Saturday, 04 January 2014 12:41

የደቡብ ሱዳን አዙሪት…

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

…ከሪፍረንደም ወደ ደም!
“እኔ ደቡብ ሱዳንን ነፃ አወጣት ዘንድ የተመረጥኩ የኑዌሮች ልጅ ነኝ… ተከተሉኝ ወደ ነፃነት እንሂድ!”
በስተመጨረሻም ሱዳናውያን ከዘመናት የእርስ በርስ ጦርነትና የጎሳ ግጭት ትርፍ እንደሌለ ገባቸው፡፡ ከጠመንጃ የተሻለ አማራጭ ለመውሰድ ፈቃዳቸው ሆነ፡፡ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲና የሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ በፈረሙት የሰላም ስምምነት፣ ከ25 ዓመታት በላይ የዘለቀውን የእርስ በርስ ግጭት መቋጫ አበጁለት - እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም፡፡
ይህን ስምምነት ተከትሎ ሱዳናውያን፣ ዕጣ ፋንታቸውን በፍጥጫ ሳይሆን በምርጫ፣ በደም ሳይሆን በሪፈረንደም ለመወሰን ተስማሙ፡፡ ከአጠቃላዩ የደቡብ ሱዳን ህዝብ 99 በመቶ ያህሉ፣ የሱዳንን ሁለት መሆን ደግፈው ድምጻቸውን ሰጡ።
 ሃምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም፡፡ ይህቺ ቀን ከ11 ሚሊዮን ለሚበልጡት ደቡብ ሱዳናውያን ልዩ ትርጉም አላት፡፡ የዘመናት ደም መፋሰስ የተቋጨባት፣ የአዲስ ንጋት ጮራ የፈለቀባት፣ ነጻነት የታወጀባት ልዩ ቀናቸው ናት - አዲሲቷ ደቡብ ሱዳን 195ኛዋ  አገር ሆና አለምን የተቀላቀለችበት፡፡
ለሩብ ምዕተ አመት ከዘለቀ የእርስ በርስ ግጭትና ደም መፋሰስ በኋላ፣ ሱዳንን ሰሜን ከደቡብ ለሁለት የሚከፍል ድንበር ተሰመረ፡፡ “የነጻነት ቀን መጣች!!” የሚል መዝሙር ከደቡብ ሱዳን ሰማይ ስር ተዘመረ። ይህ ክስተት ከአለም ፖለቲካዊ ስኬቶች አንዱ እንደሆነ ተነገረለት፡፡ ከደቡብ ሱዳን ሰማይ ስር የሰላም ጀንበር ወጣች ተብሎ አገር በደስታ ፈነጠዘ። ደስታ፣ እልልታና ጭፈራ ሆነ፡፡ የአዲሲቷ ደቡብ ሱዳን ባንዲራ፣ በነጻነት ዝማሬ ታጅባ ከፍ ብላ ተሰቀለች። ለሁለት አመታት አንጻራዊ የሰላም አየር ከሚነፍስበት ሰማይ ስር በነጻነት ተውለበለበች፡፡ ወደሶስተኛው አመት መንፈቅ ያህል እንደተጓዘች ግን፣ ያልተጠበቀ አውሎንፋስ ሳይታሰብ ከተፍ ብሎ ከወዲያ ወዲህ ያራግባት ጀመር፡፡
ከሱዳን ለመገንጠልና ነጻ ለመውጣት በአንድነት አብረው ለዘመናት ሲዋደቁ የኖሩ የደቡብ ሱዳን ጎሳዎች፣ የጋራ ጠላታቸውን ባሸነፉና ነጻ ወጣን ባሉ በሁለት አመታቸው እርስ በርስ ጦር ለመማዘዝ ተዘጋጁ፡፡ ጎሳ ድንበር ሆኖ አይለያየንም ብለው አብረው ለመኖር የተስማሙ ደቡብ ሱዳናውያን፤ ጎራ ለይተው ሊታኮሱ፣ ጎሳ መድበው ሊጫረሱ፣ ዳግም ለሌላ ጦርነት ክተት አውጀው ተነሱ፡፡ ተነጋግረው ያወረዱትን፣ በቃን ብለው የጣሉትን ደም የለመደ ጠመንጃ ዳግም መልሰው ጨበጡ፡፡ ወደ አደባባይ ወጡና እርስ በርስ ተበጣበጡ፡፡
ከሁለት አመታት በፊት በሪፈረንደም ነጻነታቸውን ያወጁት ደቡብ ሱዳናውያን፣ ከሳምንታት በፊት አዲስ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። አዲሲቷን ደቡብ ሱዳን ይመሩ ዘንድ በምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፣ መንበራቸው ላይ ሶስት አመት ሳይቆዩ ነቅናቂ መጥቶባቸዋል፡፡ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር ናቸው፣ በሳልቫ ኬር ላይ አማጽያንን አስታጥቀው የዘመቱባቸው፡፡
