Saturday, 28 December 2013 11:31

የጋዜጠኞች እስር መንግስትን፣ ማህበራትንና ፓርቲዎችን እያወዛገበ ነው

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(22 votes)

           መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው ሲፒጄ የተሠኘው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ጋዜጠኞችን በማሠርና በማንገላታት ኢትዮጵያ ከአለም ሁለተኛ ናት ማለቱን መንግስት እና በሃገሪቱ የሚገኙ የጋዜጠኞች ማህበራት አምርረው ሲያወግዙ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው፤ በእርግጥም ሃገሪቱ ጋዜጠኞችን እያሠረች ነው፤ ደረጃው ይገባታል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃም፤ “ሲፒጄ የሃገራችንን ስም ለማጥፋት ስለሚፈልግ ነው እንጂ፣ በፃፈው ፅሁፍ የታሠረ አንድም ጋዜጠኛ የለም፡፡ 3 ጋዜጠኞች የታሠሩት አሸባሪ ተብለው ነው” ብለዋል፡፡ በማህበራችን ጥረት በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች እስር ቆሟል ሲሉም ተናግረዋል አቶ አንተነህ። የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) ሊቀመንበር አቶ ወንደሰን መኮንን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሙያው ጋር በተያያዘ የታሠረ ጋዜጠኛ እንደሌለ ገልፀው፣ የታሠሩ ጋዜጠኞች ጉዳያቸው ሌላ ቢሆንም መፈታት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የሲፒጄን መግለጫ እንደማይቀበሉትና ድርጅቱ የራሱ ተልዕኮ እንዳለው አቶ ወንደሰን ጠቁመው፤ “ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሠር በአለም ሁለተኛ መሆን አትችልም፤ ሆናም አታውቅም” ብለዋል። የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ “ሲፒጄ የፖለቲካ አጀንዳ ያለውና መንግስትን በሃይል ለመለወጥ ከሚንቀሣቀሡ ድርጅቶች ጋር የተሰለፈ ድርጅት ስለሆነ፤ በተግባር ከጋዜጠኝነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም” ብለዋል፡፡ አቶ ሽመልስ፤ “እናንተ መቼ ታሠራችሁ? የማታውቁት ከማርስ የመጣና ‘የታሠረ ጋዜጠኛ አለ እንዴ?’ ሲሉም ጠይቀዋል። የሲፔጂ የአፍሪካ ወኪል፣ በ97 ምርጫ የቅንጅት አመራር የነበረና የኢትዮጵያን መንግስት በሃይል ለመገልበጥ የሞከረ ግለሠብ ያሉት አቶ ሽመልስ፤ እንዲህ ያሉግለሠቦች እየፈተፈቱ የሚያቀርቡለትን ነገር ሲፒጄ እየተቀበለ ያስተጋባል ብለዋል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በሠጡት አስተያየት፤ መንግስት ጋዜጠኞችን እንደሚያስርና እንደሚያንገላታ ለማረጋገጥ እስር ቤት ሄዶ ማየት ይቻላል ብለዋል፡፡

የታሠረ ጋዜጠኛ የለም እየተባለ መነገሩ የተለመደ ቀልድ ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፤ እነ እስክንድር፣ ውብሸት እና ርዕዮት በጋዜጠኝነታው እንጂ ሽጉጥ ሲሠርቁ አይደለም የታሠሩት ብለዋል፡፡ “ለመሆኑ እዚህ አገር ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገት ማህበር አለ እንዴ?” በማለት የጠየቁት ዶ/ር መረራ፤ “የነፃ ጋዜጦች እና የጋዜጠኞች ህልውና ከፖለቲካ ምህዳሩ ጋር አብሮ የተዳፈነ ነው” ብለዋል። የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ በበኩላቸው፤ ሲፔጂ መግለጫውን ሲያወጣ የራሱ መስፈርት እንዳለውና ዝም ብሎ እንደማይዘላብድ በመግለፅ፣ ሪፖርቱ ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ሃሣባቸውን በነፃነት የሚገልፁ ሠዎች በአደባባይ የሚሠቃዩባት፣ ጋዜጠኞች እስር ቤት የሚታጎሩባት ማተሚያ ቤቶች መንግስትን የሚተች ጋዜጣ አናትምም የሚሉባት፣ ጋዜጦች ተዘግተው ጋዜጠኞች የተሰደዱባት አገር መሆኗን በተጨባጭ እናውቃለን” ብለዋል አቶ ዳንኤል፡፡ የታሠሩት ጋዜጠኞች ከሙያው ጋር በተያያዘ አይደለም መባሉን እንደማይቀበሉት አቶ ዳንኤል ገልጸው፤ ከነፃው ፕሬስ ጀማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው እስክንድር ነጋ፤ ለሃሣብ ነፃነት የቆመ የመብት ተከራካሪ መሆኑ መታሠብ አለበት ብለዋል፡፡

Read 4544 times