Sunday, 05 January 2014 00:00

በሽታ ተከላካይና ሕመም ፈዋሽ ምግቦች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(26 votes)

          የልብ ሕመም፣ ካንሰር፣ ራስ ምታትና በርካታ የዕለት ተዕለት በሽታዎችን የሚከላከሉና የሚያሽሉ ተብለው በህክምና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የተረጋገጡ 12 ምርጥ ምግቦችን አስተዋውቃችኋለሁ።
ፊግስ:- ከበለስ ጋር የሚመሳሰል የፍራፍሬ ዓይነት ነው፡፡ እነዚህ ፍሬዎች እንደልብ አይገኙም እንጂ በውስጣቸው ካልሲየም የተባለውን ማዕድን የያዙ ናቸው። ፍሬዎቹ፣ ዕድሜን ተከትሎ የሚመጣውን የአጥንት መዳከም (Bone loss) ይከላከላሉ፡፡ ከፍተኛ አሰር (fibre) ስላላቸው፣ በደንዳኔ (Colon)፣ በጡትና በወንድ የዘር ፍሬ መንሳፈፊያ ፈሳሽ አመንጪ ዕጢ (Prostate) ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሳሉ፡፡
ያልተላጡ ትኩስ የፊግስ ፍሬዎችን ከትፈው ከአይብ ወይም ከሰላጣ ጋር ይመገቡ፡፡ እንዲሁም የደረቁ ፍሬዎችን የአትክልት ምግብ ላይ ጨምሮ መመገብ ይቻላል፡፡ በደንብ ያልበሰሉ ፍሬዎች ስለሚጐመዝዙ የበሰሉና ለስለስ ያሉትን ይምረጡ፡፡
ቀይ ስር፡- በንጥረ-ምግብ (Nutrient) የበለፀገው ቀይ ስር፤ ቀልጣፋና ፈጥኖ አሳቢ (Sharp mind) አዕምሮ እንዲኖረን ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። ቀይ ስር፣ በማርጀት ላይ ባሉና  ቅልጥፍና በሌላቸው የአንጐል ክፍሎች ጭምር፣ የደም ዝውውር እንዲጨምር የሚያደርገውን ናትሪክ አሲድ (Nitric Acid) ያመርታል።
ስለዚህ ቀይ ስር ከትፈውና ጠብሰው ከእርጐ ጋር በመደባለቅ ወይም ጥሬ ቀይ ስር ልጠውና ከትፈው ከሰላጣ ጋር ይመገቡ፡፡ ሰውነት፣ በካንሰር እንዳይያዝ የሚረዳውን አንቲ ኦክሲደንት (Anti-oxident) በደንብ ማግኘት ከፈለጉ ግን ጥሬውን እንዲመገቡ ይመከራሉ፡፡
ትኩስ አጋም (Cranberries) እነዚህ ቀይ ወይም የቀይ ዳማ ፍሬዎች የሽንት ቧንቧ ሕመም (urinary tract infection) በማከም የሚስተካከላቸው የለም፡፡ የእነዚህ ትናንሽ ፍሬዎች ጐምዛዛ ጣዕምም፣የልብ ሕመምን ለመከላከል እንደሚረዳ ይታመናል፡፡ የአጋም ፍሬዎች LDL የተባለው አደገኛ ኮሌስትሮል ከኦክስጂን ጋር ተዋህዶ በደም ስር ግድግዳ ላይ እንዳይጣበቅ በሚያደርጉ anthocyanins፣ flavonols፣ እና Proanthocyanidins በተባሉ የአትክልት ኬሚካሎች የበለፀጉ ናቸው፡፡
ትኩስ ቀይ አጋም በጋለ መጥበሻ አመስ አመስ አድርገው፣ ከስጋ ወይም ከሙዝ፣ አናናስና ብርቱካን ሳላድ ጋር አደባልቀው ይመገቡ፡፡ ምክንያቱም የፍራፍሬዎቹ ጣፋጭነት የአጋሙን ጐምዛዛነት ይቀንሰዋል፡፡