ሲጀመር ስልጣን ፈላጊዎች ያሴሩት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው ተብሎ የተነገረለት የሰሞኑ የአገሪቱ ግጭት፣ እየዋል እያደር ግን የአገሪቱን ጎሳዎች ጎራ ለይቶ ያሰለፈ መረር ያለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄ መሆኑ እየለየ መጥቷል፡፡ ከአገሪቱ ህዝብ አብላጫውን ቁጥር (ከህዝቡ 15 በመቶ) የሚይዙት የዲንቃ ጎሳ አባላት ሲሆኑ፣ የኑዌር ጎሳ አባላት ደግሞ 10 በመቶ በመያዝ በብዛት የሁለተኛነትን ደረጃ ይይዛሉ፡፡ ሳልቫ ኬር ከዲንቃ፣ ማቻር ደግሞ ከኑዌር መሆናቸው የሁለቱን ግጭት የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የጎሳዎች ጉዳይ አድርጎታል እየተባለ ነው፡፡
በአብዛኛው ሳልቫ ኬር የወጡበት የዲንቃ ጎሳ አባላትን የያዘው የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦር፣ ከኑዌር ጎሳ የሆኑት የቀድሞው ምክትል ፕሬዜዳንት አስታጥቀው ያሰለፏቸውን አማጽያን ለመደምሰስ ታጥቆ ተነስቷል፡፡ በአሜሪካ የሰላም ኢንስቲቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ፖለቲከኛ ጆን ቴሚን እንደሚሉት፣ ኬርና ማቻር እንዲህ በይፋ ባይታኮሱም በወንበር ጉዳይ በጥርጣሬና በጥላቻ ሲተያዩ የኖሩ የረጅም ጊዜ ባላንጣዎች ናቸው። የግጭቱ ሰበብ ብዙዎች እንደሚሉት ነዳጅ በገፍ የመጥለቅ ጉጉት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ባለስልጣናት መካከል ያለው የስልጣን ሽኩቻና የዘመናት ታሪክ ያለው ያልተፋቀ የጎሳ ልዩነት ነው ባይ ናቸው ፖለቲከኛው፡፡
ሳልቫ ኬር ባለፈው ሃምሌ የቀድሞውን ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻርን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ አባላትን ማባረራቸው፣ ከዘመናት የእርስ በርስ ግጭት ለአፍታ አርፋ የነበረችውን አገር ዳግም ወደከፋ ነገር ሊከታት የሚችል መንገድ ጠርጓል። በአጭር የስልጣን ዘመናቸው ህገመንግስቱን የጣሱ በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል ተብለው የሚታሙት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፣ በካቢኔው ላይ ያሳለፉት ውሳኔ ብዙዎችን አበሳጭቷል፡፡ የወሰዱት እርምጃ የስልጣን ጥመኛነታቸውን ብቻም ሳይሆን ዘረኛነታቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
የሱዳን ትሪቢዩኑ ዘጋቢ አቲያን ማጃክ ማሉ እንደሚለው፣ ሳልቫ ኬር ባባረሯቸው የካቢኔ አባላት ምትክ የሾሟቸው አብዛኞቹ ባለስልጣናት፣ በእርስ በርስ ጦርነቱ ጊዜ ከካርቱም ባለስልጣናት ጋር ይሰሩ የነበሩና አሁንም ድረስ ቅርበትና ወዳጅነት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም በሹም ሽሩ ውስጥ የሱዳን እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል ጥርጣሬን በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል፡፡
በዚህ አወዛጋቢና ፍትሃዊ አለመሆኑ የሚነገርለት ሹም ሽር ከምክትል ፕሬዚደንትነታቸው ተነቅለው የተባረሩት ማቻር፣ ቂም ቋጥረው ነበር ወደ ትውልድ ቦታቸው ዩኒቲ ግዛት የሄዱትና የኑዌር ጎሳ አባላትን ለአመጽ የቀሰቀሱት፡፡
“ሳልቫ ኬር የሚሉት አምባገነን የሚመራው የዲንቃ ጎሳ መንግስት፣ ከአገራችን ጠራርጎ ሊያጠፋን ተነስቷል፡፡ እኛ ኑዌሮች በድህነት ስንማቅቅ፣ እነሱ ግን ነዳጅ እየቸበቸቡ ሊንደላቀቁ ማነው የፈቀደላቸው?!... ተነሱ እንጂ ጎበዝ!” ብለው ቀሰቀሱ ማቻር፡፡ ድሮም በመንግስት ስልጣን አናሳ ቦታ ይዘናል፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችንም ፍትሃዊ አይደለም ብለው እርር ትክን ይሉ የነበሩት ኑዌሮችና የሌሎች አናሳ ጎሳዎች ወታደሮች ናቸው፣ የማቻርን ጥሪ ሰምተው ነፍጥ ያነገቡት፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ታማኝ የጸጥታ ሃይሎች ጋር የከረረ ግጭት ውስጥ የገቡት፡፡
