Saturday, 28 December 2013 11:10

የኢትዮ ቴሌኮም ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

           ጋዜጣችሁ ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 12 ቀን 2006 ዓ.ም እትሙ ላይ፣ “ከዓመት በፊት ለተበላሸ ሲሚንቶ ማስቀመጫ ከ30ሺ ብር በላይ ወርሃዊ ኪራይ ይከፈላል” በሚል ርዕስ ለቀረበው ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ የሚከተለውን ምላሽ አቅርበናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዜና ዘገባው ሚዛናዊነት የጎደለው ከመሆኑም ባሻገር በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ፣ አንባቢን የሚያሳስት እና የኩባንያችንን ገጽታ የሚያጎድፍ ነው፡፡ በዜና ዘገባው መነሻ “በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ ለቴሌ ታወሮችና የኔትወርክ ግንባታ ከጅቡቲ ተገዝቶ የገባው ሲሚንቶ ከአንድ ዓመት በፊት መበላሸቱ ቢታወቅም በየወሩ ከ30ሺ ብር በላይ ለግለሰቦች ኪራይ እየተከፈለ የህዝብና መንግስት ሀብት እየባከነ እንደሚገኝ---” ሲል የፈጠራ ሃተታውን ይጀምራል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ሌሎች የሃገራችን ክልሎች ሁሉ በተለይ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና በክልሉ ባሉ ወረዳዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እና ለሌሎች ንብረቶች ማስቀመጫ የሚያገለግል ግምጃ ቤት በከተማዋ ከሚገኝ የግል ድርጅት ተከራይቶ ሲጠቀም መቆየቱና አሁንም እየተጠቀመበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዘገባው ተቋሙ መጋዘን መከራየቱ የተገለፀው ትክክል ቢሆንም መጋዘኑ የሚያገለግለው ግን ለሲሚንቶ ማስቀመጫ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ቁሳቁሶች ለማስቀመጥ ጭምር ነው፡፡

ምንም እንኳን በዘገባው እንደተገለፀው፣ ከንብረቶቹ መካከል የተበላሹ ሲሚንቶዎች ቢኖሩም መጋዘኑ ግን ለፕሮጀክቶች ሥራ የሚያገለግሉ የተለያዩ ንብረቶች ማኖሪያነት እና ለሌሎች ግብዓቶች ማስቀመጫነት እያገለገለ በመሆኑ፣ በዜናው እንደተጠቆመው ያለ አገልግሎት ለመጋዘኑ በከንቱ ክፍያ እየተፈፀመ እንዳልሆነ ውድ አንባቢያን እንዲረዱልን እንፈልጋለን፡፡ ሌላው የዘገባው ስህተት ደግሞ የወርሃዊ ክፍያ መጠን ላይ ነው፡፡ በዜናው እንደተጠቀሰው፣ ለመጋዘን ኪራይ የሚከፈለው ወርሃዊ ክፍያ 30ሺ ብር ሳይሆን 12,360 ብር ነው፡፡ መጋዘኑ በአሁኑ ሰዓትም በእንቅስቃሴ ላይ ለሚገኘው ለቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችና ለሪጅኑ የኦፕሬሽን ስራ የሚሆኑ ንብረቶች የሚቀመጡበትና ለነዚህ ሥራዎች አገልግሎት እየሰጠ ያለ ሆኖ ሳለ “ጥቅም ላይ ለማይውሉ ሲሚንቶዎችና ብረቶች ያለ አግባብ ኪራይ እየተከፈለ ይገኛል” በሚል መዘገቡ ስህተት ከመሆኑም በላይ የአንድ ወገን መረጃን ብቻ በዋቢነት በመጠቀም ለአንባቢያን የቀረበ በመሆኑ የዘገባውን ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ በጥቅሉ ዜናው ሲዘገብ መረጃውን ከሚመለከተው አካል ማጣራትና ሚዛናዊ ማድረግ እየተቻለ፣ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ የተሳሳተ መረጃ መቅረቡ አግባብ አይደለም፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ

Read 2864 times