Print this page
Monday, 27 January 2014 09:18

የእናቶች ሞት ቅኝት እና ተገቢው ምላሽ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(2 votes)

እ.ኤ.አ በ2015/ አለም አቀፉ ህብረተሰብ መሻሻል ሊያሳይባቸው ካሰባቸው 8/ ነጥቦች አንዱ የእናቶች ሞት መጠንን ከነበረበት በ3/4ኛ መቀነስ ነው፡፡ ይህንን እቅድ ማሳካት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለብዙ ሀገራት የቤትስራ በመሆኑ እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ይገኛል፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው አሰራር ምን ይመስላላ በሚል በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች ለዚህ እትም ጋብዘናል፡፡
ዶ/ር ማርታ ምንውየለት በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  የእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተርና ዶ/ር ኢክራም መሃመድ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  የእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ኬዝ ቲም ኦፊሰር በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የእናቶች ሞት ምክንያት የማወቅ አሰራር እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡
ዶ/ር ኢክራም መሐመድ እንደሚሉት “...ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችን እና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የተለያዩ የአሰራር ዘዴዎችን ቀርጾ እየተገበረ ይገኛል፡፡ ለዚህም በከፍተኛ ሁኔታ የእናቶችን ሞት ምንነት ለማወቅ ይረዳል ተብሎ የታመነበት አዲስ አሰራር የእናቶች ሞት ቅኝት እና ተገቢው ምላሽ የሚባል አሰራር ነው፡፡ ይህም ማለት አንዲት እናት በአንድ አካባቢ በምትሞትበት ጊዜ በአካባቢው ከሚገኙ ሰዎች አንዳቸው ለጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛዋ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛዋ ያለውን ሁኔታ በስፍራው በመገኘት ካጣራች በሁዋላ ወደጤና ጣብያ በመሄድ እሪፖርት ታደርጋለች፡፡ በጤና ጣያ ደረጃ ከደረሰ በሁዋላ በተቋቋመው ኮሚቴ ሁኔታውን በመመልከት የሞተችው እናት ጉዳይ ደረጃ በደረጃ ማለትም ወደዞን ከዚያም ወደፌደራል ይተላለፋል፡፡ የዚህ አሰራር ጥቅም 1/ ምን ያህል እናቶች እንደሞቱ ለማወቅ  2/ የሞት ምክንያቱ ከታወቅ ወደፊትም ሌሎች እንዳይጎዱ እርምጃ ለመውሰድ 3/ በጤና ጣቢያ ደረጃ ሊሰሩ የማይችሉትን በዞን ወይንም በወረዳና በክልል እንዲሰራ ማስቻል ነው፡፡  
ዶ/ር ማርታ ምንውየለት እንደሚሉት “... በእድሜዋ ከ15-49 አመት ያለች ሴት ስትሞት የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛዋ ለጤና ጣብያ ሪፖርት ታደርጋለች፡፡ በጤና ጣብያ ይህንን ጉዳይ ለመከታተል ብቻ የተቋቋመው ኮሚቴ የሞት ምክንያቱን ለማወቅ ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛዋ ያገኘውን መረጃ በመያዝ ወደስፍራው ያመራል፡፡ ይህ ስራ የሚሰራው የአካባቢውን ነባራዊና ባህላዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንጂ ከባድ ሀዘን ላይ ሆነው ወይንም በድንገት አይደለም፡፡ የኮሚቴው አባላት ወደስፋራው ከደረሱ በሁዋላ በሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች መሰረት የተከሰተው ሞት የእናት ሞት ነው? ወይንስ አይደለም የሚለውን ይለያሉ፡፡ የእናት ሞት ማለት አንዲት ሴት ነፍሰ ጡር ሆና ወይንም በወለደች በስድስት ሳምንት ውስጥ የሚከሰት ሲሆን ከእርግዝናው ጋር በቀጥታ በተያያዘ ወይንም ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ሕመሞች ተባብሰው ለሞት ያበቋት ከሆነ ተጣርቶ ይመዘገባል፡፡ በእርግጥ ከአሁን ቀደምም የእናቶች ሞት የሚመዘ ገብበት አሰራር የነበረ ቢሆንም አሁን የተነደፈው ስልት ግን ዛሬ አንዲት እናት የሞተችበት ምክንያት ነገ ለሌላ እናት ሞት ምክንያት እንዳይሆን እርምጃ ለመውሰድ በሚያ ስችልበት መንገድ የሚመዘገብ በመሆኑ አሁን የተዘረጋው አሰራር ይበልጥ ጠቃሚ ነው፡፡”
ዶ/ር ኢክራም መሐመድ በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ለእናቶች ሞት ምክንያት ናቸው ተብለው የተመዘገቡትን እንደሚከተለው ገልጻለች፡፡
“...የእናቶች ሞት ምክንያት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ በሚል በሁለት ይከፈላል፡፡ ቀጥተኛው የእናቶች ሞት ምክንያት ከእርግዝና ጋር የተገናኘ ሲሆን ይህም ከእናቶች ሞት ውስጥ ወደ 85% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህም ሲዘረዘር፡-
የተራዘመ ምጥ 13%
የማህጸን መተርተር ወደ 12%
በእርግዝና ወቅት ከሚከሰቱ የደም ግፊት ጋር በተያያዘ ወደ 11%
ከውርጃ ጋር በተያያዘ ወደ 6%
ከወሊድ በሁዋላ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ወደ 5%
ከወሊድ በፊት ደም መፍሰስ 5%
