Saturday, 18 January 2014 13:32

ፓትርያርኩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሙስና ላይ እንዲዘምቱ አዘዙ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

“በቤተክርስትያናችን ሽፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል”
ሰንበት ት/ቤቶቹ የአማሳኝ አስተዳዳሪዎችን ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በተንሰራፋው ሙስናና ሸፍጥ ላይ በተጠናከረ ኃይል በመዝመት የተጀመረውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ከዳር እንዲያደርሱ አዘዙ፡፡ አቡነ ማትያስ ትእዛዙን የሰጡት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በሥር ነቀል የእርማት ርምጃዎች ለማስተካከል ያስተላለፉትን መግለጫ ለመደገፍና የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት የኾነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ያዘጋጀው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ተግባራዊ እንዲኾን ለመጠየቅ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ፣ ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለተሰበሰቡት በሺሕ ለሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሰጡት መመሪያ፣ ቃለ ምዕዳንና የበዓለ ጥምቀት ቡራኬ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 160 ገዳማትና አድባራት የተሰበሰቡት 1800 ያህል የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሀ/ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አማካይነት ባወጡት መግለጫ፤ ፓትርያርኩ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በማውገዝ ለማስተካከል አበክረው ሥራ በመጀመራቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ብዙኃን የሰንበት ት/ቤት አባላት አይነኬ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያስተቻት የቆየውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ስከ እስር ደርሰው ሲታገሉት እንደቆዩም ተናግረዋል፡፡ የሙስናና ብልሹ አስተዳደር ተጠቂ እየኾኑ በማደጋቸው አስከፊነቱን በሚገባ እንደሚያውቁ በመግለጫቸው ያተቱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ፤ ፓትርያርኩ በየጊዜው ያስተላለፏቸውን መመሪያዎች በመከታተልና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ስለ ሚያደርገው እንቅስቃሴ በመወያየት ችግሩ ከመሠረቱ እንደሚወገድና በዘመናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ትንሣኤ እንደቀረበ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ ሙስናንና ብልሹ አስተዳደርን ለማረም የሚካሔደው እንቅስቃሴ በእነርሱም በወላጆቻቸውም ጽኑ እምነትና አቋም እንደተያዘበት የጠቀሱት ወጣቶቹ፤ ጥረቱን ከግቡ ለማድረስ ከፓትርያርኩ ጎን ቆመው በታዘዙበት መሥመር ለመሰለፍ ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የፀረ ሙስና እንቅስቃሴውን እንደግፋለን ብላችኁኛል፤ እኔም እንደምትደግፉኝ አምናለኹ፤›› በማለት ተስፋቸውን የገለጹት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው÷ ‹‹ዘመኑ የእምነት ጉድለትና የኑፋቄ ነው፤ ሐቅ፣ መልካም አስተዳደር፣ እውነተኝነትና ሓላፊነት ጠፍቷል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል፤›› ሲሉ አምርረው ተናግረዋል፡፡ ስለሙስናና ብክነት ከሚሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ጋር ተያይዞ ‹‹ኹላችንም ሌቦች ተብለናል›› የሚል ቅሬታ ያቀረቡላቸው ወገኖች መኖራቸውን ያልሸሸጉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹የሚያመው ያመው ይኾናል፤ ሁላችኁም አማሳኞች ናችሁ የሚል አልወጣኝም፤ የሚያማስኑ እንዳሉ ግን ሐቅ ነው፤›› ሲሉ የችግሩ አስከፊነት ሊካድ እንደማይገባው አረጋግጠዋል፡፡ ሙስና ማለት ጥፋት ነው ሲሉ የቃሉን ትክክለኛ ንባብና ገላጭነት ያብራሩት ፓትርያርኩ፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ያለው የሙስና ሙስና›› መኾኑን በመግለጽ፣ በፀረ ሙስና ቅስቀሳው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ በይበልጥ እንዲዘምቱበት አሳስበዋቸዋል፡፡ ‹‹ተይዞ ባለው የፀረ ሙስና ቅስቀሳ እናንት የሰንበት ት/ቤት አባላት በይበልጥ ብትዘምቱበት፤ በተጠናከረ ኃይል ይህን ብትረዱኝና ከዳር ብናደርሰው አመሰግናችኋለሁ፡፡›› በተያያዘ ዜና÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ እንቅስቃሴ የሚበዙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እንደሚደግፉት እየተገለጸ ቢሰነብትም ‹‹ምእመናን በእኛ ሕግ ምን ያገባቸዋል፤›› የሚሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ቅሬታቸውን ለፓትርያርኩ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

እንደምንጮቹ መረጃ፣ ቅሬታ አቅራቢ አስተዳዳሪዎቹ የመዋቅር ለውጡን የሚቃወሙ ሲኾኑ ከእነርሱም መካከል ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጡ በተከታታይ የተካሔዱት የድጋፍ መግለጫ ስብሰባዎች ምእመናኑን በእነርሱ ላይ ኾነ ተብሎ ለማነሣሣት የታለሙ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሰንበት ት/ቤቶቹ ከፓትርያርኩ ጋር ባካሔዱት ውይይት፣ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በግልጽ በመቃወማቸውና በማጋለጣቸው ያሳሰሯቸውና ያስደበደቧቸው አስተዳዳሪዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅም በማዋልና ለባዕድ አሳልፎ በመስጠት አላግባብ በልጽገዋል የሚሏቸውን አማሳኝ አስተዳዳሪዎች ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ፣ እንደ ሕጉ አግባብም ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለማመልከትም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አባላት ተጠቁሟል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥቅምት ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ ‹‹የሃይማኖት ዕንከን ሳይኖርባት፣ ሞያ ሳያንሳትና ተቆርቋሪ ምእመናን እያሏት›› በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ መገታት እንዳለበት የገለጸ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን የአገልግሎት አፈጻጸም እሴቶችና መርሖዎች የሚገልጸው መሪ ዕቅድ ከገመገመ በኋላ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ ለመቅረፍ በሚያስችል አኳኋን ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

Read 5417 times