከልደት በፊት 1800 አመት ተገምቶ ይገኛል፡፡ የጥንተ ሲናው እድሜ ከዚህ ያነሰ ሆኖ (1500 ቅ.ል) እያለም ነበር ያንኛው ከሲናው የወረደ እንደሆነ የተገለፀው፡፡
ጥንተ ሲናው የዶክተር አየለ በከሬ መጽሐፍ እስከሚታተምበት ድረስ (በ.1996) የነበረው የጥንተ ሲናው ግኝት የ1500 ቅ.ል. ያስቆጠረ ነበር። ዛሬ ሲና ተብላ በምትጠራው የስራ ቤት የከርሠ ምድር ማስረጃ ብቻ ነበር፡፡
መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ሁለት አመት ቆይቶ፣ በመኻል ግብጽ፣ በአባይ ሸለቆ ውስጥ ሌላ ሁለተኛ የዚሁ ጽሕፈት የከርሠ ምድር ግኝት ተገኝቷል፡፡ የዚኸኛው ዕድሜ ደግሞ ከበፊቱ ላይ 200 አመት ያህል ጨምሮበታል፡፡
(ይህ ጽሑፍ ግን በ2001 (እ.ኤ.አ) ቢሠራ ከሁለት አመት በፊት የተገኘውን አዲስ ግኝት ሳይጨምር በቀጥታ ከዶክተር አየለ በከሬ እንደተገኘው የ1500 አመት ዕድሜን ብቻ ይዞ ነው የሚገኘው፡፡ ይህም ስለ ጽሑፉ አስቀድመን እንደጠቆምነው የዶክተሩን መጽሐፍ ብቻ በዋነኝነት መጠቀሙን ያመለክታል።)
ዋናው ጉዳያችን ግን የዘመኑ ጉዳይ እንዲህ ሲገኝ የሚቀየር በመሆኑ፣ አንደኛው ከአንደኛው የቀደመ ዘመንን ያስቆጠረ የከርሠ ምድር ማስረጃ ስላለው፣ ያንኛው ይኸኛውን አስገኘ ማለቱ እምብዛም አያስተማምንም፡፡
ግእዝም ሆነ ጥንተ ሲናዊው የሂየሮግሊፍ ውላጆች ናቸው ማለቱ በዚህ ረገድ ታይቶ ከሆነ አያስተማምንም፡፡ ምሑራኑም የሂየሮግሊፍ ለጥንተ ሲናው ወላጅ አባትነት ላይ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ አልደረሱም፡፡ በተለይ በግእዝ የትመጣ ላይ ዶክተር አየለ፤ ግብፃዊው ጽሕፈት ከተገኘበት በተለየ አካባቢና ባህል የተገኘ መሆኑን ፊደላቱ ራሳቸው እንደሚመሰክሩት እነዚህኑ ሁለት ጽሕፈቶች በንጽጽር ባቀረቡበት ገጽ ይጠቁማሉ፡፡
ስለዚህ በዚህ ጥናታዊ ወረቀት የግእዙም ሆነ የሮማዊ ሥር ሂየሮግሊፍ እንደሆነ የተገለፀበትንና ከዚህ በኋላም ይህንኑ በመያዝ የሚገለፀውን በጥያቄ ምልክት ማለፉ ይሻላል፡፡
የጥናት ወረቀቱ ከዚህ ዓይነቱ ጥቆማው በማስከተል የሮማዊውን ጽሕፈት በየዐረፍተ ዘመኑ ያሳያቸውን ለውጦችና ዕድገቶች ያቀርባል፡፡
ሮማዊው ጽሕፈት ከልደት በፊት 600 አመት ላይ 21 ፊደሉን (5ቱን የግሪክ ዋየሎች ጭምር) ይዞ ተጀመረ፡፡ ያን ጊዜ አጻጻፉ ከግራ ወደቀኝ ሔዶ ሲያበቃ፣ ከቀኝ ወደ ግራ እንደሚመለስ፣ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ እንደገና ከግራ ወደቀኝ እያለ የሚጻፍበት ነበር፡፡ (ባውስትሮ ፌዶን” የሚሉት ዓይነት፡፡)ከዚህ በኋላ 500 ዘመን ቆይቶ ያንንም ያህል ትልቅ ሥራ ተደርገው ያልተቆጠሩ 4 ፊደላትን ጨመረ። የፊደላቱ ንድፍ እና ተመጣጣኝነት ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጣ፡፡ ከልደት በፊት የመጀመሪያ መቶ ዓመት ላይ የመጀመሪያዎቹ ሦስት የሮማን ፊደላት ተሠሩ፤ ካፒታል ሌተርስ የሚባሉት ተጨመሩ፤ አጻጻፉም ከግራ ወደቀኝ ብቻ በመሆን ጸና፡፡
በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በጽሑፍ መስመር ላይ ውበትን የሚጠብቁ ማሻሻያዎች ተደረጉለት (በቃላት መካከል ያለው ርቀት እኩል እንዲሆን ማድረጉን የመሰለው)
በ7ኛው መቶ ተነባቢነትን እና የጽሕፈት ፍጥነትን የሚጨምሩ ትናንሽ ፊደላትን መጨመሩን የመሰሉ ሥራዎች ተሠሩለት፡፡
በመካከለኛው ዘመን በፈረንሳይና ስፔይን ውስጥ የነበሩ የተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶች ማስተማሪያዎች ብቅ አሉ፡፡
በሻር ለማኝ ጊዜ ዘ(768-814 እ.ኤ .አ የኖረ) የአልፋ ቤትን ደረጃ መደበኛና ቀዋሚ የሚያደርግ መንግሥታዊ ዓዋጀ ታወጀ፡፡ ሻር ለማኝ ራሱ ያልተማረ፣ ማንበብ እና መጻፍ የማይችል ቢሆንም መንግሥቱን አንድ ለማድረግ (አንድ) የጽሕፈት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን የተረዳ (አስተዋይ) ነበር።
በዚኹም ምሑራኑን እና የሃይማኖት አስፋፊዎችንም አንድ አድርጐ፣ ሕዝብንም እንዲሁ ወደ አንድነት እሚያመጣ መሆኑን ስለተገነዘበ፣ ለዚሁ ሥራ የዮርኩን አልኩዊንን (አማካሪው የነበረ) በመመደብ ከተለያዩ ክልሎች የተለያዩ የአጻጻፍ ስልት አላባዎችን በመጠቀም፣ የካሮሊንጋን አጻጻፍ የተባለውን የሮማዊው ጽሕፈት ስልት እንዲያዝ አድርጓል፡፡
እስከ 13ኛው መቶ ክ/ዘ አንዳንድ ጊዜያዊ የአጻጻፍ ለውጦች በማድረግ፣ ጐቴክን የመሳሰሉ ድርብ ጽሑፎችን ጨማምሮ በ1500 ዛሬ ላይ አውሮፓውያን የሚጠቀሙበትን መልክ ያዘ፡፡
የጥናት ወረቀቱ የግእዙን ታሪክ ለመቀጠል፣ በግእዝና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ዩሮም እክልናዊነት ያለው ምሑራዊው አቀራረብ ያደረሰውን በደል ያነሳሳል፡” ይህ አውሮፓን ማዕከል ያደረገውን ምሁራዊነት፣ በዶክተር አየለ በከሬም ሰፊ እና ኃይለኛ ሙግት የተያዘበት ጉዳይ ነው፡፡
አየለ በከሬ በዩሮም እክልናዊ እውቀት ስለ ኢትዮጵያ፣ አልፎም ስለ አፍሪካ ታሪክ፣ በተለይም ከጽሕፈት ጋር የተያያዙ የታወቁ የ “ሂስትሪ” ትምሕርቶች እየጠቃቀሱ በመሞገት ከጣሉ በኋላ አፍሮምዕክልናን ያስይዛሉ፡፡
በጋብሬላ ኤፍ ሴልታ ወረቀትም የግእዝ ፊደላትን በተመለከተ የዩሮምዕክልናው ዘረኛ አመለካከት፣ የተሳሳተ እውቀትን ይዞ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
“የግእዝ ሥርዓተ ጽሕፈት ታሪክን እንደሮማዊው ለማቅረብ የቀለለ አይደለም። ለዚህም በዋነኝነት በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ፣ ነገር ግን ልክ ያልኾነ፣ በዩሮምዕክላዊው ግምቶች ላይ የተመሠረተው ትምሕርት ያመጣው ነው፡፡ ዛሬም የዩሮምእክልናዊው አመለካከት በስነ ቋንቋ አፈራረጅ ግዕዝን አፍሪካዊ ቋንቋ ሳይኾን ሴማዊ ቋንቋ ውስጥ ይመድበዋል፡፡ የግእዝን የትመጣ ጥናት ላይ የዘረኝነቱ ወረርሽኝ እንደሲልቪያ ፓንክረስት ባሉት የቅርብ ጊዜ ምሑራዊ የታሪክ ሥራዎች ላይም የሚታይ ነው፡፡”
ሲልቪያ ፓንኮርስት “ኢትዮፕያ ኤ ካልቸራል ሂስትሪ” በማለት ባቀረቡት መጽሐፍ ከደቡብ ዓረብያ የመጡ ፈላሲያን “የበለጠ ድንቅ የኾነ ሥልጣኔን” ለኢትዮጵያ እንዳስተዋወቁ ይገልጻሉ፡፡


Read 4079 times