“ልብ አርጉልኝ!... ማቻር የሚሉት ሴረኛ መንግስቴን ሊፈነቅል ነው!” ሲሉ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ አቤት አሉ ሳልቫ ኬር፡፡ ማቻር በበኩላቸው፣ “ያለ ስሜ ስም እየሰጠኝ ነውና አትስሙት!... ሰውየው እልም ያለ ሙሰኛና አምባገነን ነው!” በማለት ውንጀላውን አስተባበሉ፡፡ ሁለቱም ያሉትን ሲሉ፣ የሁለቱም ጦር ተግቶ መታኮሱን ቀጠለበት፡፡
ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋ የመጣው ጦርነት ከአገሪቱ አስር ግዛቶች አምስቱን አዳርሷል፡፡ ታማኝ ምንጮቼ ያላቸውን ጠቅሶ ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው፣ ደቡብ ሱዳናውያን የጎሳ መደባቸው እየታየ ብቻ ግድያና ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መረጃን ዋቢ በማድረግ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ እስካለፈው ማክሰኞ ብቻ በግጭቱ ከ1ሺህ በላይ ዜጎች ሞተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ባሉ የጅምላ መቃብሮች ውስጥ እየተገኙ ያሉ አስከሬኖች የሟቾችን ቁጥር ከፍ እያደረገው ነው ተብሏል፡፡ የዩኒቲ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ቤኒቱ ውስጥ ባለ የመቃብር ስፍራ ብቻ 34 አስከሬኖች ሲገኙ፣ በአቅራቢያዋ ካለ የወንዝ ዳርቻም የሌሎች 20 ሟቾች አስከሬን ወድቆ ተገኝቷል፡፡
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ናቪ ፒላይ በበኩላቸው፤ የማቻር ወታደሮች በተቆጣጠሩት አንድ አካባቢ 75 አስከሬኖች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡ ፍለጋው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥርም ከዚህ በእጅጉ እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡
የመንግስት ጦር ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያለባቸውንና 95 በመቶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሰረተባቸውን በአማጽያኑ በቁጥጥር ውስጥ የገቡ ቤኒቱን የመሳሰሉ ቦታዎች ለማስለቀቅ መታኮስ ከጀመረ ሁለት ሳምንታት አልፈዋል። የአማጽያኑ ጦር የአገሪቱን መዲና ጁባን ለመቆጣጠር 200 ኪሎ ሜትሮች ብቻ እንደቀረው ሲናገር፣ መንግስት በተራው እየጠራረግኋቸው ነው እያለ ይገኛል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በነዳጅ አምራችነቷ ወደምትታወቀው የላይኛው አባይ ግዛት ዋና ከተማ ማላካል የተዛመተው ግጭት፣ ቀስ በቀስ ወደ ቦርና ሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡
በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ከኑሯቸው ተፈናቅለው በርእሰ መዲናዋ ጁባና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ተበትነው ይገኛሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከመጣባቸው መከራ ለማምለጥ ወደ ቢሮው ለመጡ ከ80 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ዜጎች ከለላ ለመስጠት የቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 24 ሺህ ያህል ተፈናቃይ ዜጎች ከመጣው መዓት ለማምለጥ በጫካዎች ውስጥ ተደብቀው እንደሚገኙና፣ ሌሎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩም በአብያተ ክርስቲያናት ቅጽር ግቢ እንደተጠለሉ ዘ ጋርዲያን ባለፈው ማክሰኞ ዘግቧል፡፡
