Print this page
Saturday, 28 December 2013 11:48

“አመድ ሰፈር”ን ያስዋበው አሻም አፍሪካ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(11 votes)

ከአዲስ አበባ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና በሀይቅ በተከበበችው ቢሾፍቱ ከተማ፣ በቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ይገኛል - “አሻም አፍሪካ ሆቴልና ሪዞርት”፡፡ ሪዞርቱ የተገነባበት ቦታ ቀድሞ የከተማው ጠቅላላ ቆሻሻ መድፊያ ነበረ። በዚህም የተነሳ “አመድ ሰፈር” እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ዛሬ ግን ቦታው ለአይን ማራኪ በሆነው “አሻም አፍሪካ ሆቴልና ሪዞርት” ተተክቷል፡፡ እንደ ሪዞርቱ ባለቤት አቶ ሳህሉ ሃይሉ ገለፃ፤ ይህን ቦታ አፅድቶ እዚህ ለማድረስ 815 መኪና ቆሻሻ ማንሳት ነበረባቸው፡፡ ለዚህም የወጣው ወጪ ሌላ ግንባታ ይሰራ ነበር ብለዋል፡፡ “እውነት ለመናገር ቦታው የቆሻሻ መጣያ መሆኑን ባውቅ ኖሮ አልረከብም ነበር” ያሉት አቶ ሳህሉ፤ አሁን ያ ሁሉ ድካም አልፎ ለዚህ መድረሱ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡
“አሻም አፍሪካ ሆቴልና ሪዞርት” በቢሾፍቱ ሀይቅ ዙሪያ ከተገነቡት አምሳያዎቹ በብዙ ነገሮች ይለያል። ለምሳሌ ኤርትራን ጨምሮ በ32 የአፍሪካ አገሮች የተሰየሙ የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ በየአገራቱ ስም የተሰየሙት የመኝታ ክፍሎች የየአገራቱን ገፅታ የሚያንፀባርቁ ስዕሎች የተሰቀሉበት ሲሆን እስካሁንም 16ቱ የአፍሪካ አገራት በየመኝታ ክፍሎቹ የአገራቸውን መገለጫ ስዕል አስቀምጠዋል፡፡ ሌሎቹ 16ቱ አገራት ስማቸው ተፅፎ ያለቀ ሲሆን ቀስ በቀስም ስዕሎቻቸውን እንደሚያስገቡ ተገልጿል፡፡
40 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደወጣበት የተነገረው ሆቴልና ሪዞርቱ፤ የመኝታ ክፍሎቹን በአፍሪካ አገራት ስም ለምን መሰየም እንዳስፈለገ የተጠየቁት ባለቤቱ፤ ላለፉት 35 አመታት በአለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በሰሩበት ወቅት ከባለቤታቸው ጋር በርካታ የአፍሪካ አገራትን የመጐብኘትና የመኖር እድል እንዳጋጠማቸው ገልፀው፤ በኋላም እነዚህን አገሮች አንድ የሚያደርግ እና የሚያስተናግድ ሪዞርት ለመክፈት መምከራቸውን ይገልፃሉ፡፡
“ከስያሜ ባለፈ አንድ ኬኒያዊ እንግዳ በናይጄሪያ ስም የተሰየመ መኝታ ቤት ሲገባ፣ ስለ ናይጄሪያ የተለያዩ መረጃዎችን ያገኛል” ያሉት የ65 አመቱ አቶ ሳህሉ፤ በየአገራቱ ስም መሰየሙና የየአገሩ ስዕል በየመኝታ ቤቱ መሰቀሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያብራራሉ፡፡ የሆቴልና ሪዞርቱን ስያሜ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም “አሻም” የሚለው ቃል በሀዲይኛና በኦሮምኛ “እንኳን ደህና መጣችሁ” (Welcome) ማለት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
“አሻም አፍሪካ”ን ለየት ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል ከመታጠቢያ ክፍሎች፣ ከወጥ ቤትና ከሌሎች ክፍሎች የሚወጡ ፍሳሾችን በማጣራትና ሪሳይክል በማድረግ በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋሉ ሲሆን ከዚህም ባሻገር ለባዮ ጋዝነት በማዋል፣ በባዮ ጋዝ ምግብ እንደሚያበስል ለማወቅ ችለናል።
