Saturday, 04 January 2014 00:00

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ 7 ከፍተኛ ሃላፊዎች በሙስና ተከሠሡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ስራ አስኪያጅና ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊዎች፤ ዶዘር ለማስጠገን የወጣውን ጨረታ ያለ አግባብ ለአንድ ድርጅት በመስጠት በሙስና የተከሰሱ ሲሆን ፍ/ቤቱ፤ የተከሳሾችን መቃወሚያና የአቃቤ ህግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 16 ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡
ዶዘር ለማስጠገን በወጣ ጨረታ በመንግስት ላይ ከ224ሺ ብር በላይ ጉዳት አድርሠዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ አሠፋ፣ የንግድ ክፍል ዋና ሃላፊው አቶ አበባዬህ ታፈሠ፣ የግዥ ቡድን መሪው አቶ መስፍን ደምሠው፣ የመስክ መሣሪያ ጥገና አገልግሎት ሃላፊው አቶ አብደላ መሃመድ፣ የጠቅላላ ሂሣብ ቡድን መሪው አቶ በለጠ ዘለለው፣ የማቴሪያል ፕላኒንግና ኢንቨንትሪ ማናጅመንት ቡድን መሪው አቶ ታደሠ ኃ/ጊዮርጊስና  የእቃ ግዥ ባለሙያው አቶ ሣሣሁ ጌታቸው ናቸው፡፡  
የእቃ ግዢው ባለሙያ አቶ ሳሳሁ ጌታቸው፤ “ኮማትሱ 801 ዶዘር” የተሠኘውን ተሽከርካሪ ለማስጠገን ለወጣው ጨረታ ከተለያዩ ድርጅቶች ዋጋ መሠብሠብ ሲገባቸው “አንድ አቅራቢ ብቻ ነው ያለው” በማለት ቲኖስ ኃላ.የተ.የግ.ማ ከተባለው ድርጅት ብቻ ዋጋ  ያቀረቡ ሲሆን የቀሩት የስራ ሃላፊዎች ደግሞ ሶስት እና ከዚያ በላይ ተጫራቾች መሳተፍ እንደሚገባቸው እያወቁ አንድ ብቻ ተጫራች የተሣተፈበትን፣ ተጫራቹም የንግድ ፈቃድ ማቅረቡንና ግብር መክፈሉን ሣያረጋግጡ እንዲሁም አማራጭ የእቃዎች ዋጋ ሣያዩ ግዢው እንዲከናወን በማድረግ በመንግስት ላይ ከ224ሺ ብር በላይ ጉዳት አድርሠዋል  ተብሏል፡፡
አቃቤ ህግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሠው እና የሠነድ ማስረጃውን አያይዞ ያቀረበ ሲሆን ተከሣሾቹ ከትናንት በስቲያ ለዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት  የክስ መቃወሚያቸውን በጠበቃቸው በኩል አቅርበዋል፡፡ በእለቱ የተከሣሾች ጠበቃ፤ “ከተከሳሾቹ መካከል የጨረታ ኮሚቴ አባል ያልሆኑ ስላሉ ተለያይቶ ይቅረብልን፣ ለክሡ መነሻ የሆነው ዶዘር ለጥገና የገባው በመድህን በኩል ነው፣ የስኳር ድርጅት የግዥ መመሪያ ለመድህን የግዥ መመሪያ አይሆንም” በማለት መቃወሚያቸውን አቅርበው ክሡ እንዲነሣላቸው ጠይቀዋል፡፡ የጨረታ ኮሚቴውን በተመለከተ የተነሣው ጉዳይ ምስክሮቼንና የሰነድ ማስረጃ በማቀርብበት ጊዜ ሊነሳ የሚችል ነው፣ ያለው አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ዶዘሩ የፋብሪካው መሆኑን አመልክቶ፣ ከመድህን ጋር ተያይዞ የቀረበው አግባብ አይደለም፤ በማለት ተከሳሾች ክሱ እንዲነሳ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 3503 times Last modified on Monday, 06 January 2014 10:11