Saturday, 28 December 2013 12:28

ሴትና ኪነት

Written by 
Rate this item
(18 votes)

እንደውሀ ሀሳብ እየወረድልኝ ድርሰት መፃፍ ህልም ሆኖብኛል፤በቃ መፃፍ አቅቶኛል! አንድ አመት. . . ሁለት አመት. . . ሶስት አመት. . አምስት አመት. . .  ሙሉ ጠበቅሁ፤  ምንም ነገር ብቅ አላለም- አንድ ገፅ ቃለ ተውኔት መፃፍ እንኳ አልቻልኩም!
ድርሰት መፃፍ አቅቶኝ ማዘኔ ሳያንስ የምወዳት ሚስቴ ሜላት መካሻ ጥላኝ ሔደች!
መለየት እንደዱብዳ ወረደብኝ፡፡ የመፃፍ ችሎታዬ ተሟጦ ከእንግዲህ  መፃፍ እንደማልችል በትያትር ቤት ገምጋሚዎች በተነገረኝ በሁለተኛው ወር ምሽት ላይ ወደቤቴ ስገባ ባለቤቴ ጥላኝ እንደሔደች ተነገረኝ፡፡ ኪነትና ሴት ተመካክረው እስኪመስል ከህይወቴ ሰተት ብለው ወጡ። ኪነትና ሴትን አንድ ላይ ማጣት ልቋቋመው የምችለው አልነበረም። መኖር ራሱ ከዚህ በኋላ ምን ያደርግልኛል? ሰው መኖር ያለበት በምክንያት ነው፡፡ የመኖር ምክንያቶቹ በሙሉ የተወሰዱበት ሰው መኖር ምን ያደርግለታል? ለኔ የመኖር ምክንያቶቼ የነበሩት ሴት እና ኪነት ናቸው. . .  ሁለቱን ከተነጠቅሁኝ በኋላ መኖር ከመተንፈስ የዘለለ አይሆንልኝም፡፡  
ሀያ ስምንት ተውኔት ከፃፍኩ በኋላ በድንገት የመፃፍ ኃይሌን ተቀማሁ፡፡ የመፃፍ ችሎታዬን እንደተነጠቅሁ የተረዳሁት ከግማሽ በላይ ቴአትሮቼን ላሳየሁበት ቴአትር ቤት ያስገባሁት የተውኔት ፅሁፍ በተደጋጋሚ ውድቅ ሲደረግ ነበር።  ለመጨረሻ ጊዜ ግምገማ ሲደረግ፤ ገምጋሚዎቹ የተውኔቱን ፅሁፍ ቀሽምነት የሚያሳዩ ነጥቦችን እያነሱ አስተያየት ሲሰጡ ተሸማቅቄ መግቢያ ሳጣ- በቃ መፃፍ እንደማልችል በግልፅ  ገብቶኝ ነበር።  “መፃፍ አለመቻል ማለት የህይወት መጨረሻ አይደለም!” ብዬ ነበር ለራሴ ደጋግሜ የነገርኩት፡፡
ተሳስቼ ነበር፡፡ መፃፍ ለኔ ህይወት ነበር፡፡ ቃላትን መደርደር የህይወት ምልልሴ ነበር፡፡ ድርሰት ከመፃፍ ውጪ ጫማ ማሰር እንኳ አልችልም፡፡ የተወለድኩት እንድፅፍ ነበር የሚመስለኝ፡፡ በድንገት ግን ብዕሬ አልታዘዝ አለኝ፤ቃላት እንደሰማይ ራቁኝ። ለማን አቤት እንደምል አላውቅም. . . . . .
የመጨረሻውን ቴያትሬን ለግምገማ ሳቀርብ የመሞት ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ከተውኔት ግምገማው ቢሮ ስወጣ ውስጤ ጭር ብሎ ነበር። በቁሜ የተገነዝኩ ያህል፣የራሴን የቀብር ንፍሮ የቀመስኩ ያህል . . . ድንጋጤ አቅሌን ሰውሮ ጭልም እንዳለብኝ ----ምን ነበር የቴያትር ገምገሚው ያለኝ? የቴያትር ገምጋሚው ንግግር በአእምሮዬ ደጋግሞ ያቃጭልብኛል፡፡ እስከ ህልፈተ ህይወቴ ድረስ በህሊናዬ የሚቀመጥ ንግግር ነበር የተናገረው፡፡
“ህሩይ እርግጠኛ ነህ ይህንን ጽሁፍ አንተ ለመፃፍህ?” ነበር ያለኝ ባለማመን፡፡ በአንገቴ ንቅናቄ ማረጋገጫዬን እንዳገኘ ወደኔ አፍጥጦ እያየ. . .
