Saturday, 28 December 2013 10:55

ዌስተርን ዩኒየንና ሚድሮክ ጎልድ በውጭ ምንዛሪ ይመራሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

         ከምርት ላኪ ድርጅቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና በአመት ውስጥ ከ100 ሚ. ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኘው ሚድሮክ ጎልድ፤ እንዲሁም በሃዋላ አገልግሎት መስክ ከ300 ሚ. ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኘው ዌስተርን ዩኒየን ሰሞኑን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሸለሙ፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የደረሰ ሲሆን፣ ከአንጋፋው ዌስተርን ዩኒየን በተጨማሪ ሌሎች ገንዘብ አስተላላፊ የሃዋላ ድርጅቶች በተፎካካሪነት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከሚሰሩት የሃዋላ ድርጅቶች መካከል፣ በአንደኛነት ከተሸለመው ዌስተርን ዩኒየን በመቀጠል ኤክስፕረስ መኒ ትራንስፈር ከ100ሚ. ዶላር በላይ በማስገኘት በሁለተኛነት ተሸልሟል፡፡ ቦሌ ኢንተርናሽናል የሃዋላ አገልግሎትም ከ50ሚ. ዶላር በላይ በማስገኘት የሦስተኛነት ደረጃ አግኝቷል፡፡

ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የአንደኝነት ደረጃ የተቆጣጠረው የሼክ መሐመድ አልአሙዲ ሚድሮክ ጎልድ ነው፡፡ ከወርቅ ምርት በየአመቱ የሚገኘው የሽያጭ ገቢ እያደገ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር ያለፈ ሲሆን ሚድሮክ ጎልድ በከፍተኛ እድገት የአንበሳውን ድርሻ የሚያመርት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሚድሮክ ጎልድን ተከትለው፤ በላይነህ ክንዴ የንግድ ድርጅት፣ አደም ከድር ትሬዲንግ እና ዋርካ ትሬዲንግ ከ35 ሚ. ዶላር በላይ በማስገኘት በሁለተኛ ደረጃነት ተሸልመዋል፡፡ ከ15 ሚ. ዶላር በላይ ያስገኙ ስምንት የቢዝነስ ድርጅቶች በሦስተኝነት የተሸለሙ ሲሆን፣ ከአስር ሚ. ዶላር በላይ ያስገኙ 12 ድርጅቶችና ከአምስት ዶላር በላይ ያስገኙ 29 ድርጅቶችም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከአንድ ሚ. ዶላር በላይ ያስገኙ 93 ላኪዎችና ሁለት የሃዋላ ድርጅቶችም ምስጋና ተቀብለዋል፡፡ ሁሉም ድርጅቶች ለሽልማት የበቁበት የስኬት ደረጃ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የሚያካሂዱት የቢዝነስ እንቅስቃሴን ብቻ እንጂ በሌሎች ባንኮች በኩል የሚያከናውኑትን ስራና የቢዝነስ ደረጃ አይጨምርም፡፡

Read 1722 times