Sunday, 05 January 2014 00:00

ሕይወት እየለወጡ ያሉ የአንኮበር የልማት ሥራዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

           “ይኼ የመስኖ ውሃ ከመምጣቱ በፊት ዝናብ ጠብቀን ነበር የምናርሰው። ስለዚህ ቤተሰብ ለማስተዳደር ብዙ እንቸገር ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የማደርገው ባጣና ግራ ቢገባኝ ከአካባቢው ጠፍቼ ልሰደድ ነበር፡፡፡ አክሽን ኤድና-ፓዴት የመስኖ ውሃ አምጥተው ከስደት አዳኑኝ” ያለችው ዙሪያሽ መኮንን ናት፡፡ በአንኮበር ወረዳ የእንዶዴ ጐጥ ነዋሪ የሆነችው ዙሪያሽ፤ የ28 ዓመት ወጣት ብትሆንም የሦስት ልጆች እናት ናት፡፡
“መሬቴ ትንሽ ብትሆንም የመስኖ ውሃ በመጠቀም ሽንኩርት፤ ቀይ ስር፣ ካሮት፣ ቃሪያ፣ ድንች ጐመን አለማለሁ፡፡ አትክልቱን እየወሰድኩ በመሸጥ ለችግሬ አውላለሁ፤ ቤቴንም ለውጫለሁ። ልጆቼንም አስተምራለሁ፣ ትልቋ ልጄ 9ኛ ክፍል ናት፡፡ ሕይወቴም ተለውጧል፣ እንለብሳለን፣ በልተን እናድራለን፣ እየቆጠብን ወደ ባንክም መወርወር ጀምረናል፡፡ በወር 50 ብር ባንክ እከታለሁ፤ አሁን 3ሺህ ብር ቆጥቤአለሁ፡፡ በወር ደግሞ 180 ብር እቁብ እጥላለሁ፤ ቆርቆሮ ቤትም ለመሥራት እያሰብኩ ነው፡፡ ተለውጫለሁ ብዬ አስባለሁ፤ ፓዴት አክሽንን አመሰግናለሁ” ብላለች፡፡
አክሽን ኤድና ፓዴት (የባለሙያዎች ኅብረት ለልማት) እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአንኮበር ወረዳ፣ ከሕዝቡና ከአስተዳደሩ ጋር በመተባበር፣ በርካታ የልማት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች፣ ባከናወኑት ጠቃሚ ሥራ የልማቱ ተጠቃሚ የሆነው ሕዝብ ሕይወታቸው መለወጡን ይናገራሉ፤ አስተዳደሩም ይመሰክራል፡፡ ለመሆኑ ምን ቢያከናውኑ ነው አመኔታና አክብሮት የተቸራቸው?
አሁን መሻሻል አሳይተዋል እንጂ የኅብረተሰቡ ዋነኛ ችግሮች በነበሩት፣ በምግብ ዋስትና፣ በሴቶች ልማት፣ በጤናና ኤች አይቪ ኤድስ ዙርያ ከሕዝቡና ከአስተዳደሩ ጋር በመመካከርና በመግባባት መሥራታቸውን ቀደም ሲል የአንኮበር ፕሮግራም አስተባባሪና መሥራች፣ አሁን ደግሞ በፓዴት ዋና መ/ቤት የፕሮግራም ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርቅነህ ተዋቸው ይናገራሉ፡፡
አቶ ብርቅነህ፣ በምግብ ዋስትና ዘርፍ፣ የተፈጥሮ ደን ጥበቃ፣ መስኖ ልማት፣ የገበሬውና የመንግሥት ባለሥልጣናት አቅም ማጐልበት ሥልጠና መስጠታቸውን፣ ለሴቶችና ወጣቶች ደግሞ የገቢ ማስገኛ መፍጠራቸውን ይናገራሉ፡፡ በጤና ዘርፍ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሟላት 29 ምንጮች አጐልብተው ከ7ሺህ ሕዝብ በላይ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን፣ 1,200 ሰዎች ውሃ የሚያገኙበትንና በአራት ከተሞች በሴቶች የሚመራ የውሃ ማኅበር ከመንግሥት ጋር ሲያቋቁሙ፣ የሴቶች የአመራር አቅም እንዲጐለብት ድጋፍ ማድረጋቸውንና የሴቶች ማኅበር ማቋቋማቸውን፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች ማኅበር እንዲቋቋምና የገቢ ማስገኛ እንዲፈጠርላቸው ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ዘርፍ፣ የአንደኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች አቅም እንዲጐለብት ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ በወረዳው ያልነበረ ቅድመ መደበኛ ት/ቤት (መዋለ ሕፃናት) እንዲከፈት አድርገዋል፡፡ መደበኛ ት/ቤት የውስጥ ቁሳቁስ እንዲሟላና ክበባት እንዲቋቋሙ፣ የክፍል ጥበትን ለማስወገድ አራት ክፍሎች ያላቸው ስድስት ብሎኮች መሥራታቸውን፣ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ደግሞ የቤተመጻሕፍት ብሎክ በመሥራት ተማሪዎች መጻሕፍት እንዲያገኙና አንድ የአስተዳደር ብሎክ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡  