“ህሩይ ይህ ግምገማ በሁለት አመት ውስጥ ስድስተኛ  ሥራህ ላይ ያደረግነው ነው፡፡ አይገባህም እንዴ? በቃ! የጥበብ አድባር ርቃሀለች! መክሊትህን ጨርሰሀል! እስካሁን በሰራኸቸው እና ተመልካችን አጀብ ባሰኙ ሥራዎችህ እየታወስክ ትኖራለህ፡፡ ከእንግዲህ ግን ሙያ ቀይር! ለወጣቶቹ እድል ስጥ!” ሲል  የራሴን መርዶ ለራሴ ነገረኝ፡፡ ሀያ ስምንት ተውኔቶች ተለምኜ በፃፍኩበት መድረክ ላይ አንድ የሚበቃ ሥራ ማቅረብ አቃተኝ! ኪነት ጨርቄን ማቄን ሳትል ጣጥላኝ ሔዳለች. . . . .እብስ!
እውነቱን ስላላመንኩት ነው እንጂ በቃ መጻፍ አልችልም! አልችልም! አልችልም! ቃላት ያጎርፍልኝ የነበረው ምናቤ ሞቷል!
ለሀያ ምናምን ዓመት ያለማቋረጥ የሰራሁት ሥራ መፃፍ ነው! መፃፍ! መፃፍ! በቃላት ነፍስ መዝራት፤ በቃላት ህይወት መዝራት፤ ከህይወት ህይወትን ቀድቼ ህይወት ላላቸው ህይወትን ማጠጣት፡፡ አሁን ግን የህይወት ምንጬ ደረቀ፡፡ የፈጣሪነት ሚናዬን ተቀምቻለሁ!  ሥራዬ መፍጠር ነበር፡፡ ህይወቴ መፍጠር ነበር፡፡ ነበር፣ነበር፣ነበር. . . . . !!! አንድ የሚረባ ፅሁፍ መፃፍ አቅቶኝ አምስት አመት ተቆጠረ፡፡ መፃፍ እችላለሁ የሚለውን እምነት ይዤ ለአምስት አመት ታገልኩ. . .በቃ መፃፍ አቅቶኛል!
አእምሮዬ ድንገት እንደ ሻተር ዝግት አለ! በፊት በፊት ድርሰት እንዴት ነው የሚመጣልህ? ብለው ሲጠይቁኝ እስቅ ነበር- የአለቃ ገብረሀናን አሽሙር እንደሰማሁ፣የቻርልስ ቻፕሊንን ድምፅ አልባ ቧልት እንዳየሁ ሁሉ በሳቅ ፍርስ እል ነበር፡፡ በምድር ላይ ቀላሉ ሥራ በቃላት ሰዎችን መፍጠር፣እንዲናገሩ ፣እንዲያዝኑ ማድረግ ይመስለኝ ነበር፡፡ ሀያ ስምንቱም ተውኔቶቼ የተዋጣላቸው የሚባሉ ነበሩ፡፡ አምስት አመቴ! ቃላት ከአእምሮዬ መፍለቅ ካቆሙ፣ ቢፈልቁም ጣዕም አልባ ደረቅ ቃላት ናቸው፤ታሪክ በጣቴ በኩል አይመጣም፣ ታሪክ ብዬ የምፅፈው ከተራ ዝብዘባ ያነሰ ነው፡፡ በቃ መፃፍ አልችልም!!
አንድ የማላውቀው ኃይል የድርሰት አቅሜን ነጥቆኛል፡፡ የት ሔጄ አቤት እላለሁ? የትኛው ፍርድ ቤት ይግባኜን ይሰማኛል?
ስለማያስችለኝ ከቴያትር ቤቱ ደጃፍ ላይ ሔጄ ቁጭ እላለሁ፡፡ ከየት መጣ ያላልኩት እንባ አይኔን እየበረቀሰው ወደ ጉንጬ ይንፎለፎላል፡፡ ሰዓሊ ብሩሹ ሲደርቅ፣ቀራፂ መዶሻው ሲወልቅ. . . ምን ይላል? . . . ዘፋኝ ድምፁ ሲጎረንን፣ዳንኪረኛ እግሩ ሲሰበር. . . .  ምን ይሆን የሚሰሩት? እኔ ግን ግራ ገብቶኛል! ህይወት ትርጉም አጥታብኛለች፡፡ ስፅፍ እንዴት ደስተኛ ነበርኩ! ስፅፍ እንዴት ሀሴት አደርግ ነበር!. . . . ንስር የሆንኩ ይመስለኝ ነበር፤ሰማየ ሰማያት በርሬ ቁልቁል ዓለምን ሙሉ የምቃኝ ይመስለኛል፡፡ ሥነ-ፅሁፍ ነፃነቴ ነበር፣ ሥነ-ጽሁፍ ቁልፌ ነበር ከተዘጋ የአስተሳሰብ ሳጥን የምከፈትበት. . . . ሥነ-ፅሁፍ ማዕረጌ ነበር የምጠራበት. . .