የብርቱካን ልጣጭ (Orange Pith)፡- ብርቱካን በቫይታሚን ሲ የበለፀገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ብርቱካን ልጠው ቅርፊቱን (ልጣጩን) አይጣሉ። በቅርፊቱ የውስጠኛ ክፍል ተጣብቆ የሚገኘው ነጭ ለስላሳ ነገር (pith) ለጤና በእጅጉ ጠቃሚ ስለሆነ የቻሉትን ያህል ይመገቡ፡፡ መረር ቢልም አሰርና ኮለስትሮል ከደም ጋር እንዳይዋሃድ የሚያደርገውን አንቲኦክሲደንት (Antioxident) በብዛት ይዟል፡፡
የብርቱካን ቆዳ (ልጣጭ) ወይም የውስጡ ነጭ ለስላሳ (pith) ሲመገቡ፣ፀረ-ተባይ ያልተረጨበት የተፈጥሮ (Organic) ብርቱካን መሆኑን ያረጋግጡ።  
እንቁላል፡- እነዚህ የፕሮቲን ምንጮች ሌላም የጤና ጥቅም አላቸው፡፡ በእንቁላል ውስጥ የሚገኙት የብረትና የዚንክ ማዕድናት፣ ጤነኛ ፀጉርና ጥፍር እንዲኖረን ያደርጋሉ፡፡ እንዲሁም አስኳሉ ውስጥ የሚገኘው ለሲቲን (Iecithine) የተባለ ንጥረ-ቅመም፣ የተጐዱ የአንጐል ሕዋሳትን በሚጠግነውና ኮሌስትሮል ደም ስር ላይ ሳይጣበቅ በደም ውስጥ እንዲዘዋወር በሚያደርገው ኮሊን (Choline) በተባለ ማዕድን የበለፀገ ነው፡፡
የእንቁላልን አበላል ለመንገር መሞከር ምጥ ለእናቷ አስተማረች … ዓይነት ይሆናል፡፡ ነገር ግን እፍኝ ያህል ስፒናች ከእንቁላል ጋር ደባልቀው ወይም በአትክልት በተሞላ አትክልት አናት ላይ በደንብ ያልበሰለ (ለጋ) እንቁላል፣ ሰሊጥና የአኩሪ አተር ሾርባ ጨምረው ቢመገቡ፣ የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡
ሰሊጥ (Sesame seeds) የLDL (መጥፎ) ኮሌስትሮል መጠን ከፍተኛ የሆነባቸው ሰዎች፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሰሊጥን አይመገቡም ነበር፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ጥቂት ማንኪያ ሰሊጥ የበሉ ሰዎች የደም ኮሌስትሮላቸው 10 በመቶ መቀነሱን አንድ በቅርቡ የተካሄደ ጥናት አመልክቷል፡፡የተቆላ ሰሊጥ ከአጃ ጋር ደባልቃችሁ ወይም ያልበሰለ አትክልት፣ የሰሊጥ ፍሬ ወይም የሰሊጥ ዘይት ከሰሊጥ ቅቤ ጋር ደባልቃችሁ ተመገቡ፡፡
ሰናፍጭ (mustard)፡- ሰናፍጭ መፋጀቱ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ካንሰርን በሚከላከለውና  የልብ ሕመምን በሚያድነው፣ እንዲሁም ሴሎችን ከሚጐዱ ፍሪ ራዲካልስ (Free radicals) በሚከላከለውና የአካልን የበሽታ መከላከያ ሥርዓት በሚያነቃቃው Selenium በተባለ ንጥረ-ነገር የበለፀገ ነው፡፡  
የተጠበሰ አትክልት ላይ ሰናፍጭ በማድረግ ወይም የሰናፍጭ ዘይትና ኮምጣጤ አደባልቀው ሰላጣ ላይ በመጨመር ይመገቡ፡፡