“ሪዞርቱ ሲገነባ አንዳንድ ዛፎችን የቆረጥን ቢሆንም 1ሺህ 500 ያህል ዛፎችን ተክለናል” ያሉት አቶ ሳህሉ፤ ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ሌላው አጃኢብ የሚያሰኘው እና አይንን የሚማርከው ከሆቴሉ የመኝታ ክፍሎች መካከል ለየት ባለ ሁኔታ የተገነቡ ክፍሎች መኖራቸው ነው። የውሀ ማሸጊያ ፕላስቲኮችን እንደ ብሎኬት እኩል በመደርደርና በሲሚንቶ በማያያዝ የተገነቡት የመኝታ ክፍሎች ውበት ግርምትን ይፈጥራል። “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ … ወዲህ ውበት ወዲህ ደግሞ አካባቢን መጠበቅ ድንቅ ነው፡፡ ሪዞርቱ የተገነባው በቢሾፍቱ ሀይቅ ዳርቻ ገደላማ ቦታ ላይ ነው፡፡  
አለታማውን ዳገት በረሃ ላይ የሚበቅሉ እና ስራቸው እምብዛም ወደ ውስጥ የማይዘልቅ የተለያዩ አበቦችን በመትከል፣ ግቢው ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ እንዲለብስና ማራኪ እንዲሆን ተደርጓል። በአጠቃላይ ከአካባቢና ከተፈጥሮ ጋር ህብር የፈጠረ ሆቴልና ሪዞርት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትልቅ ሬስቶራንት፣ 300 ሰው ማስተናገድ የሚችል የስብሰባ አዳራሽና ባሮችን ያካተተው አሻም አፍሪካ፤ ከ29 የአፍሪካ አገራት በተሰባሰቡ ስዕሎች የተሞላ ማራኪ አርት ጋለሪ ያካተተም ነው፡፡ ከመኪና ወርደው ገና ወደ እንግዳ መቀበያው ሲገቡ፣ እጅግ በርካታ የአፍሪካ አገራት የመገበያያ ብሮች ግድግዳው ላይ ተለጥፈው አይንን ይማርካሉ፡፡ የኢትዮጵያም ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋሉ የአስር፣ የሀምሳና የመቶ ብር ኖቶች ይገኙበታል፡፡
በአሜሪካ አገር ስሩ ሽቶና እጣን የሚሰራበት የሳር አይነት ከሪዞርቱ ግርጌ መጨረሻ ላይ ተተክሏል፡፡ ስሩ አምስት ሜትር ድረስ ወደ መሬት ይጠልቃል የተባለው ይሄው ሳር፤ አፈር በውሃና በንፋስ እንዳይሸረሸር በማድረግ ረገድ ወደር የለሽ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ከሆለታ ግብርና ምርምር አምጥተው እንደተከሉትም የ “አሻም አፍሪካ” ጠቅላላ አገልግሎት ኦፊሰርና የእለቱ አስጐብኚ አቶ ዳንኤል ግርማ ገልፀውልናል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ስራ ከጀመረ አንድ አመት ተኩል የሆነው “አሻም አፍሪካ”፤ ከ50 በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን  ከፈረንጆች አዲስ አመት በኋላ በይፋ ይመረቃልም ተብሏል፡፡
“እኔ ባለሀብት አይደለሁም፤ ሪዞርቱን የገነባሁት ከላይ እንደገለፅኩት አፍሪካን አንድ የሚያደርግና የሚያቀራርብ እንዲሆን ነው” ያሉት አቶ ሳህሉ፤ አብዛኛውን ወጪ ከባንክ በተገኘ ብድር መሸፈናቸውንና ብር ሲያገኙ ሲቀጥሉ፣ ብር ሲያጥራቸው ሲያቋርጡ ለግንባታው ወደ አምስት አመት ገደማ መውሰዱንም ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ የአፍሪካ ባህል፣ ገፅታ እና አጠቃላይ ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን በአንድ ቦታ የሚገኝበት አሻም አፍሪካን በመገንባቴ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፤ አቶ ሳህሉ ሀይሉ፡፡ 

Read 4985 times