Saturday, 11 January 2014 10:40

ሰማያዊ ፓርቲ፤ የምናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥልኝ አልፈቅድም አለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

            ሰማያዊ ፓርቲ፤ የምናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥልኝ አልፈቅድም ሲል ገለፀ፡፡ ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም፤ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ግንኙነት አላቸው፤ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ይሰራሉ” መባሉ በሰላማዊ ትግል የሚሳተፉ ፓርቲዎችን ለመወንጀል ያለመ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል አጣጥሎታል፡፡ “ዘጋቢ ፊልሙ፤ የፓርቲያችንን ከፍተኛ አመራሮችና የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ፎቶ እያሳየ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ይሰራሉ ማለቱን አጥብቀን እንቃወማለን” ያለው ፓርቲው፤ በህግ ስልጣን የተሰጠው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት “አሸባሪ” ብሎ ሳይፈርጀው ኢሳት ቴሌቪዥንን መጠቀም እንደሚያስከስስ እና ከአሸባሪዎች ጋር እንደመተባበር ተድርጐ መቅረቡ የዜጐችን መብት የሚጥስና ህገመንግስቱን የሚቃረን ነው ብሏል፡፡

“መንግስት የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን በቁጥጥር ስር በማዋሉና አንዳንድ የግል ጋዜጦችም በተጽእኖ ስር በመውደቃቸው፣ በአሸባሪነት እስካልተፈረጀ ድረስ በአማራጭነት በኢሳት ቴሌቪዥን እንናገራለን፤ ሃሳባችንንና ፕሮግራማችንን እናስተዋውቃለን፤ የደጋፊዎቻችንን ቁጥርም እናበዛለን” ያለው ፓርቲው፤ በኢሳት ቴሌቪዥን መናገር ያስከስሳል የሚለውን የመንግስት ማስፈራሪያ አንቀበለውም ሲል አጣጥሎታል፡፡ “የብሔራዊ ደህንነትና የፀረ ሽብር ግብረ - ሃይል አድርጐ ራሱን የሚጠራ አካል ይህን ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ብቃትም የህግ አግባብም የለውም” ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ይህ ራሱን ከህግ በላይ የሰቀለ አካል ያለ ምንም ገደብ ከሚሰራቸው ጥፋቶችና የመብት ጥሰቶች እንዲታቀብ እንጠይቃለን ብሏል፡፡ “የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ - ሃይል የሚሰራውን ስህተት ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተባባሪ ሆኖ እያገዘው ነው” ያለው ፓርቲው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለ ሰላማዊ ትግል፣ ስለፓርቲያቸው እንቅስቃሴና ስለ እቅዳቸው ለመግለጽ ኢሳትን እንደ አማራጭ እንዳይጠቀሙ ለማሸማቀቅና ከትግሉ ለማስወጣት የሚያደርገውን ጥረት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል፡፡

“መንግስት ከዚህ ቀደም በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩ ዜጐች ገና ሳይፈረድባቸው አሸባሪ እያለ ሲወነጅል በተደጋጋሚ ተቃውሟችንን አሰምተናል” ያለው ፓርቲው፤ ተፈርዶባቸው ከታሰሩ በኋላም መንግስት ያልተባለ ነገር እየጨመረ ነው ሲል ነቅፏል፡፡ ፓርቲው በዋቢነትም “ርዕዮት አለሙ የሽብር ድርጊት ልትፈጽም እንደተዘጋጀች እጮኛዋ ስለሺ ሀጐስ መስክሮባታል” ተብሎ በዘጋቢ ፊልሙ የተገለፀው ፈጽሞ ውሸትና መሰረተቢስ ውንጀላ በመሆኑ ፓርቲው እንደሚቃወመው ገልጿል፡፡ “ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና ሌሎች ባለስልጣናት ቃለ ምልልስ አድርገው ያውቃሉ፤ የኢሳት ጋዜጠኞች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች የመንግስት ባለስልጣናት ምላሽ ሲሰጡ ሰምተናል” ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ “ኢሳት አሸባሪ ከሆነና የአሸባሪ ልሳን ከሆነ ባለስልጣናቱ ለምን ቃለ -ምልልስ ያደርጋሉ፣ ለምንስ ምላሽ ይሰጣሉ?” ሲል ጠይቋል፡፡ “እስካሁን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ኢሳትን አሸባሪ ብሎ አልፈረጀውም፤ ኢሳትም የግንቦት ሰባት ልሳን ነኝ ብሎ አያውቅም” ያለው ፓርቲው፤ በአገር ውስጥ ያሉ አማራጮች እስካልሰፉ ድረስ፣ በኢሳት የምንናገረው ስለ ሽብርና ለሽብርተኞች ግብአት እስካልዋለ ድረስ በአማራጭ ሚዲያነት እንጠቀመዋለን ብሏል፡፡ መንግስት በተለያየ መንገድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርሰውን ማሸማቀቅ እንዲያቆም በማሳሰብም፤ የሚናገርበትን ሚዲያ ማንም እንዲመርጥለት እንደማይፈቅድ ሰማያዊ ፓርቲ አስታውቋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ለሆኑት ለአቶ ሬድዋን ሁሴንና ለሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሽመልስ ከማል በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

Read 3061 times