የመጨረሻ የተውኔት ፅሁፌ በግምገማ እንዲያልፍልኝ ክፉኛ እንደተመኘሁ ትዝ ይለኛል፡፡ እናቴ በጠና በመታመሟ  ገንዘብ ማግኘት ነበረብኝ። የቤት ኪራይ አለ፣ፋሲካ እየደረሰ ነው. . . ገንዘብ ግን የለኝም ነበር፡፡ ገንዘብ እንዳገኝ የተውኔት ፅሁፍ አዘጋጅቼ ለቴያትር ቤቱ አስገባሁ፡፡ በግምገማ ቅስሜን እንደእንስራ ሰበሩት. . . .ይህ ሁሉ ጫና ኖሮብኝ ከኪነት እና ከሴት አንደኛቸው አብረውኝ ካሉ ጭንቅ አጠገቤ አይደርስም ነበር፡፡ ኪነት እና ሴት በአንድነት ሲርቁኝ ግን. . . .የጨለማ ግድግዳ የከበበኝ ይመስለኛል፡፡
በአንድ ተውኔቴ ውስጥ “ማበድ ሲያንሰኝ ነው!” የሚል ገፀ ባህሪ አለ፡፡ የመፅሀፍ ቅዱሱ ኢዮብን አይነት መከራ የሚደርስበት ይኼ ገፀ ባህሪዬ፤ በመጨረሻ የዓለምን ስቃይ መቋቋም አቅቶት አቅሉን ይስታል-ያብዳል፡፡ ካበደ በኋላ ማበዱን የሚያሞካሽበት ቃለተውኔት አለ።  “ባላብድ ይገርመኝ ነበር! ማበድ ሲያንሰኝ ነው!” ይላል ይህ ገፀ ባህሪዬ፡፡ “እንኳን አበድኩ! በጤነኛ አእምሮዬ ይህንን ሁሉ መከራ አልችለውም ነበር!” ይላል። የራሴን ህይወት እየተነበይኩ ነበር ማለት ነው። አንዴት አንድ የተሳካ ተውኔት መፃፍ ያቅተኛል? ማበድ ሲያንሰኝ ነው! ባብድ ይሻል ይሆን? እብደትን ተመኘሁ. . . .
ከድርሰት ውጪ ሰርቼ ገንዘብ ያገኘሁበት ሥራ ኖሮ አያውቅም! ስለዚህ ዓለም ያለጀንበር መኖር የጀመረች መሰለኝ. . . . .ጨለማ!
የመጨረሻ ተውኔቴ በግምገማ ከወደቀ በኋላ መጠጥ መቀማመስ አዘውትሬ ነበር፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ የተለመደውን አድርሼ ወደ ቤቴ አቅጣጫ ጉዞ የጀመርኩት. . . . .
11፡00 ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት የሚመለሱበት፣ ፀሀይዋ መስከን የምትጀምርበት፣ሠራተኞች ከሥራ ወደ ቤት የሚቻኮሉበት. . . ጓዳናው ላይ ሰው የሚፈስበት የምወደው ሰዓት ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ጎዳና ላይ መውጣት የድርሰት አምሮቴን ይቀሰቅሰው ነበር። ሰውን የማንበብ ሱስ ነበረብኝ፡፡ ብዙ አይነት ፊቶችን ማንበብ እወድ ነበር... የተከፋ፣ የደነገጠ፣ የተደሰተ፣ የተኮሳተረ፣ የፈገገ፣ የሚቸኩል፣ የተናደደ፣ ተስፋየቆረጠ፣ የተቆጣ፣ የተራበ፣ የተፀፀተ ፊት...፤ በፂም የተከበበ፣ በመነፅር የተጋረደ ፊት፤ ሾካካ፣ መልከቀና፣ የዋህ፣ ጅላጅል ፊት. . . .እነዚህን ፊቶች ማየት ነበር የቃላት ክምር፣ የዓረፍተ ነገር ቋጥኝ ወደ አእምሮዬ የሚያንደረድረው፡፡
ምን ሆኖ  ይሆን ያዘነው? ምን ሆና ይሆን የምትስቀው? ለምን ተፀፀተ?. . .እያልኩ የሰዎችን ፊት ካየሁ በኋላ. . . ወደ መመሰጤ እመጣለሁ --- የፈጠራ ሀሳቦች እየተንከባለሉ ወደ አእምሮዬ ዘው ይሉ ነበር፡፡ የሰው ፊት ነበር መጽሀፌ! የተገለጠ፣ያልተደበቀ፣በብራና ያልተለበጠ፣ነፍስ ያለው መፅሀፍ --- የሰው ልጅ ፊት! እነዚህ ሁሉ ትርጉም ከሰጡኝ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሰው ፊት ሳይ አፍንጫ እና አይን፣ቅንድብና ጉንጭ፣ከንፈር እና ግንባር. . . ወዘተ ብቻ ናቸው የሚታዩኝ፡፡ ከዛ ውስጥ ያለው የሰው ልጅ ማንነት አይታየኝም. . .ምናቤን ተነጥቄያለሁና፡፡
መፃፍ አቅቶኛል! በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ወደ ቤቴ እየሄድኩ ነበር፡፡ በመንገዴ ሙሉ የማስበው ስለተለየችኝ  ኪነት ነበር፡፡ ሚስቴ ያኔ አብራኝ ስለነበረች የኪነትን እጦት መፅናኛዬ እሷ ነበረች፡፡ እሷ ጋ እስክደርስ ግን ስለኪነት አስብ ነበር. . . .