6ሺህ 800 ሰላም አስከባሪዎችን በስፍራው ያሰማራው የተመድ የጸጥታው ምክርቤት፣ ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን በማጤን ተጨማሪ 5ሺህ 500 ወታደሮችን ለማሰማራት ውሳኔ ላይ ደርሷል። ያሰማራቸውን ፖሊሶች ቁጥርም ከ900 ወደ 1ሺህ 323 ከፍ ለማድረግ አቅዷል። ይህ እርምጃ ተፈናቃይ ዜጎችን ለመርዳት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባይካድም፣ የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪሙን ግን፣ ግጭቱ ፖለቲካዊ እንደመሆኑ ፖለቲካዊ እንጂ ወታደራዊ መፍትሄ እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ በአገሪቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የነዳጅ ምርት ስራ በከፍተኛ ሁኔታ እየደናቀፈ ይገኛል፡፡ የደቡብ ሱዳን የፔትሮሊየም ሚንስትር ስቴፈን ዲሁ ዳው እንዳሉት፣ በዩኒቲ ግዛት ይከናወን የነበረው የነዳጅ ምርት፣ ግጭቱ መከሰቱን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል፡፡ ይህም 250 ሺህ በርሜል ከነበረው የአገሪቱ ዕለታዊ የነዳጅ ምርት 45 ሺህ በርሜል ያህል ቅናሽ አስከትሏል፡፡ ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለም የአገሪቱን የነዳጅ ምርት ክፉኛ እንደሚጎዳው ይጠበቃል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ግጭት አገሪቱ ለአለማቀፍ ገበያ በምታቀርበው የነዳጅ ድፍድፍ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል በሚል ስጋት፣ የተለያዩ ኩባንያዎች ባለፈው ማክሰኞ በነዳጅ ዋጋቸው ላይ የተወሰነ ጭማሪ አድርገዋል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት በጉዳዩ ላይ የተለያየ አቋም መያዛቸው እየተነገረ ነው፡፡ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ የአሸባሪዎች ስፖንሰር ከምትላት ሱዳን ተገንጥላ ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች አገር መሆኗን አጥብቃ ስትደግፍ ነው የኖረችው፡፡ ለወደፊት ከነዳጇ የመቋደስ ዕድል ይኖረኛል ብላ የምታስበዋ አሜሪካ፣ ደቡብ ሱዳን ወደ ሌላ ጦርነት እንድትገባ አትፈልግም፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም፤ ኬርና ማቻር ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ ጥሪያቸውን ልከዋል፡፡ ድርድሩን የሚያመቻች ልዩ ልኡክና ዜጎችን ከአደጋው የሚያተርፉ 150 ያህል ልዩ የባህርና የአየር ሃይል አባላትንም በጅቡቲና ኡጋንዳ በኩል ወደዚያው ልከዋል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኡጋንዳና ኬኒያን የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸውን ከደቡብ ሱዳን ለማስወጣት እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን 380 አሜሪካውያንና 300 የሌሎች አገራት ዜጎች በአፋጣኝ ከደቡብ ሱዳን እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ቀውስ እንዲህ እንደዋዛ በአጭር ጊዜ እልባት አግኝቶ የሚበርድ አለመሆኑን የሚናገሩ ተንታኞች ብዙ ናቸው፡፡
