Monday, 27 January 2014 07:55

“የሰንደቅ” ጋዜጣ አዘጋጆች ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ዋና አዘጋጁ በ5ሺህ ብር ዋስ ተለቋል

 “ሰንደቅ” ጋዜጣ ስለ ጉዲፈቻ በሰራው ሰፊ ዘገባ ላይ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር  በስም ማጥፋት አቤቱታ እንዳቀረበበት የገለፀው ዋና አዘጋጁ ፍሬው አበበ፤ ባለፈው ሀሙስ ጠዋት ማዕከላዊ ምርመራ ቀርቦ ቃሉን ከሰጠ በኋላ በ5ሺህ ብር ዋስ መለቀቁን ተናገረ፡፡
ጋዜጣው ታህሣሥ 23 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ‹‹የጉዲፈቻ ዘመቻ በተጠያቂነት መጀመር አለበት›› ርዕስ አንቀጽና በሕግ አምዱ ላይ ‹‹ጉዲፈቻና የሕጎቻችን ክፍተቶች›› በሚል ዘገባ ማውጣቱን ዋና አዘጋጁ ተናግራል፡፡ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በጋዜጣው የአገርን ገፅታ የሚያበላሽ፣ የፍትህ ስርዓቱን ተዓማኒነት የሚያሳጣና የሚኒስትሯን ክብር የሚያዋርድ ዘገባ አውጥቷል ሲል ለፓሊስ አቤቱታ ማቅረቡን የተናገረው ዋና አዘጋጁ፤ ከትላንት በስቲያ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ቀርቦ ቃሉን ከሰጠ በኋላ፣ በ5ሺህ ብር ዋስ መለቀቁን ገልጿል፡፡
በጉዲፈቻ ዙሪያ ባወጡት ዘገባ ስም በማጥፋት በመንጀላቸው እንዳሳዘነው የገለጸው ዋና አዘጋጁ ፍሬው፤ “የተፈለገው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን እንዳናጋልጥ ቢሆንም ፈርተን ወደ ኋላ አንልም፤ ሞያው የሚጠይቀውን  መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን” ብሏል፡፡ 

Read 2753 times