Saturday, 11 January 2014 10:40

ሙሴቪኒና አልበሽር ፕሬዚዳንቱን ሲደግፉ፣ ከስልጣን የተገለሉ መሪዎች ለተቃዋሚው ወግነዋል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ደቡብ ሱዳንን ለመገንጠል የትጥቅ ትግሉን የመሩት ጆን ጋራንግ ከሞቱ በኋላ፤ ስልጣኑን እያጠናከረ በመጣው የሳልቫ ኪር ቡድን እና ከስልጣን በተገለለው የሬክ ማቻር ቡድን መካከል በተፈጠረው ግጭት፣ ኢትዮጵያዊው አምባሳደር ስዩም መስፍን ከቻይና ተጠርተው እያደራደሩ ሲሆን ሰሜን ሱዳን እንደ ኡጋንዳ ወደ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አዘነበለች፡፡ ሳልቫ ኪር የዲንቃ ጐሳ ተወላጅ፣ ተቃዋሚያቸው ሬክ ማቻር ደግሞ የኑዌር ተወላጅ እንደመሆናቸው ግጭቱም የጐሳ ልዩነት የተራገበበት እንደሆነ ቢገለጽም የሟቹ መሪ የጆን ጋራንግ ሚስት እና ልጃቸውን ጨምሮ ከስልጣን የተገለሉ የዲንቃ ጐሳ ተወላጆች ከተቃዋሚው ወገን ጋር እንደተሰለፉ ታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ ምክትላቸው የነበሩት ሬክ ማቻርን ጨምሮ በርካታ የትጥቅ ትግል ዘመን አንጋፋ መሪዎችን ከስልጣን በማግለል፣ በትጥቅ ትግል ያልነበሩ ባለሙያዎችን መሾማቸው የእርስ በርስ ቅራኔን እንዳባባሰ ይገለፃል። በሌላ በኩል ሬክ ማቻር ያቀነበባበሩት መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን ተከትሎ ግጭቱ ሲፈነዳ፤ የኑዌር ጐሳ ተወላጅነታቸውን ከሳልቫኪር የዲንቃ ጐሳ ተወላጅነት ጋር በማነፃፀር የእርስ በርስ ግጭቱ ጐሳን የተከተለ ነው በማለት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ነገር ግን፣ የሟቹ መሪ የጆን ጋራንግ ሚስትና ወንድ ልጃቸው እንደ ፕሬዚዳንቱ የዲንቃ ጐሳ ተወላጆች ቢሆኑም፤ ከተቃዋሚው ሬክ ማቻር ጐን እንደተሰለፉ ታውቋል፡፡ በአምባሳደር ስዩም አስታራቂነት በሚካሄደው ድርድር ላይ ሬክ ማቻርን በመወከል ከመጡት ተደራዳሪዎች መካከል አንዱ የጆን ጋራንግ ልጅ ናቸው ተብሏል፡፡

ሳልቫ ኪርን ለመደገፍ ጦራቸውን እንደላኩ ከሚነገርላቸው የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ለመነጋገር፣ ሬክ ማቻርን በመወከል ወደ ካምፓላ የተጓዙትም የጆን ጋራንግ ሚስት እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ድርድሩን ከምትመራው ኢትዮጵያ ጋር ኬንያ በድጋፍ ሰጪነት የተሰለፈች ሲሆን፤ ሰሜን ሱዳን ከኡጋንዳ በተቃራኒ ተቃዋሚውን ወገን ትደግፋለች ተብሎ ሲነገር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር በድንገት ወደ ጁባ በመሄድ ከሰሜን እና ከደቡብ ሱዳን በተውጣጣ ጦር የነዳጅ ማውጫ አካባቢዎችን እንዲጠብቅ ከሳልቫኪር ጋር መስማማታቸው የብዙዎችን ግምት የሚያፈርስ ሆኗል። በትጥቅ ትግሉ መሪዎች መካከል ፀብ በተነሳ ቁጥር ወደ አልበሽር በመሄድ ይጠለሉ የነበሩት ሬክ ማቻር፤ ሰሞኑን በተፈጠረው የአልበሽር የሳልቫ ኪር ሽርክና ቅር እንደተሰኙ ተገልጿል፡፡

ከድርድሩ ጐን ለጐን የኢጋድ አደራዳሪ በመሆን የተሾሙት አምባሳደር ስዩም መስፍን ሬክ ማቻር ለተኩስ አቁም ስምምነት ባቀረቡት ቅድመ ሁኔታ መሰረት ወደ ጁባ በመሄድ እስረኞችን አነጋግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን በተፈጠረው ግጭት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሠማርተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ንብረታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በጋምቤላ በኩል የገቡት ኢትዮጵያውያን፤ ጊዜያዊ መጠለያ ከቆዩ በኋላ ወደየአካባቢያቸው እየሄዱ ሲሆን በማላካ እና ናስራ በተባሉ የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች መጋዘኖች እንደተዘረፈባቸው እና ያልተዘረፉ መጋዘኖቻቸውንም ጥለዋቸው እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን አለመረጋጋት ምክንያት ብዙ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ጋምቤላ እየገቡ ሲሆን ቁጥራቸው ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ይገኛል፡፡

Read 3262 times