መፍጠር መቻል የሚያስገኘው ደስታን ምናልባት የወለደ ብቻ ያውቀው ይሆናል፡፡ መፃፍ ደግሞ ከዚያ ይበልጣል፡፡ የተወለደ ልጅ ነፍስ ካወቀ በኋላ የራሱን የህይወት ትልም እራሱ ነው የሚኖረው። አማልክቱ ናቸው የተወለደ ልጅን እጣ ፈንታ የሚወስኑት፡፡ በድርሰት ግን ከዚያ በላይ መብት አለ፡፡ ገጸ ባህሪን መውለድ ብቻ ሳይሆን ጥሩና መጥፎ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ጥቁር አለያም ቀይ የፊት ቀለም መሥጠት ይቻላል፡፡ የፈጠሩትን ገጸባህሪ እንዲሳካለት ማድረግ ይቻላል፡፡ ደራሲነት የአማልክትን እጣ ፈንታ መጋራት ነው፡፡ እስካሁን ከነበሩ ወላድ እናቶች መካከል የልጁን አንድ ስንዝር አፍንጫ ቁመት የጨመረ የለም፡፡ በድርሰት ውስጥ ግን እነዚህ ሁሉ ይቻላሉ፡፡ የሳምሶን ኃይል ፀጉሩ ውስጥ ነበር፤ የጸሀፊ ደግሞ ምናቡ ውስጥ፡፡ ምናቤን ተቀምቻለሁ. . . በቃ ከእንግዲህ መጻፍ አልችልም!
ይኼን እያሰብኩ ቁልቁል ወደ አትክልት ተራ አቅጣጫ መጓዜን ቀጠልኩ፡፡ ከኋላዬ የሁለት ወጣት ልጃገረዶች ሹክሹክታ ይሰማኝ ነበር፡፡
“አየሽው! ህሩይ ማለት እኮ እሱ ነው፡፡ የዛሬ አምስት አመት በቴሌቪዥን ይታይ የነበረው የህልም ዓለም ሰዎች የሚለውን ድራማ አስታወስሽ? የሱ ደራሲ እኮ ነው፡፡” አለች ተለቅ የምትለው፡፡ የህልም ዓለም ሰዎች በሚል የፃፍኩት ድራማ በጣም ታዋቂ ነበር፡፡
“አረ እኔ አላውቀውም!” አለች አነስ የምትለው
“በተደጋጋሚ መፅሔት ላይ ይወጣ ነበር እኮ! ብዙ ቴያትር ፅፏል!. . .”ትልቅየው ልታስረዳት ሞከረች፡፡
ዞር ብዬ አየኋቸው፡፡ ትልቋ አስራ ስምንት፣ትንሷ ደግሞ አስራ ሁለት አመት ቢሆናቸው ነው፡፡ ትልቋ በአውቅሀለው ስሜት ፈገግ አለችልኝ. . . ትንሷ ደግሞ በእንግዳ ስሜት አየችኝ፡፡ ደነገጥኩ! ለአዲሱ ትውልድ የሚሆን ሥራ የለኝም! በቃ እኔ ታሪክ ነኝ!. .. መፃፍ አልችልም፡፡ ልጆቹን ትቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ከሸዋ ሱፐር ማርኬት በሶማሌ ተራ አድርጌ፣ ወደ ሰፈሬ ወደ አሜሪካን ግቢ እስክደርስ ድረስ የሚራመድ ግዑዝ አካል ሆኜ ነበር፡፡ ለወትሮው አሜሪካን ግቢ ስደርስ የሚሰማኝ ሰላም አብሮኝ አልነበረም። የአሜሪካን ግቢ ግርግር፣ልባሽ ጨርቅ የሚሸጡ ወጣቶች ውርውርታ፣በትንንሽ ፔርሙዝ ቡና የሚሸጡ ሴቶች፣የወደቀ የጫት ገረባ የሚበላ ፍየል፣ከመስጂድ የሚመለሱ አባት፣መኪና ላይ የሚጫን ካርቶን፣ ረጅም የብረት ቱቦ በትከሻው ተሸክሞ ”ዞር በሉ! ዞር በሉ!” እያለ የሚያስጠነቅቅ ወጣት፣የተደረደሩ የሊስትሮ ዕቃዎች፣የመስጅድ አዛን፣የራጉኤል ቅዳሴ. . . .አሜሪካን ግቢ የሰው እርሻ ነች፣ሰው ግጥግጥ ተደርጎ የተዘራባት የመርካቶ አዝመራ! አሜሪካን ግቢ የድርሰት ሀድራዬ ነበረች። ሰው ሰው የሚሸት ትንፋሽ የምታሸተኝ. . . ሰው ሰው የሚል ስሜት እንዲሰማኝ የምታደርግ. . . . ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን አሜሪካን ግቢ እነዚህን ሁሉ አትሰጠኝም! የማየው ተራ ግርግር ነው! የሰዎች ትርምስ - ምክንያቱም ምናቤን ተቀምቻለሁ!