ሌሎች ምክንያቶች ወደ 9% ይደርሳሉ፡፡
ቀጥተኛ ያልሆነ የእናቶች ሞት ሲባል አንዲት እናት ቀደም ሲል ሕመም የነበራት ሆኖ ነገር ግን በጽንሱ ምክንያት ከተባባሰ ደረጃ በመድረስ ለህልፈት ሲዳርጋት ነው፡፡ እነዚህ ሕመሞችም በመቶኛ ሲሰሉ፡-
ኤችአይቪ ኤይድስ ወደ 4%
የደም ማነስ 4%
ወባ 9% ናቸው፡፡
እናቶችን ለሞት እንዲበቁ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብለው የተመዘገቡ ደግሞ ሶስት መዘግየቶች አሉ፡፡
እናቶች ወይንም የትዳር ጉዋደኞቻቸው እንዲሁም በቅርብ የሚገኙ ቤተሰቦች በጤና ተቋም የመጠቀምን ጥቅም በሚመለከት ግንዛቤ ማጣት፣
አንዲት እናት ወደጤና ተቋም በተገቢው ሰአት አለመድረስ (የትራንስፖርት እጥረት የመንገድ አለመኖር ወይንም የገንዘብ እጥረት) በመሳሰሉት ምንያቶች፣
አንዲት እናት ወደጤና ተቋም ከደረሰች በሁዋላ የሚያጋጥሙዋት መዘግየቶች... በቂ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ...ወዘተ...”
ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ለማስወገድ ወይንም እናቶች ሞት እንዳይገጥማቸው ለማድረግ ያለውን አሰራር ዶ/ር ማርታ ሲገልጹ ...
“...ዋናው በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራበት ያለው ጉዳይ ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን አስፈላጊነት እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ ያ ማለትም ህብረተሰቡ ወይንም እናቶች በጤና ተቋም የመውለድን ጥቅም እና አስፈላጊነት ከተረዱ ሁሉም እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይል ስለሚወልዱ በከፍተኛ ደረጃ ለሚጠበቀው የእናቶች ሞት መቀነስ ያግዛል፡፡ ይህንንም ለማድረግ... የጤና ልማት ሰራዊት የአንድ ለአምስት ትስስር እና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አሉ፡፡ እነዚህ አካላት 2500 /ሁለትሺህ አምስት መቶ/ በሚሆኑ የህብረተሰብ አባላት ዙሪያ በመሆን በማስተማርና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በሙሉ ተሳትፎ ይሰራሉ፡፡ ህብረተሰቡ መረዳት ወይንም ማወቅ የሚፈልገውን ነገር በየሳምንቱ ወይንም በየአስራ አምስት ቀኑ ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር በመገናኘት ግንዛቤያቸውን ያዳብራሉ፡፡ በዚህ የተቀናጀ አሰራር የአካባቢው ሰዎች በመሀከላቸው እርጉዝ ሴት ካለች ወደህክምና ተቋም በመሄድ ክትትል እንድታደርግ ሀሳብ ያቀርባሉ... የተወለዱ ልጆች ካሉ የእናቱን ጡት እንዲጠባ እንዲሁም ክትባት በወቅቱ እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ እቅድ መጠቀም ያለባት ሴት ካለች እንድትጠቀም እና ሌሎች ከጤና ጋር የተያያዙ ክንዋኔዎችን ከጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጋር እየተወያዩ ይሰ ራሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሴቶች እራሳቸው ጤናቸውን ለመንከባከብ አስፈላጊውን ድጋፍ ስለሚ ያደርጉ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ማርታ በጤናው ዘርፍ ያሉትን አገልግሎቶች በማጠናከር ረገድ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አብራርተዋል፡፡
በመንግስት ደረጃ ወደ 150 /አንድ መቶ ሀምሳ/ የሚጠጉ ሆስፒታሎች ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጤና ጣብያዎች በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡
የግል ባለሀብቶችም በዘርፉ እንዲሰማሩ መንግስት የሚያበረታታ ሲሆን አሁን በስራ ላይ ያሉትም የህክምና ተቋማት የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ ያላቸው እገዛ ቀላል አይባልም፡፡
የትራንስፖርቱን አገልግሎት ለማሻሻል የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው አመት ወደ 811 /ስምንት መቶ አስራ አንድ/ አምቡላንሶችን ገዝቶ ለክልሎች አሰራጭቶአል፡፡
ሆስፒሎችንና ጤና ጣብያዎችን በማስተሳሰር የሕመምተኞችን ቅብብል ወይንም ሪፈራል የተሳካ ለማድረግና ታካሚዎች ተገቢውን ሕክምና በወቅቱ እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ ትግበራው ተጀምሮአል፡፡
የድንገተኛ የቀዶ ጥገና ሐኪሞችን እያሰለጠኑ ብዛታቸውን በመጨመር እንዲሁም የሐኪሞችንና የአዋላጅ ነርሶችን ቁጥር በማሳደግ በጥራት እና በፍጥነት ህብረተሰቡ ጋ የመድረስ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው፡፡
ባጠቃላይም ከላይ የተገለጹት የአሰራር ሂደቶችና ሌሎችንም ተግባራት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቀዳሚነት እያስተባበረ እና እራሱም እየፈጸመ የሚገኝበት ሁኔታ ያለ ሲሆን የእና ቶችን ሞት በመቀነሱ ረገድ ግን መንግስት ብቻውን የሚወጣው ሳይሆን መላው ህብረተሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት እጅ ለእጅ ተያይዘው ከተፈለገበት ደረጃ ለማድረስ ኃላፊነቱን እንደሚ ጋሩ እሙን ነው፡፡” ብለዋል ዶ/ር ማርታ ምንውየለት፡፡






Read 3218 times