Monday, 27 January 2014 07:50

ኖህ ሪል እስቴት ያስገነባቸውን ቤቶች ከሦስት ወር በኋላ ያስረክባል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

በመዲናይቱ የተመረጡ ቦታዎች ለሱቅ፣ ለቢሮና ለመኖሪያ ያሠራቸውን ቤቶች ግንባታ አጠናቆ ፊኒሺንግ ላይ መሆኑን የገለጸው ኖህ ሪል እስቴት፤ በቀጣይ ሦስት ወራት ቤቶቹን ለባለቤቶቹ እንደሚያስረክብ አስታወቀ፡፡
የኖህ ሪል እስቴት ተባባሪ መሥራችና ማናጀር አቶ ቴዎድሮስ ዘላለም እንደገለጹት፤ ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አጠገብ ለሱቅና ለቢሮ የሚሆን ባለ 12 ፎቅ (አቢሲኒያ ሞል)፣ እንዲሁም ሲኤምሲ አካባቢ በጀንበር የመኖሪያ ሰፈር የተሠሩት ዘመናዊ ቪላ ቤቶች ግንባታ ተጠናቋል፡፡
ከሁለት ዓመት ወዲህ ቤትን በጊዜ ባለማስረከብ በዘርፉ የተፈጠረውን ፍርሃትና ስጋት ለመቅረፍ፣ ኖህ ሪል ኢስቴት አዲስ ስትራቴጂ አማራጭ ነድፎ፤ በከተማዋ የተመረጡ ቦታዎች ቤቶችን ገንብቶ በጊዜ ለማስረከብ መወሰኑን የተናገሩት ማናጀሩ፤ በዚህም መሠረት፤ በሁለት ቦታ የጀመራቸውን የቤቶች ግንባታ ዓመት ሳይሞላ በዘጠኝ ወር ያስረክባል ብለዋል፡፡ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት የተሸጡ ንብረቶች ቢኖሩም ባለንብረቶቹ አንዱንም ስላልተረከቡ አቢሲኒያ ሞል የመጀመሪያው ይሆናል ያሉት ማናጀሩ፤ ሞሉ እስከ 4ኛ ፎቅ ለሱቆች፣ ከ5ኛ ፎቅ እስከ 12ኛ ለቢሮና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እንደሚውሉ ተናግረዋል፡፡
ሲኤምሲ አካባቢ የተሠሩት 15 እጅግ ዘመናዊ ቪላ ቤቶች ግንባታ በ6 ወር ተጠናቆ ቀለም የተቀቡ ስለሆነ ከ3 ወር በኋላ እንደሚያስረክቡ ጠቅሰው፣ አሁን የቀራቸው የአጥር ሥራና ታንከር ውስጥ ውሃ መሙላት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሞሉም ሆነ የቪላዎቹ ሽያጭ 40 በመቶ መድረሱንና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም ሽያጭ እንደሚያጠናቅቁ ማናጀሩ ተናግረዋል፡፡

Read 3986 times