ከከተማ ራቅ ባሉ የገጠር መንደሮች ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለማቅረብ፣ ምንጮች አጐልብተው ሰዎችና እንስሳት ለየብቻ እንዲጠጡ፣ ልብስ ማጠቢያ ገንዳና የገላ መታጠቢያ ሻወር ሠርተው ሕዝቡ ንፅህናውን እንዲጠብቅ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ የደጋና የወይና ደጋ ከብቶች ውሃ ሲጠጡ አልቂት በአፋቸው እየገባ ለጉዳትና ለሞት ያደርሳቸው ነበር። ይህን የገበሬውን ችግር ለመቅረፍ፣ የከብቶች ውሃ መጠጫ ሠርተው እልቂት እንዳይገባ በሽቦ ወንፊት ከድነው እንዳስረከቡ ገልጸዋል፡፡
የወጣቶችን ሥራ አጥነት ለመቀነስ፣ አስተዳደሩ፣ አክሽን ኤድና ፓዴት ወጣቶችን በማኅበር አደራጅተው የመሥሪያ ቦታና ቁሳቁስ አሟልተው ሰጥተዋል፡፡ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን በማኅበር አደራጅተው፣ የገቢ ማግኛ እንዲፈጠርላቸው ሙቅና ቀዝቃዛ ሻወር ያላቸው 10 ክፍሎች ፔንሲዮን ሠርተው ሰጥተዋል፡፡
ሌላው የልማት ሥራ፣ የተጐዳ አካባቢ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ነው፡፡ አፋጀኸኝ በተባለው ጐጥ ጥሩ የእርሻ መሬት የነበረው ስፍራ ከተራራው በሚፈሰው ውሃ ተቦርቡሮ የተፈጠረው ገደል ሰውም ሆነ እንስሳ አያሻግርም ነበር፡፡
ያንን 3 ሜትር ያህል ጥልቀት የነበረውን ገደል፣ አክሽንኤድ ፓዴት ሕዝቡን በማሳመን አፈሩ እንዳይሸረሸር ሦስት ጊዜ በጋቢዮን በመሙላትና የተለያዩ ዛፎች በመትከል፣ አካባቢው ሊድንና እንደገና ሊያገግም ችሏል፡፡ በዚሁ ጐጥ ነዋሪ የሆነው የ32 ዓመቱ ዲያቆን ዘነበ ወርቅነህ፤ የእርሻ ማሳ የነበረው መሬት በጐርፍ ተገምሶ ገደል ሲሆን እያየ እንደነበር ጠቅሶ፣ ያ መሬት አገግሞ በማየቱ ሰው ማጥፋትም ሆነ ማልማት ይችላል በማለት አግራሞቱን ገልጿል፡፡
አክሽን ኤድ-ፓዴት በፈጠረላቸው የመስኖ ውሃ ሕይወታቸው መለወጡን የሚናገሩት ሌላው ገበሬ አቶ ወንዳፈራው ጌጤ ናቸው፡፡ የጐልጐ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወንዳፈራው፤ የ45 ዓመት ጐልማሳ ሲሆኑ የ5 ወንዶችና የሁለት ሴት ልጆች አባት ናቸው፡፡ አቶ ወንዳፈራው የመስኖውን ውሃ ካገኙ በኋላ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሙዝ፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጐመን፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ካሮት፣ … የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች እያመረቱ ነው፡፡