የጠቦት ሥጋ፡- ከቀይ ሥጋ ሁሉ፣ የጠቦት ሥጋ የምግብ ይዘቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር ደግሞ ከልብ በሽታና ከስትሮክ በሚከላከለው ኦሜጋ-3 (Omega-3) በተባለ ፋቲ አሲድ የበለፀገ ነው፡፡ በጠቦት ሥጋ ውስጥ የሚገኘው የብረት ማዕድንም ከሰውነታችን ጋር በቀላሉ ይዋሃዳል፡፡ ስለዚህም የደም ማነስ (anemia) ይከላከላል፣ የሰውነት ኃይልም ይጨምራል፡፡
ከጠቦቱ ጐንና ጐን (ወርች)፣ ከጭራው አካባቢ፣ ከጉበትና ከቁርጨምጭሚት መኻል ከሚገኝ ስፍራ ቀይ ሥጋ መርጠው ይቁረጡ፡፡ ሁሉም የቤተሰቡ አባል በሚሰበሰብበት ዕለት፣ ለእራት የጠቦት እግር ጠብሰው ያቅርቡ፡፡ እንዲሁም የተፈጨ የጠቦት ሥጋ በፒዛ ወይም በአትክልት አናት ጨምረው ይመገቡ፡፡
በጣም የቀዘቀዘ ብሮኮሊ (Frozen Broccoli) እንደ በረዶ የቀዘቀዘው የብሮኮሊ ዝርያ ከገበያ ከተገዛው ትኩስ ብሮኮሊ 35 በመቶ የበለጠ፣ በደም ውስጥ በመዘዋወር ጉዳት የሚያደርሰውን ፍሪ ራዲካልስ የሚዋጋውን ቤታ ካሮቲን የተባለ ንጥረ-ቅመም ይፈጥራል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ብሮኮሊ ውስጥ የሚገኘው ሰልፎራፎን (Sulforaphone) የተባለ ኬሚካል፤ ሳንባና የደም ስሮች (አርተሪስ) አመርቅዘው የማቃጠል ስሜት እንዳይፈጠር ይከላከላል፡፡ በቫይታሚን ሲ የበለፀገ መሆኑ ደግሞ ቆዳችን ጤናማ፣ ጠንካራና እንዲያንፀባርቅ የሚያደርገውን ኮላይጅን (collagen) የተባለ ንጥረ-ቅመም ለማምረት ይረዳል፡፡
 የሚፋጁት አትክልቶች (Chili):- ቃሪያና ሚጥሚጣ እንዲፋጁ (እንዲያቃጥሉ) የሚያደርገው ካፕሲያሲ (Capsaicin) የተባለው ኬሚካል፣ ደም ረግቶ ድንገተኛ የልብ በሽታና ስትሮክ እንዳይከሰት ሊረዳ ይችላል፡፡ በተጨማሪም፣ ቃሪያና ሚጥሚጣ መብላት፣ የአፍንጫና የጭንቅላት አጥንቶች ቧንቧ እንዳይጣበቁ ያደርጋል፤ የምግብ ስልቆጣንም እንዲፋጠን ይረዳል፡፡
ስለዚህ እነዚህን አትክልቶች ከትፎ እንቁላል፣ ሾርባና እና ሌሎች ምግቦች ውስጥ ጨምሮ መመገብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ኪዊ (kiwis) :- ይሄ አረንጓዴ ጣፋጭ ፍሬ ዓይን ጤናማ እንዲሆን የሚረዱትን ሉቲን (lutein) እና ዜዛንቲን (Zeaxanthin)  የተባሉ ኬሚካሎች ይዟል። የኪዊ ፍሬዎች፣ በቫይታሚን ሲ እና ኢ እንዲሁም በመጨረሻ ወደ ካንሰር ሊያደርስ የሚችለውን ፍሪ ራዲካልስ በሚዋጋው phytochemicals የበለፀጉ ናቸው።
የሾርባ ቅጠል(Celery leaves):- ሰዎች ብዙ ጊዜ አገዳውን ወስደው ቅጠሉን ይጥሉታል፡፡ ይሄ ግን ስህተት ነው፡፡ የሾርባ ቅጠል ከፍተኛ የምግብ ይዘት ያለው ከመሆኑም በላይ፣ ካልሲየም፣ አይረን፣ ፖታሲየም፣ ቤታ ካሮቲንና ቫይታሚን ሲ፣ ከአገዳው በላይ ይዟል፡፡ ስለዚህ እንደፓርሲሊ አድቀው በመክተፍ ምግቦች ላይ ነስንሰው ወይም ከሳላድ ጋር ደባልቀው ይመገቡ፡፡
ምንጭ፡- (Reader’s digest, March, 2013)

Read 24691 times