እንዲህ እያሰብኩ ስሔድ. . . . ከኋላዬ ድምፅ ሰማሁ.. .
“ህሩይ!” ወደ መንደራችን መግቢያ መንገድ ጫፍ ላይ ካለው ሱቅ የተሰማ ድምፅ ነበር-የበድሩ ድምፅ። በተረቡ፣በቀልዱ፣በጨዋታው ቀኔን የሚባርክልኝ በድሩ። መከፋቴን ላጋባበት አልፈለግሁም- ዝም ብዬ ወደ ቤቴ አቅጣጫ መጓዜን ቀጠልኩ፡፡
“ህሩይ ፈልጌህ ነው!” በድሩ ተከትሎኝ ነበር፡፡ አጠገቤ ደርሶ ሁኔታዬን ሲያየው ደስ አላለውም፡፡
“ምን ሆነሀል ህሩይ?” በተጨነቀ ስሜት አስተዋለኝ። ምን ሆንኩ እለዋለሁ? ተዘረፍኩ ልበለው? የመፃፍ አቅሜ ተሟጠጠ፣ቃላት አውላላ ሜዳ ላይ ጥለውኝ እብስ አሉ!.. .ሊገባው አይችልም። እንኳን እሱ የገዛ ጓደኞቼ ችግሬን አውቀውት ምን ፈየዱልኝ?  “ you know what has happened to you? It is a writer’s block. ” እያሉ ለገጠመኝ ጉድ ገለፃ ለመስጠት ነው የሚሞክሩት፡፡ “አሜሪካዊው ደራሲ ፍራንሲስ ስኮት በዚህ በሽታ ይሰቃይ ነበር..   The love of the last tycoon የሚል ድርሰት ጀምሮ እስከህይወቱ ፍፃሜ ሳይጨርሰው ነው የሞተው...” ምናምን እያሉ ነገር ያራቅቃሉ።  እኔ የማውቀው ደስታዬን መነጠቄን ነው! የፀሀፊ መዘጋት የሚባል በሽታ እንደያዘኝ ማወቁ ሳይሆን መድሀኒቱን ነበር የምፈልገው፡፡ ከቃላት የማገኘውን ደስታ ድጋሚ ማግኘት የምችልበትን መንገድ! “ሶደሬ ለሁለት ሳምንት ተዝናና! ወደ ውጪ ሀገር ለምን ቫኬሽን አትወጣም?. . .” የአንዳንድ ሰዎች ምክር ነበር፤በሽታዬ እንዲለቀኝ፡፡ እኔ ግን ደራሲ ነኝ. . . ሶደሬ ለሁለት ሳምንት የሚያስኬድ ገንዘብ ብይዝ እናቴን ነበር የማሳክምበት፡፡
“ባክህ ተወኝ በድሩ! ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም!” አልኩት፡፡
አንድ ነገር  ሊነግረኝ እንደፈለገ ሲያመነታ ቆየና በእሺታ አንገቱን ነቅንቆ ትቶኝ ሔደ፡፡
ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ቤት ውስጥ ማንም የለም ነበር፡፡
“ሜላት?” የባለቤቴን ስም ደጋግሜ ጠራሁ፡፡ ምላሽ የለም!
የት ሔደች? ሜላት ከሌለች ቤቱ ሊበላኝ ይደርሳል፡፡ ሜላት ባትኖር በነዚህ አምስት አመታት ውስጥ ምን ልሆን እችል እንደነበር ማሰብ ይከብዳል፡፡ የብዙ ነገር መፅናኛዬ ሜላት ናት! እና እሷን ፈለግሁ. .  የት ሔዳ ነው? በእቅፏ ውስጥ ሆኜ ተስፋ መቁረጤን መርሳት ሻትኩ፣በእቅፏ ውስጥ ሆኜ ዓለምን መርሳት፣በእቅፏ ውስጥ ሆኜ ነገን መርሳት. . .ሜላት የመድሀኒት ያህል ናት ለኔ። በጡቶቿ መካከል አስገብታ፣ በጭኖቿ ደግፋ፣ በተስፋ መቁረጥ የደረሰብኝን ሀዘን የምታስረሳኝ መድሀኒቴ፡፡ . . .እና ክፉኛ ፈለግኋት. . . .
