Print this page
Sunday, 05 January 2014 00:00

በደረቅ ቼክ ለአመታት የታሰሩ ከ200 በላይ ነጋዴዎች ይቅርታ ጠየቁ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

ደረቅ ቼክ ክስ ላይ የሚጠቀሱት የህግ አንቀፆች ባይለወጡም ከ2002 ዓ.ም ወዲህ የእስር ቅጣቱ በብዙ እጥፍ እየከበደ መምጣቱን የሚናገሩት ነጋዴዎች፣ ሆን ብለው ባልፈፀሙት ስህተት መፀፀታቸውን በመግለጽ ሐሙስ ዕለት ለፕሬዚዳንቱ የይቅርታ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
“የደረቅ ቼክ” ክስ ደረጃውና አይነቱ እንደሚለያይ የሚገልፁት ነጋዴዎች፤ በደረቅ ቼክ አጭበርብሮ ለመጥፋት ወይም ክህደት ለመፈፀም የሚሞክር ባይጠፋም፣ በአብዛኛው ነጋዴ ላይ የሚከሰተው ችግር ግን በጊዜ የመክፈልና የማዘግየት ጉዳይ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በተለያዩ ስህተቶች ሳቢያ እንጂ ሰውን ለማጭበርበር አስበን የፈፀምነው ተግባር አይደም የሚሉት እነዚሁ ነጋዴዎች፣ እዳችንን ከፍለን፣ ተበዳይን ክሰን እርቅ ብንፈጥርም፤ ለበርካታ አመታት ከመታሰር አለመዳናችን ያሳዝናል ብለዋል፡፡ ቼክ ከቆረጡ በኋላ በኪሳራ ወይም በሌላ ምክንያት የባንክ ሂሳባቸው ተራቁቶ እዳቸውን መክፈልና ከተበዳይ ጋር እርቅ መፍጠር ያልቻሉ ጥቂት ሰዎች መኖራቸው ግን ይታወቃል፡፡ እንዲያም ሆኖ ሰውን ለማጭበርበር አስበው ድርጊቱን እንደፈፀሙት ካልተረጋገጠ በቀር በበርካታ አገራት የገንዘብ ቅጣት እንጂ የእስር ቅጣት እንደማይፈረድባቸው የህግ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያም ለተወሰነ ጊዜ  የደረቅ ቼክ ክሶች አያያዝ ደህና እንደነበር ሲያስረዱ፤ በ2001 ዓ.ም ለተለያዩ አምስት ሰዎች በድምሩ የ1.2 ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ በመስጠት የተከሰሰ ነጋዴ፣ ከተበዳዮች ጋር እርቅ ባይፈጥርም የአንድ አመት እስር እንደተፈረደበት ይጠቅሳሉ፡፡
የእስር ቅጣቱ እየከበደ የመጣው ግንቦት 2002 ስራ ላይ በዋለው አዲስ መመሪያ መሆኑን ነጋዴዎቹ ገልፀው፤ በ2003 ዓ.ም ለአምስት ሰዎች በድምሩ የ540ሺ ብር ቼኮችን ቆርጦ የሰጠ ነጋዴ፤ ለጊዜው በቂ የባንክ ሂሳብ ስላልነበረው መከሰሱንና የተወሰነበት ቅጣት እጅግ ከባድ መሆኑን በማነፃፀሪያነት አቅርበዋል፡፡ በጊዜያዊ ስህተት ምክንያት የተፈጠረበት ችግር እንጂ ደንበኞቹን ለማጭበርበር የፈፀመው ድርጊት እንዳልሆነ ነጋዴው ሲያስረዳ፣ እዳውን ከፍሎ ተበዳዮችን ክሶ እርቅ መፍጠሩን ይገልፃል፡፡ እንዲያውም፤ ደንበኞቹ ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው፣ ገንዘባቸው እንደተከፈላቸውና እንደታረቁ በመግለጽ የክስ ሂደቱ እንዲቀረጥ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን፤ የተበዳዮቹ ምስክርነት፣ የእስር ቅጣቱን በ6 ወር ወይም በአንድ አመት ከማስቀነስ ያለፈ ውጤት አያስገኝም፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ተከሳሹ የ15 አመት እስር ተፈርዶበታል፡፡
በርካታ ነጋዴዎች ባላሰቡት አጋጣሚ ለችግር እንደሚጋለጡ የተናገረው ሌላው ታሳሪ በበኩሉ፣ ከውጭ አገራት የሚያሰመጣቸውን ሸቀጦች በማከፋፈል ይተዳደር እንደነበር ይገልፃል፡፡
ያስመጣቸው እቃዎች የጉምሩክ ጣጣ እስኪጨርሱ ድረስ ያለ ስራ ላለመቀመጥ ሲልም፤ ከደንበኞቹ ጋር ተስማምቶ የቅድሚያ ሂሳብ እየቀበለ ተጨማሪ ሸቀጦችን ያስመጣል፡፡ ነገር ግን፤ ቀብድ የከፈሉ ደንበኞቹ ከጉምሩክ የሚወጡትን ሸቀጦች እስኪረከቡ ድረስ መተማመኛ ስለሚየስፈልጋቸው፣ በከፈሉት የገንዘብ መጠን በድምር የ850ሺ ብር ሰባት ቼኮችን ቆርጦ እንደሰጣቸው ይሄው ታሳሪ ገልጿል፡፡
ሸቀጦቹን ከጉምሩክ አውጥቶ ሲያስረክባቸው፣ ለመተማመኛ የቆረጠላቸውን ቼክ ይመልሱለታል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንዳሰበው አልሆነም፡፡ በተለመደው ጊዜ ውስጥ የጉምሩክን ሂደት አጠናቅቆ ሸቀጦቹን ማስወጣት አልቻለም፡፡
ደንበኞቹ ለመተማመኛ የሰጣቸውን ቼክ ይዘው ወደ ባንክ ቢሄዱ ደግሞ፣ በቂ የባንክ ሂሳብ አልነበረውም፡፡
ስለሆነም፤ አቤቱታ ቀርቦበት ታሰረ፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ለበርካታ ቀናት ሲደክምበት የነበረው የጉምሩክ ሂደት ተጠናቅቆ እቃዎቹ የተለቀቁት በታሰረ ማግስት እንደሆነ የሚገልፀውም ይሄው እስረኛ፣ ቤተሰቦቼ ወዲያውኑ እቃዎቹን ለደንበኞቼ አስረክበዋል ብሏል፡፡
ነገር ግን፤ እሱ አልተፈታም፤ ሰባት ደረቅ ቼኮችን ቆርጠሃል ተብሎ ሰባት ክስ ቀረበበት፡፡ በእርግጥ፤ አቤቱታ አቅርበው የነበሩት ደንበኞቹ ፍ/ቤት ፊት ቀርበው፣ ስለታማኝነቱ በመመስከር ክሱ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል፡፡ ቢሆንም፤ በ2002 ዓ.ም በወጣው መመሪያ መሰረት 16 ዓመት እስር ተፈረደበት፡፡
እስር ቤት ልትጠይቀው የመጣች ህፃን ልጁ፣ የሀዘን ስሜቱን እንዳታይበት እየተጨነቀ ሃሳቡን ሲናገር፤ ሆን ብዬ የፈፀምኩት ስህተት ባይሆንም ይፀጽተኛል፤ ነገር ግን አጭበርብሬ የወሰድኩት የሰው ንብረት ወይም ሳንቲም የለም፤ ሚሊዮን ብር የሰረቀ ወንጀለኛ እንኳ እንደኔ የ16 ዓመት ከባድ ቅጣት የሚፈረድበት አይመስለኝም ብሏል፡፡

Read 4953 times