Monday, 27 January 2014 07:57

ባሏ በነዳጅ ያቃጠላት እናት ሞተች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

            በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፤ ባሏ በነዳጅ ቃጠሎ ያደረሰባት ወ/ሮ ብዙነሽ ነጋ ከአራት ሳምንት ስቃይ በኋላ ማክሰኞ እለት የሞተች ሲሆን፤ ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለው አቶ ሽታው ሁሴን በፖሊስ ተይዞ ምርመራ እየተካሄደ ነው፡፡
ለ12 አመታት በትዳር የቆዩት ባልና ሚስት አንድ ልጅ ማፍራታቸውን የገለፁት ዘመዶች እንደሚሉት፤ በሟቿ ላይ የደረሰው ጥቃት ያልታሰበ ዱብዕዳ አይደለም፡፡ ለበርካታ ጊዜ ባለትዳሮቹ እየተጋጩ፤ ወ/ሮ ብዙነሽ በተደጋጋሚ ጥቃት ይደርስባት ነበር ብለዋል፡፡
አቶ ሽታው ባለቤቱን ከቤተሰብና ከጐረቤት ጋር እንዳትቀራረብ ብቻ ሳይሆን ከቤት ውጭ እንዳትንቀሳቀስ እያስፈራራ፣ በተደጋጋሚ ጉዳት እንዳደረሰባት የሚናገሩት የሟች እህት ወ/ሮ አበባ ነጋ፤ ባለፈው ወር ታህሳስ 17 ቀን እኔ ቤት ቆይታ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቷ ከሄደች በኋላ ነው ጥቃት የፈፀመባት ይላሉ፡፡ እህታቸው መጐዳቷን ሰምተው ወዲያውኑ መሄዳቸውን እና አሰቃቂነቱ ለማመን እንደሚከብድ የገለፁት ወ/ሮ አበባ፤ “ህይወቷ አላለፈም፤ ግን በቃጠሎው ቆዳዋ እንደጨርቅ ከላይዋ ላይ የወለቀ ይመስል ነበር” ብለዋል፡፡
ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ በቃጠሎ ክፉኛ የተጐዳችው ወ/ሮ ብዙነሽ፤ በአካባቢው በሚገኝ ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ተደርጐላት፣ ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የተላከችው ከሌሊቱ 7 ሰዓት እንደሆነ ቤተሰቦቿ ገልፀዋል፡፡
ለከፍተኛ ስቃይ የተዳረገችው ወ/ሮ ብዙነሽ ጥቃቱ እንዴት እንደደረሰባት ሆስፒታል ውስጥ በቆየችባቸው ቀናት እንደነገረቻቸው የገለፁት ቤተሰቦቿ፤ ቤት ውስጥ በነጭ ጋዝ ምድጃ ወጥ እየሠራች ነበር ብለዋል፡፡ ባለቤቷ የቤቱን በር ቆልፊው ብሏት ከቆለፈችው በኋላ እራት እንድትሰጠው አዘዛት፡፡ ወጡ ውስጥ ጨው ጨምራ እራት ልትሰጠው ስትል ነው ከመቀመጫው ተነስቶ፣ ምድጃውን እስከነድስቱ አንስቶ የደፋባት፡፡ ከእሳቱ ጋር የምድጃው ጋዝ እላይዋ ላይ የተከለበሰባት ወ/ሮ ብዙነሽ፤ መላ አካሏ በእሣት ነደደ፡፡  “ሰላም ሳታገኝ ስትኖር የቆየች እናት ላይ ነው አሰቃቂው ኢ- ሰብአዊ ድርጊት የተፈፀመባት” የሚሉት ቤተሰቦቿ ሟች ከሁለት አመት በፊት አንገቷን በገመድ ሊያንቃት ሲሞክር ጐረቤት ነበር ያስጣላት ብለዋል፡፡
ለጊዜው በህይወት የተረፈችው ወ/ሮ ብዙነሽ ከነልጇ ሸሽታ በታላቅ እህቷ ቤት ቤት ተጠግታ ብትቆይም ኑሮን ለማሸነፍ ወደ አረብ ሃገር ስራ ፍለጋ ሄዳለች፡፡ ግን አረብ ሀገርም አልተሳካላትም፡፡ 11 ወር ቆይታ የተመለሰችው ወ/ሮ ብዙነሽ፤ ከባለቤቷ ጋር እርቅ ተፈጽሞ አብራው መኖር ብትጀምርም፤ ከቀድሞው ጥቃት አልተገላገለችም፡፡ አንድ አመት ሳይቆይም የባሏ ጥቃት ህይወቷን የሚያጠፋ አሰቃቂ ደረጃ ላይ ደረሰ ብለዋል - ቤተሰቦች፡፡
 ከአንገቷ በታች በስተቀር መላ ሰውነቷ በእሣት ቃጠሎ እንደነደደና ያለማቋረጥ እያበጠ በሚፈነዳ ቁስል እንደተሸፈነ የገለፁት የሟች ቤተሰቦች፤ የተኛችበት አንሶላ ከአንድ ሰዓት በላይ ያስቸግር ነበር ብለዋል፡፡
ከአራት ሳምንት በኋላ ህይወቷ አለፈ፤ የቀብር ስነ ስርአቱም በአካባቢው በሚገኘው ሳሎ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጥር 14 ቀን 2006 ተፈጽሟል፡፡
የአቃቂ - ቃሊቲ ገብርኤል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ሃላፊ ሳጅን ጐሽሜ አገኘሁ፣ ተጠርጣሪው በእለቱ ተራ በሆነ ቅናት ተነሳስቶ ሟች ወደ ቤቷ ስትመለስ ጠብቆ “የት ቆይተሽ ነው የመጣሽው፣ “አልኮል ጠጥተሻል” በሚል ፀብ አንስቶ፣ የተቀጣጠለውን ምድጃ ሰውነቷ ላይ በመወርወር ቃጠሎውን እንዳደረሰ ገልፀዋል፡፡ ፖሊስም ጥቆማው እንደደረሰው ወዲያው ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማድረጉን የገለፁት ሳጅን ጐሽሜ አገኘው፤ ተጠርጣሪው በአካባቢው በሚገኘው የከተማ ነክ ጉዳዮች ፍ/ቤት ቀርቦ ፣ ፍ/ቤቱ በ2ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ  ፖሊስ ለፍ/ቤቱ በህይወት እና በሞት መካከል ያለችውን ተጐጂ የጉዳት መጠን የሚያሳይ ፎቶግራፍ በማቅረብ ጭምር ዋስትናው እንዳይፈቀድ ቢያመለክትም ፍ/ቤቱ በአቋሙ ፀንቷል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ጉዳዩን ለከፍተኛው ፍ/ቤት በድጋሚ አቅርቦ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት እንዲቆይ በተደረገበት ሁኔታ ተጐጂዋ ህይወቷ ማለፉን  ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የምርመራ መዝገቡ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተልኮ በምርመራ ላይ መሆኑን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡  

Read 4117 times