ወደ ሞባይሏ ስደውል ተዘግቷል የሚል ምላሽ አሰማኝ፡፡ በድሩ ትዝ አለኝ፡፡ እሱ ጋ መልዕክት አስቀምጣ ይሆናል፡፡ ወደ በድሩ ሱቅ ፈጠን ብዬ ሔድኩ፡፡
“ህሩይ እንኳን መጣህ! ቤት ልመጣ እያሰብኩ ነበር --- ሜላት መልዕክት ነግራኝ ነበር. . .እዚህ ቆመን ከሚሆን ሻይ ቤት ምናምን ሔደን. . . !” አለኝ። በድሩ ከበድ ያለ ጉዳይ ሲጋጥመው “ሻይ ቤት ሔደን እናውራ” የሚል ልማድ አለው፡፡
“በጣም እቸኩላለሁ! የምን መልዕክት ነው አንተ ጋ ያስቀመጠችው?”  አልኩት ነገሩን ለመስማት ጓጉቼ፡፡
“ትንሽ ጥሩ ነገር አይመስለኝም!. . . . . .” አለና በድሩ አቀርቅሮ ሲያስብ ቆየ፡፡ የፊቱን ጭንቀት ሳይ አንድ ጥሩ ያልሆነ ነገር እንዳለ ገመትኩ፡፡
“ግዴለም ንገረኝ ምንድነው? ሜላት ደህና አይደለችም እንዴ?” አልኩት
“ሜላት ሔዳለች ህሩይ!” አለኝ አንገቱን እንዳቀረቀረ
“የት ነው የሔደችው?”
“የት እንደሄደች ባላውቅም ምናልባት ወደ ክፍለ ሀገር እንደሔደች እገምታለሁ!”
“ለምንድነው የሄደችው? አልነገረችኝም እኮ!. . ” በቁጣ ጠየቅሁት
“አልገባህም ማለት ነው ህሩይ! ጥላህ ሔዳለች እያልኩህ ነው! . . . ላትመለስ ሔዳለች እያልኩህ ነው...” በድሩ እንደእድር ጥሩንባ ነፊ ሞቴን ያወጀ መሰለኝ፤ ከዛ በኋላ ያለውን ንግግሩን አልሰማሁትም። ውስጤ የነበረው ባዶነት እንደጥቁር አዘቅት blackhole/ ጥልቅ ሲሆን ይታወቀኛል- ወሰን አልባ ባዶነት!  
እንደቀፎ ባዶ የሆነ አካሌን እየጎተትኩ ወደ ቤቴ ነበር የተመለስኩት፡፡
ሜላት የወትሮ ፉከራዋ ጥዬህ እሔዳለው የሚል ነበር፡፡ ጨክና ታደርገዋለች የሚል እምነት ግን አልነበረኝም! ፈፅሞ!
ለብዙ ዘመን ፅሁፌ ላይ አተኩሬ ለሴት ልጅ የሚሆን ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ሜላትን ካየኋት በኋላ ግን የሴትን ልጅ ውበት ችላ ማለቴን መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ውድድ! አደረኳት፡፡ ጓደኞቼ እንኳን “ለረጅም ጊዜ አንድም ሴት ሳታፈቅር የቆየህበትን ጊዜ ለማካካስ ይመስላል” እያሉ ለእሷ ባለኝ ፍቅር ላይ ይቀልዱ ነበር፡፡ እንዲህ እንደምወዳት እያወቀች እንዴት ጥላኝ ትሔዳለች?
“ጠብ የሚል ነገር ለሌለው ለምን ጊዜህን እና ጉልበትህን ታጠፋለህ? ሌላ ሥራ ሞክር! መቀየር አለብን፣መሻሻል አለብን. . . ” ከተጋባን ጀምሮ እንዲህ ነበር የምትለኝ ሜላት፡፡  የእኔ ትልቁ መለያ ደግሞ ለሥጋ ማሰብ አለመቻሌ ነው፡፡ ካልሲ እንኳን ገዝቼ መቀየር የሚከብደኝ አይነት ሰው ነበርኩ፡፡ ሜላት ደግሞ የኔ ተቃራኒ ነበረች። የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ትወዳለች፡፡ አዲስ የቤት ዕቃ፣መኪና፣የራሳችን ቤት. . .ቢኖረን የደስታዋ ምንጭ ነው፡፡ ለሷ ስል የቲያትር ቤቶችን መድረክ የሚነቀንቅ ተውኔት ለመፃፍ ደጋግሜ ሞከርኩ. . .ግን አልሆነም! በትዳር በቆየንባቸው አምስት አመታት አብዛኛው የቤት ወጪ የሚሸፈነው ሜላት ሰርታ በምታመጣው ገንዘብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሔዳለች . . . .
በቃ ተሸነፍኩ! ሴትንም ኪነትንም በተከታታይ ማጣት ይከብዳል፡፡ የሁለቱም ፍቅር ገላንም ነፍስንም የሚያነድ፣የሚያንገበግብ አቅም ነበረው... “ማበድ ሲያንሰኝ ነው!” የሚለው ገፀ ባህሪዬ እያሽካካ የሚያየኝ ይመስለኛል፡፡ ኪነትንም ሴትንም በተከታታይ እንዳጡ ማወቅ ከባድ ነው. . . .ሴትና ኪነት ኪነትና ሴት. . . . .
