Monday, 27 January 2014 08:22

የግብፆች “አዲስ የምስራች”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከሰው ቤት ተገኝቶ ምንድነው ቅልውጡ፣
ግብፆች ለሀበሻ ደግሰው ላይሰጡ፡፡
ይህ ቅኔ የተነገረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በግብጽ ቤተክርስቲያን ሥር በምትመራበትና፣ ዻዻሳት ከግብጽ ታስመጣ በነበረበት ዘመን ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው የሃይማኖት አባት እንይሾሙ የተጣለባቸው ገደብ ትክክል አይደለም፣ በሚል ውሣኔው ይሻርና ይታረም ዘንድ ጥያቄ ላነሱ ኢትዮጵያዊን ክብር ይግባቸው፡፡ ከሰላሣ ዓመት በላይ የወሰደው ሙግትና ድርድር ለፍሬ በቅቶ ኢትዮጵያዊያን ከራሳቸው የሃይማኖት አባቶቻቸውን ለመሾም በቁ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከ1600 ዓመታት በኋላ ለእኩልነትና ለነጻነት በቃች፡፡ አገሪቱ ለዚህ ማዕረግ እንድትበቃ ላደረጉት ለንጉሱ አጼ ኃይለ ስላሴና ረዳቶቻቸው ነፍስ ይማር ልባዊ ጸሎቴ ነው፡፡
እስከማውቀው ድረስ እስልምና እንደ ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች አንድ ማዕከል የለውም። ይህ በመሆኑም ወደ ግብጽና ወደ ሌሎች አገራት ተጉዘው ተምረው  የመጡ  ሙስሊም ወንድሞቻችን የግብጽን ወይም የሌላ አገር ተጽዕኖ አላመጡምና  እድለኞች ነን፡፡
ከግብጽ ተጽዕኖ ነጻ የመውጣት ሁለተኛው የትግል ምዕራፍ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ግብፆች “በአባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት ኘሮግራም ይኑራችሁ መጀመሪያ የእኛን ፈቃድ ወይም ይሁንታ ማግኘት አለባችሁ፣ ይህን ታደርጉ ዘንድም አስገዳጅ አለም አቀፍ ስምምነት አለ፡፡ ለአባይ ወንዝ ታሪካዊ ባለመብቶች ነን” ይሉናል፡፡ ኢትዮጵያ የምታውቀው፣ የፈረመችውና የሚያስገድዳት ውል ባለመኖሩ የግብጽ ይሁንታ አትፈልግም በማለት የሕዳሴውን ግድብ በራሷ ጊዜ ጀምራለች፡፡ ይሄንንም በተግባር እንዲገነዘቡት አድርጋለች፡፡
አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ የሕዳሴውን ግድብ የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ጊዜ፣ “ግድቡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ግብጽንም፣ሱዳንንም ስለሚጠቅም መሠራት የነበረበት በሶስቱም አገሮች ገንዘብ ነበር” የሚል መንፈስ ያለው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ግብፆች የግድቡን ትክክለኛ ባህሪ ከመረዳት ይልቅ እንደ አንድ የመቅሰፍት ኃይል በማየት ወደ  ማጥላላት ዞሩ እንጂ፡፡
የግድቡ መሠራት ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ቋሚና የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንደሚያስገኝ፣ አደጋ ሳይሆን ጥቅም መኖሩን ኢትዮጵያ አጠንክራ ለማስረዳት ብትጥርም፣ በተለይ ግብፆች የሚሰማ ጆሮ፣ የሚያገናዝብ አእምሮ ያገኙ አይመስልም፡፡
መረዳት የተቸገረው አእምሮአቸው ግን ጥያቄ በመጫር ሰነፍ ስላልነበረ የግድቡ ዝርዝር ጥናት ተሰጥቶን በራሳችን ባለሙያዎች እናስፈትሸው የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ ይህን ጤነኛ ያልሆነ ጥያቄ፣ ትክክለኛ አላማና ፍላጐት የተረዳው የኢትዮጵያ መንግስት “ ሲያምራችሁ ይቅር” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ በመስጠት ምራቃችው አፋቸው ውስጥ እንዲደርቅ አደረጋቸው፡፡