“መስኖ ባልነበረ ጊዜ ሁለቴ ነበር የምናመርተው። ዛሬ ዕድሜ ለፓዴት አክሽን ኤድ በየሦስትና አራት ወሩ እያመረትን እንሸጣለን፡፡ ጐመኑ ሲደርስ ነቅለን ሽንኩርት እንተክላለን፡፡ ጐርጐ ገበያ እየወጣን በመሸጥ ለልጆቻችን ደብተርና ሌላም ነገር ለማሟላት ብዙ ረድቶናል፡፡ አሁን ስለመስኖ አጠቃቀም በየጊዜው ሥልጠና እየሰጡን ልምድ አዳብረናል፡፡ ድሮ ሽንኩርትና ቃሪያ ከገበያ እየገዛን ነበር የምንበላው፡፡ ዛሬ ግን ተክለን እየተጠቀምን ነው። ሸንኮራውም ሙዙም ተሸጦለታል፡፡ ከዚህ በታች 1,500 ብር ሸጬለታለሁ፡፡ ከዚያ በላይ ያለው ደግሞ 800 ብር ያወጣል ብያለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሕይወታችን ተለውጧል፡፡ በተለይ ተማሪዎች ሳይጨነቁና ትምህርት ሳያቋርጡ ነው የሚማሩት” በማለት መስኖ ያስገኘላቸውን ጥቅም አስረድተዋል።
አክሽን ኤድ-ፓዴት በአንኮበር ወረዳ የተሳካ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የወረዳው አስተዳደርም ይመሰክራል። አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ የአንኮበር ወረዳ ም/አስተዳዳሪ፣ የአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ኃላፊ፣ አቶ ታዲዎስ እሸቴ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ዮሐንስ ላቀው የገንዘብና ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ኃላፊና ወ/ት ሜሮን አበበ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጽ/ቤት ኃላፊ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ አክሽን ኤድ-ፓዴት፣ የመንግሥትን ክፍተት ለመሙላት አብሮን የሚሠራ አጋራችን ነው ብለዋል፡፡
የድርጅቶቹን ሥራ በአራት ዘርፍ በመክፈል ማየት ይቻላል ያሉት አቶ ዋሲሁን፤ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን ፈጽሟል፡፡ በግብርና ዘርፍ በምግብ ዋስትና፣ በተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት፣ የተፈጥሮ ተፋሰስ ጥበቃና በመስኖ ልማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ ብዙ ሥራዎች አከናውኗል ብለዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማሳደግና ት/ቤቶችን ምቹና ሳቢ ለማድረግ፣ ብሎኮችን በመስራትና የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። በጐልማሶች ትምህርት ዘርፍ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ 37 ሺህ ዜጐች ከመሃይምነት እንዲወጡ ለአምስት ዓመት ድጋፍ ሲያደርግልን ቆይቷል፡፡
በጤና ዘርፍ ደግሞ 29 ምንጮች አጐልብቶ አርሶ አደሩ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ረድቷል። ምንም ለሌላቸው ሴቶችና ወጣቶች በተዘዋዋሪ ብድር በግ ገዝቶ እየሰጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በእኛ ወረዳ ከድርጅቱ ጋር ለሦስትና ለአራት ዓመታት ተከታታይ የሆነ ሰፊ ሥራ ሠርተናል፡፡ አሠራራቸው ግልፅ ነው፤ የፋይናንስ አጠቃቀማቸው በእኛ ሲስተም የሚተላለፍ በመሆኑ እንከን የለውም። ለሌሎች ድርጅቶችም አርአያ የሚሆን ነው፡፡ መጀመሪያ ያሉ ችግሮችን አጥንቶ፣ ከመንግሥት አካላትና ከአርሶ አደሩ ጋር በመወያየት፣ አርሶ አደሩና መንግሥት በባለቤትነት፤ አክሽን ኤድ-ፓዴት በድጋፍ ሰጪነት ይሠራል።
ማንኛውንም አርሶ አደርና ልጆች ብትጠይቁ “ፓዴት ይኑርልን፣ ሕይወታችንን ለወጠልን” ይላችኋል በማለት ለድርጅቶቹ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። የሌሎችም ጽ/ቤት ኃላፊዎችም አስተያየት ተመሳሳይና በሙገሳ የታጀበ ነበር፡፡   

Read 1632 times