ሜላት ጥላኝ እንደሄደች ካወቅሁ በኋላ ነገር ዓለሙ ዞረብኝ፡፡
ጥላኝ በሔደች በሶስተኛው ሳምንት አንድ ተአምር ተፈጠረ፡፡ እስከ ውድቅት ድረስ የቤቴን በር ሳልዘጋ በጨለማ ውስጥ በተቀመጥኩበት፤ ተስፋ መቁረጥ፣ብቸኝነት፣ባዶነት፣መሸነፍ. . . ዙሪያዬን እንደጥንብ አንሳ ይዞሩኝ በጀመሩበት አንድ ተአምር ተከሰተ፡፡ ሴት ብቸኝነትን ማርካ የምትገድል ብርቱ ጦረኛ ኖራለች? እያልኩ ሜላትን ክፉኛ በምፈልግበት ወቅት ተአምሩ መጣ፡፡ ሜላት መሸነፌን የምደበቅባት፣ተስፋ መቁረጤን የምከልልባት ስጦታዬ ነበረች፡፡ ሜላት!ሜላት!ሜላት! ብቸኝነት እንደ ውርጭ ነፍሴን አቆረፈዳት. .  ተስፋ መቁረጤን ማስተንፈሻ ፈለግሁ. . . ሜላት ስላልነበረች ሌላ አማራጭ መፈለግ ነበረብኝ. . .
ለሰአታት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መብራቱን አበራሁ፡፡ ከአልጋው አጠገብ ካለች አነስተኛ ጠረጴዛ ላይ ልሙጥ ነጭ ወረቀት ተቀምጧል፡፡ መፃፊያ እርሳሴን አነሳሁ. . . .
“ባዶ ቤት! ” የሚል ርዕስ ከአእምሮዬ ተስፈንጥሮ ወጣ. . . . . . .
እስኪነጋ ድረስ ከተቀመጥኩበት አልተነሳሁም። ሀሳብ እንደ ጢስ አባይ ፏፏቴ እየተንዶሎዶለ ይጎርፍልኝ ጀመር፡፡ ሁሉን አጣሁ ባልኩበት ሰዓት ኪነት አለሁ ማለቷን ማመን አልቻልኩም፡፡ ለሊቱ ተገባዶ በንጋት ሲተካ በማያቋርጥ የምናብ ጉዞ ላይ ነበርኩ. . .እስከረፋዱ ድረስ ስፅፍ ቆየሁ፡፡ በሰው ተከቦ ብቸኝነት የሚሰማውን አንድ ገፀ ባህሪን መሰረት አድርጎ የሚሔድ የተውኔት ፅሁፍ ነበር፡፡  
እያንዳንዷ ቃል ውስጤን ጠርምሳ ስትወጣ ይታወቀኛል. . . . .በቃ! ከአምስት አመት በፊት እንደነበረው! . . . .የሚወጡት ቃላት እስኪገርሙኝ ድረስ፣የሚፈጠሩት ታሪኮች እስኪያስደምሙኝ ድረስ... .እየፃፍኩት የምጓጓለት ፍሰት ነበረው፡፡ የተሳካ ሥራ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እራሴን በመጀመሪያ ያረካኝ ሥራ በግምገማ ፈፅሞ ወድቆ አያውቅም. . . አምስት አመት ሙሉ ያጣሁት ይኼንን ነበር፡፡ ሀያ ስምንት የመድረክ ጽሁፎቼን ስፅፍ የነበረኝ ስሜት እንደተመለሰ ገብቶኛል፡፡
“ተመልሻለሁ!” ብዬ መጮህ አማረኝ! ወይም እንደአርኬሜደስ “ዩሪካ! ተገኝቷል!” እያልኩ በአሜሪካን ግቢ ውስጣ ውስጥ ሰፈሮች፣በወለኔ ግቢ፣በወልደጋግሬ ግቢ፣በጎርዶሜ ወንዝ፣በጌሾ ጊቢ፣በአባኮራን ሰፈር... ብሮጥ በወደድኩ፡፡ መፃፍ፣መፃፍ. . በቃላት ዓለምን መበርበር. . .
ረፋዱ ላይ ትንሽ ድካም ተሰማኝ፡፡ ከድካሜ በላይ ግን የፃፍኩትን ሳይ ማመን አቃተኝ፡፡ ሀያ አምስት ገፅ ያለምንም ስርዝ ድልዝ ፅፌያለሁ፡፡ በዚሁ ፍጥነት ከሔድኩ በሁለት ቀን ውስጥ የተውኔቱን ፅሁፍ ልጨርስ እችላለሁ፡፡ የማይታመን ነገር ነው! ለእናቴ መታከሚያ ገንዘብ እንደማገኝ ሳስብ ደስታ ሰውነቴን ወረረው፡፡ ጽሁፉን አለፍ አለፍ እያልኩ አነበብኩት. . .አምስት አመት ሙሉ የቆየሁት እንዲህ አይነት ፅሁፍ ለመፃፍ ነበር!
