Saturday, 04 January 2014 10:29

ወጣቱን በብረት ቀጥቅጠው ገድለዋል የተባሉ ተያዙ

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(6 votes)

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከታናሽ ወንድሙ ጋር ነዳጅ ለመቅዳት ወደ “ኦይል ሊቢያ” የሄደውን የ24 አመት ወጣት ሙባረክ ሱልጣንን በብረት ቀጥቅጠው ገድለዋል በሚል የተጠረጠሩ አምስት የነዳጅ ማደያው ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ሟች ወጣት ሙባረክ፤ ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ከመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ፣ ጳውሎስ ሆስፒታል ፊት ለፊት ወዳለው “ኦይል ሊቢያ” የሄደው የመኪናው ነዳጅ አልቆበት በጀሪካን ለመቅዳት ነበር፡፡ “ቤንዚን በጀሪካን አንቀዳም፣ በሊትር ነው” በሚል በተነሳ ውዝግብ፣ ከነዳጅ ቀጂዎቹ ጋር ጠብ ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ቤተሰቦቹ፤ የነዳጅ ማደያው ሰራተኞች ልጃቸውን በብረት ጭንቅላቱና ጀርባው ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደደበደቡትና ታናሽ ወንድሙ ሊገላግል ሲገባም በያዙት ብረት እሱንም ደብድበው ጉዳት እንደደረሱበት ገልፀዋል፡፡
በድብደባው ክፉኛ የተጐዳውን ልጃቸውን ህይወት ለማትረፍ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል መውሰዳቸውን የጠቆሙት ቤተሰቦች፤ “ከአቅማችን በላይ ነው” የሚል ምላሽ ከሆስፒታሉ በማግኘታቸው፣ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ወስደው እንዳስተኙትና ለሁለት ቀን ህክምና ሲደረግለት ከቆየ በኋላ ህይወቱ እንዳለፈ ተናግረዋል፡፡  
ሟቹ ወጣት፤ ሰው አክባሪና ታታሪ ሰራተኛ እንደነበር ያስታወሱት ቤተሰቦቹ፤ በመልካም ባህሪው ከሠው ጋር ተግባብቶ ከመስራት ውጪ ከማንም ጋር ተጣልቶ እንደማያውቅ መስክረዋል፡፡ በድብደባው ወቅት በኪሱ ይዞት የነበረው ገንዘብና ሞባይሉ መሰረቁን ገልፀው፤ ልጃቸው በገዛ ሀገሩ ላይ በብረት ተቀጥቅጦ መገደሉ ክፉኛ እንዳሳዘናቸው በሃዘን ተሞልተው ተናግረዋል፡፡
ጉለሌ ወደሚገኘው “ኦይል ሊቢያ” ሄደን ነገሩን ለማጣራት ብንሞክርም፤ ባለቤቱን ጨምሮ የማደያው ሰራተኞች በፖሊስ ስለተወሰዱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ፖሊስ ከግድያው ጋር በተያያዘ 5 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያኮሄደ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2996 times