በወቅታዊ አለማቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ሱፍያን ቢን ኡዝያር፣ ጉዳዩ የስልጣን ብቻ ሳይሆን ስር የሰደደ የጎሳ ጥያቄ ጭምር መሆኑ አሳሳቢና የበለጠ አስከፊ እንደሚያደርገው ይናገራል፡፡ ሳልቫ ኬር ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለተቀናቃኞቻቸው የማይተኙና ወንበራቸውን ላለማስነካት ታጥቀው የቆሙ መሆናቸውን የገለጸው ኡዝያር፣ ማቻር በበኩላቸው ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የመሆን አላማ እንዳላቸው በአደባባይ ሲናገሩ መሰማቱን ጠቁሟል፡፡ መለሳለስ የማይታይበት የሁለቱ ሰዎች አቋም ነገሩን የበለጠ እንደሚያከረውም ተናግሯል፡፡
አሜሪካ፣ ኖርዌይና ኢትዮጵያ የሚመሩት ቡድንም ወደ አገሪቱ በማምራት ችግሩ በሰላማዊ ድርድር የሚፈታበትን መላ ለመፈለግ የራሱን ጥረት አድርጓል፡፡ አሜሪካ ወደ ደቡብ ሱዳን የላከችውን ልዩ ልኡክ በመምራት ወደ ጁባ ያመሩት ዶናልድ ቡዝ፣ ሁለቱን አካላት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ለማግባባት ጥረት አድርገዋል፡፡ ኬርና ማቻርም ለውይይት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ ነገሩ ከልብ አይመስልም፡፡ ማቻር ውይይቱን ማድረግ የምችለው በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አጋሮቼ ሲፈቱ ብቻ ነው ሲሉ፣ ኬር በበኩላቸው ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ አልፈልግም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ቆራጥ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ መቀጠላቸውም ሆነ፣ የአማጽያኑን ጦር የሚመሩት ማቻር አዲስ ወታደራዊ መንግስት በመመስረት ላይ እንደሚገኙ ፍንጭ መስጠታቸው፣ በዚች አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም የመውረድ ተስፋ እንደሌለ ያመላክታል ብሏል ኡዝያር። ይልቁንም አገሪቱ ወደባሰ የእርስ በርስ ጦርነት የመግባት ዕድሏ ሰፊ ነው ባይ ነው፡፡
ከአለማቀፍ ሰሞንኛ መነጋገሪያ የቀውስ አጀንዳዎች አንዱ የሆነው የሁለቱ ሃይሎች ግጭት፣ በብዙዎች የተለያየ ትንተና እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ ድህነት፣ የጎሳ ፖለቲካ፣ አምባገነንነት፣ ኢ- ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የስልጣን ጥም፣ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት… እና ሌሎችም ጉዳዮች ለደቡብ ሱዳን ግጭት መነሻ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
የሱዳን ትሪቡዩኑ ዘጋቢ የአቲያን ማጃክ ማሉ ብያኔ፣ ‘ሌሎችም’ ከሚለው መደብ ውስጥ ይፈረጃል፡፡ ማሉ እንደሚለው፣ የሰሞኑ የደቡብ ሱዳን ግጭት ንጉንዲንግ ከተባሉት የኑዌር ነብይ ትንቢት የመነጨ፣ የማቻር ቅዠት ነው፡፡ ከመቶ አመታት በፊት በህይወት የነበሩት እኒህ የኑዌር ጎሳ አባል የሆኑ የተከበሩ ነብይ፣ በአንድ ወቅት “ከኑዌር ጎሳ የሆነ ጥርሰ ፍንጭትና ግራኝ ሰው ደቡብ ሱዳንን ነጻ ያወጣታል፣ ህዝቧንም በወጉ ይመራል” የሚል ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ ትንቢቱ ከተነገረ ከዘመናት በኋላ፣ ሬክ ማቻር ወደራሱ ተመለከተ፡፡
እሱ የኑዌር ጎሳ አባል ነው፡፡
እሱ ጥርሰ ፍንጭት ነው፡፡
እሱ ግራኝ ነው፡፡
ማቻር፤ በኑዌሮች መካከል ግራ እጁን ወደላይ ከፍ አድርጎ በፍንጭት ጥርሱ እየተፍለቀለቀ እንዲህ ሲል ተናገረ…“እኔ ደቡብ ሱዳንን ነጻ አወጣት፣ ህዝቧንም በወጉ እመራ ዘንድ የተመረጥኩ የኑዌሮች ልጅ ነኝ!!... ተከተሉኝ ወደ ነጻነት እንሂድ!!...”
በደል ያንገበገባቸው፣ ጭቆና የሰለቻቸው፣ ደማቸው የፈላባቸው ኑዌሮችም፤ ሌሎች ተበዳይ ጎሳዎችን አግተልትለው፣ የጀግና ልጃቸውን ማቻርን ዱካ ተከትለው፣ ወደ ጁባ ሊተሙ ጠመንጃቸውን ወለወሉ - ይላል አቲያን ማጃክ ማሉ፡፡

Read 4877 times