ምን እየሠራች እንደሆነ የምታውቀው ኢትዮጵያ፣ ያለባቸውን ስጋት ማጥፋት ካልሆነም መቀነስ ይችሉ ዘንድ አንድ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ስለታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንዲያጠና ፈቃደኛነቷን  አሳየች። እያንዳንዱ አገር ከየራሱ ሁለት ሁለት ሰው እንዲያቀርብ፣ በሶስቱም አገራት ተቀባይነት ያገኙ ሌሎት አራት ሰዎች በቡድን ውስጥ እንዲካተቱ ተደረገ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አቋሟ በድምጽ የሚተላለፍ ውሣኔ ቢኖር የበላይነቱን እንደምትይዝ ልብ ይሏል፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ በውሣኔዋ ገፍታ አለም አቀፍ የሙያተኞች  ቡድን ወደ ሥራ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ቡድኑ ሥራውን እስኪያጠናቅቅ ለመጠበቅ ትዕግስት ያጡት ግብፆች፤ ኢትዮጵያን መረጃ እየደበቀች ነው በማለት ከሰሱ፡፡ ከአንድ ጊዜም ሶስት ጊዜ ግድቡ በሚሠራበት ቦታ በመገኘትና ሂደቱን ለመከታተል የቻለው አለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን፤ ሥራውን አጠናቆ ለሶስቱም መንግስታት ሪፖርቱን አስረከበ፡፡ ሱዳንና ኢትዮጵያ ለሪፖርቱ ቀና አስተያየት ሲሰጡ፣ ግብጽ ብቃት ይጐለዋል በማለት አጣጣለችው፡፡
አለም አቀፉ የሙያተኞች  ቡድን፤ ሪፖርቱን ለየሀገራቱ መስጠት እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ፣ የግድቡ ሥራ ከአንድ ደረጃ ላይ እየደረሰ ስለነበር፣ አባይ ድሮ ይፈስበት ከነበረው ወጥቶ አዲስ በተሠራለት መስመር እንዲፈስ ተደረገ፡፡ ግብፆች በዚህም ተናደዱ። በግብጽ የወቅቱ ኘሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ የሚመሩት የእስላም ወንድማማች ፓርቲ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጦ ስብሰባውም በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲተላለፍ ተደረገ። በዚህ ስብሰባ ላይም  በአሁኑ ወቅት ከስልጣን ተወግደው በእሥር ላይ የሚገኙት መሐመድ ሙርሲ ነገሩን በድርድር ለመጨረስ እንደሚፈልጉ ጠቁመው “አስፈላጊ ከሆነ ግን እያንዳንዷን የአባይ ጠብታ ውሃ በደም ጭምር እናስከብራለን” ሲሉ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በዲኘሎማሲያዊ ቋንቋ ተገቢ እርምጃ ከመውሰዱ በላይ፣ ባልሳሳት ተወካዮች ምክር ቤት ደርሶ እየተንከባለለ የነበረው የናይል ተፋስስ አባል አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ አደረገ፡፡ ስምምነቱ የመጨረሻ ጉዞውንም ጀመረ፡፡ አሁን ኡጋንዳም አጽድቃለች፡፡ ሌሎች እየተጠበቁ ናቸው፡፡
የባለሙያዎች ቡድን ያደረገውን ጥናት ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሶስቱ አገሮች የጋራ ስብሰባ ከብዙ  መጓተት በኋላ ካርቱም ላይ ሲጀመር፣ ግብፆች አሁንም የተለመደውን ፈቃደኝነት የማጣት  ባህሪያቸውን ይዘው ቀረቡ፡፡ የትናንት አጋራቸው ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ አቋም በማዘንበሏ፣ እንደ ከዳተኛ ቆጥረው ከመዝለፋቸውም በላይ፣ (የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ንግግር አስበው ሊሆን ይችላል)፣  በግድቡ ሥራ በቀጥታ ለመሣተፍ እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን እንዲቀንስ፣ የሚያመነጨው የኃይል መጠንም በዚያው መጠን እንዲያቀዘቅዝ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ይኸኛውም ፍላጐታቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፤ ግብፆች ቢሰሙትም ባይሰሙትም  የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ለአንድ ሴኮንድ እንኳ እንደማይቆም በተደጋጋሚ ተናገረ፡፡