አምስት አመት ሙሉ ግን የት ነበርኩ? እንደ ካዝና ቁልፍ የተዘጋብኝ የኪነት መንገድ እንዴት ሊከፈት ቻለ? እንቆቅልሹ ቅርፅ እየያዘልኝ ሲመጣ አንዳች አስደንጋጭ እውነት ውስጤ ዱብ አለ! ሜላትን ካገባሁ- አምስት አመቴ! የተውኔት ፅሁፍ መፃፍ ካቃተኝ አምስት አመት!
የመፃፍ አቅሜ ጥሎኝ የሔደው ሜላትን መከተል ስጀምር ነበር ማለት ነው! ከሜላት ጋር ከተጋባን ጀምሮ አንድ ተውኔትም ቢሆን መፃፍ አቅቶኛል! እውነቱ ይህ ነበር፡፡ ፈጽሞ ልረዳው ያልቻልኩት እውነት. . . ሜላትን ከማግባቴ በፊት ለረጅም አመት ብቻዬን ነበር የኖርኩት -በወንደላጤነት፡፡ ብሶቴን፣ንዴቴን፣ተስፋ መቁረጤን፣ጉጉቴን የምተነፍሰው በጽሁፍ ነበር፡፡ ኪነት መተንፈሻዬ ነበረች. . . ሜላትን ካገባሁ በኋላ ግን የኪነትን ቦታ ምህረት ወሰደች፡፡ ተስፋ ስቆርጥ በምህረት እቅፍ ውስጥ መግባትን እመርጣለሁ. . . . . ነፍሴ የምትተነፍሰው በሴት እና በኪነት በኩል ነው ማለት ነው. . . . አንደኛዋ ስትመጣ ሌላኛዋ ትሔዳለች. . .ሌላኛዋ ስትሔድ አንደኛዋ ትመጣለች. . . .እኩል መሔድ አይችሉም፡፡ ሁለቱም ሀሳብ ይፈልጋሉ፣ሁለቱም ውበት ይፈልጋሉ፣ሁለቱም ቀናተኞች ናቸው. . ሁለቱም ይናጠቃሉ!
ሜላት ስትሔድ ኪነት መጣች. . . . .
ሜላትን መቼም ማጣት የምፈልግ አይመስለኝም። እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ሔጄም ቢሆን የምፈልጋት ይመስለኛል. . . ለጊዜው ግን ተውኔቱን መጨረስ አለብኝ። ለእናቴ መታከሚያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ቅድሚያ የምሰጠው ተግባር ነበር፡፡ወደ ውጪ መውጣቴን ትቼ የተውኔት ጽሁፌን ቀጠልኩ፡፡ ለግማሽ ሰአት ያህል ሀሳቤ ሳይደናቀፍ ስጽፍ እንደቆየሁ የውጪው በር ሲከፈት ተሰማኝ፡፡ ማን እንደመጣ ለማየት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ በሩ እየሄድኩ ሳለ አንድ ሰው ወደ ቤት ውስጥ ገባ- ሜላት መካሻ!
ክው ብዬ ቀረሁ! መፃፊያ ብዕሬ ከእጄ ወደቀ፡፡
ሜላት በቆመችበት እንባዋ በጉንጮቿ እየወረደ በሳግ በታፈነ ድምፅ “አልቻልኩም! ምንም ሳታደርገኝ ጨክኜ ጥዬህ ልሔድ አልቻልኩም!” አለችኝ፡፡ ሜላት ተመልሳ ነበር፡፡ ከሶስት ሳምንት በኋላ . . . .
ተሸክማው የነበረውን የልብስ ሻንጣ ተቀበልኳትና ወደ ጓዳ አስገባሁት፤በቆመችበት ጥምጥም አድርጌ አቀፍኳት፡፡ በከንፈሮቼ እንባዋን መጠጥኩት፤ በከንፈሮቿ ሳመችኝ፡፡ እጅግ አድርጋ ናፍቃኝ ነበር፡፡ ሰውነቴ እንደመንቀጥቀጥ እያደረገው ተንሰፈሰፈ፡፡ ወደ አልጋው ተሸክሚያት ሔድኩ. . . . ልብሷን እስክታወልቅ ትዕግስት አልነበረኝም፤በጭኖቿ ውስጥ ለመደበቅ ተቻኮልኩ፡፡
“እወድሀለው! እወድሀለው!” የሚል ለሆሳስ ቃል ሜላት ታሰማለች፡፡ከገላዋ ተጣብቄ “እኔም እወድሻለሁ!” እላለሁ. . . .የኔ ሴት ሆይ እወድሻለሁ! ላንቺ ያለኝ መውደድ በመስዋዕት የታጀበ ነው፡፡ እናቴን እና ኪነትን መስዋዕት የሚያደርግ መውደድ. . .
ከሴትና ከኪነት ሴትን መርጫለሁ! ሴትን ስመርጥ ደግሞ ሌላ ሴትን አጥቻለሁ. . . . . ሴትና ኪነት፣ ኪነትና ሴት. . . .

Read 4666 times