Saturday, 04 January 2014 10:16

የእነ አቶ ቃሲም ፊጤ ክስ ተሻሽሎ ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

• የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተቀጥሯል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፍቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ እና በባልደረቦቻቸው ላይ አቃቤ ህግ ከፍ/ቤቱ በታዘዘው መሠረት ክሱን አሻሽሎ አቀረበ፡፡ ቀደም ሲል የቀረበው ክስ አቶ ቃሲም ፊጤ፣ የምርመራና ክስ ኤክስፐርቱ አቶ ተስፋዬ ዘመድኩን፣ የሊዝ አሰባሰብ ክትትል ኦፊሰሩ አቶ ገ/የሱስ ኪዳኔ እንዲሁም የመሬት አቅርቦት አፈፃፀም የስራ መሪ አቶ በቀለ ገብሬ፤ ንብረትነቱ የኢንጅነር ግርማ አፈወርቅ የሆነን 500 ካሬ ሜትር ቦታ በመመሳጠር ለሌላ ግለሰብ እንዲሰጥ አድርገዋል የሚል ሲሆን የተከሳሾቹ ጠበቆች በክሱ ላይ የጉዳቱ መጠን በትክክል አልተገለፀም የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ክሱ እንዲሻሻል ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ አቃቤ ህግ ባለፈው ረቡዕ አሻሽሎ ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ፤ በተበዳዩ ላይ ከ342 ሺህ ብር በላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በቦታው ላይ ሊከናወን የታቀደ ፕሮጀክት መስተጓጐሉን አመልክቷል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችም የጉዳቱ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ደንበኞቻቸው ጉዳያቸውን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቁ ሲሆን በተሻሻለው የግምት መጠን መሠረት የመከላከያ ማስረጃችንን በድጋሚ እናቅርብ የሚል ጥያቄም አቅርበዋል፡፡ ከጠበቆቹ ለተነሱት መከላከያዎች አቃቤ ህግ በሰጠው መልስም፤ ግለሰቦቹ አደረሱ የተባለው ጉዳት ትንሽ ነው መባሉ ተቀባይነት እንደሌለውና የተጠቀሰባቸው አንቀጽም ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን በማመልከት፣ ጥያቄአቸው ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው 1ኛ ወንጀል ችሎትም ባስተላለፈው ትዕዛዝ፤ ጉዳዩ ወደ መደበኛ ክርክር ተሻግሮ ማስረጃ እንዲሰማና ሁለቱም ወገኖች የማስረጃ ማሻሻያቸውን እንዲያቀርቡ በማለት፣ የአቃቤ ህግን ማስረጃና ምስክሮች ለመስማት ለጥር 28 ቀን 2006 ቀጥሯል፡፡

Read 1838 times