ግብፆች ግን አልተዋጠላዋውም፡፡ የግድቡ ግንባታ በ30% ተጠናቋል የሚለውን የመንግስት መግለጫ “ውሸት” ነው ማለት ያዙ፡፡ ሕዝቡ ድሀ ስለሆነ መንግስትም የገንዘብ አቅም ስለሌለው ግንባታው መቆሙ አይቀርም ሲሉም ተነበዩ፡፡ መንግስት ቀድሞ ነገሩን “የጠላት ወሬ ነው” አለው እንጂ እኔ የሚኖረኝ መልስ “ልክ ናችሁ እንዲያውም ከመሬት አልተነቃነቀም” የሚል በሆነ ነበር፡፡ በአገራችን “ሽል ከሆነ ይገፋል ቂጣ ከሆነ ይጠፋል” የሚል ምሣሌ አለና ጊዜ ለሚመሰክርው ጉዳይ የማንም ራስ ሊታመም አይገባውም ማለቴ ነው፡፡ ለዚህኛውም የግብፆች ቧልት የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው መልስ፣ “በድጋሚ ቁርጣችሁን እወቁ” የሚል ዓይነት ነበር፡፡ “በሚቀጥለው ዓመት ግድቡ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል” የሚል መግለጫ መስጠት   ትርጉሙ ይሄው ነው። እስከአሁን ላነሷቸው ጥያቄዎችና ፍላጐቶች በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ያጡት ግብፆች፤ “ማንም ከማድረግ አያድንም” ወዳሉት እርምጃ ገብተዋል፡፡  
አዲስ ባረቀቁትና 98% የሕዝብ ይሁንታ አግኝቷል በተባለው ሕገ መንግስታቸው ውስጥ ለአባይ (ናይል)  አንድ አንቀጽ በመስጠት፤ “መንግስት የአባይን (ናይልን) ወንዝ ደህንነት ይጠብቃል፤ ግብጽ በወንዙ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት ከማስከበሩም በላይ እስከመጨረሻው ድረስ ተጠቃሚ ያደርጋታል….” የሚል ሃሣብ እንዲካተት አድርገዋል፡፡ ይህ ቃል እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የግብጽ ባለሥልጣናት መግለጫዎች ተራና ዋጋ ቢስ ቃል አይደለም፡፡ በዚህ ህገ-መንግስት መሠረት የሚቋቋመው የግብፅ መንግስትና የመከላከያ ኃይሉ በአጠቃላይ የግብጽ ሕዝብና መንግስቱ የሚለፉለት ጉዳይ ነው፡፡ ግብጽና ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የሆነ የድንበር መዋሰን ባይኖራቸውም፣ እንዲህ በቀላሉ ወታደራዊ ወረራ ያካሂዳሉ ተብሎ ባይታሰብም፣ ብዙ ደባ ለመጠንሰስ ግን የሚያገለግል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት እንዲሁም የአለም አቀፍ ግንኙነቷን በማደናቀፍ፣ ይህን ሁሉ የምናደርገው በሕገ መንግስታችን ተደነገገውንና ግብጽ በአባይ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ሊሉን ይችላሉ። አሁንም የጀመሩት ስለሆነ ወደ ኋላ ይመለሳሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ይህ የግብፆች “አዲስ የምስራች”፤ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፡፡ የቀድሞውንና ያለውን እውነት ነው ያጐላው፡፡ አዲሱ ህገ መንግስት፤ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ተደራድራ፣ የግብጽን አቋም ለመለወጥ  የምታደርገው ጥረት ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ሌሎች የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ፈራሚ አገሮች፣ ይህን የግብጽ ሕገ መንግስት እንደ ተራ ጉዳይ ሊያዩት የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መድረኮች ላይ በማቅረብ መወያያና መከራከሪያ ሊያደርጉት፣ ያረገዘውን ደባም ሊያጋልጡ ይገባል፡፡ ይሄ ህገ መንግስት ነገ የሚያመጣውን መዘዝ አለም እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡


Read 2165 times