Print this page
Monday, 27 January 2014 09:52

ዩኒየኑ በ33 ሚ. ብር የዱቄት ፋብሪካ ሊያቋቁም ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

የግብርና ግብአት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከል ከፍቷል
ሁለት ኮምባይነርና አንድ የጭነት መኪና ገዝቷል
ካፒታሉ 13.2 ሚሊዮን  ደርሷል

የግብርና ግብአት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከል ከፍቷል ሁለት ኮምባይነርና አንድ የጭነት መኪና ገዝቷል ካፒታሉ 13.2 ሚሊዮን ደርሷል በአካባቢው ስንዴ በብዛት ይመረታል፣ ካሁን በፊት በስሩ ካሉ መሠረታዊ የገበሬ ማኅበራት የሚሰበስበውን ስንዴ፣ በጥሬው ነበር የሚሸጠው። አሁን ግን፣ እሴት ጨምሮበት፣ ዱቄቱን ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በቀን 800 ኩንታል ስንዴ የሚፈጭ ፋብሪካ ለማቋቋም፣ ከአንድ የቱርክ ኩባንያ ጋር ውል ተፈራርሞ፣ ኤል ሲ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) እየከፈተ ነው፡፡ ለዱቄት ፋብሪካው ፕሮጀክት 33 ሚሊዮን ብር መመደቡንና ለፋብሪካው ተከላ ከዶዶላ ከተማ አስተዳደር 6‚600 ካ.ሜ ቦታ በኢንቨስትመንት ማግኘታቸውን በዶዶላ ወረዳ የተቋቋመው የራያ ዋከና ገበሬዎች ኅብረት ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ዩሱፍ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከንጉሡ ዘመን አንስቶ የግብርና ምርት ግብአት አቅርቦት በማሻሻል፣ የገበሬውን ሕይወት ለመለወጥ በመንግስት፣ በማኅበራትና በግል ድርጅቶች ጥረት ቢደረግም እስካሁን ድረስ፣ ገበሬው ዘንድ የግብርና ምርት ግብአት በስፋት ሊደርስ እንዳልቻለ፣ በንግድ እርሻ አገልግሎት ፕሮግራም፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ (ኢንቫይሮመንታል ስፔሻሊስት) ዶ/ር ጂሬኛ ግንደባ ተናግረዋል፡፡

መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው ሲ ኤን ኤፍ ኤ የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ላለፉት 30 ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ለገበሬዎች የምርት ግብአት ለማዳረስ ባደረገው እንቅስቃሴ ስኬታማ በመሆኑ፣ የተከበረ ስም እንዳለው ዶ/ር ጂሬኛ ገልፀዋል፡፡ ይኼው ድርጅት በአፍሪካም በተመሳሳይ የእርሻ ምርት ግብአት ለማቅረብ ዩኤስኤ አይዲን እርዳታ ጠይቆ፣ የ2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስላገኘ፣ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሁለት ዓመት የንግድ እርሻ አገልግሎት ፕሮግራም ቀርፆ፣ በኦሮሚያ ስድስት አካባቢዎች፣ በቢሸፍቱ፣ አምቦ፣ ነቀምቴ፣ ፍቼ፣ ዶደላና ሻሸመኔ አካባቢ ነዋሪ ገበሬዎች፣ ከግል ድርጅቶችና ማኅበራት ጋር ለሙከራ የግብርና ምርት ግብአት አቅርቦት ማዕከል እያቋቋመ ነው፡፡ ከ“ራያና ዋከና ዩኒየን” ጋር በመተባበር ያቋቋመው ማዕከል፣ ባለፈው ሳምንት የተመረቀ ሲሆን ቀደም ሲልም የነቀምቴና የቢሸፍቱ ተመርቀው አገልግሎት መጀመራቸውንና የተቀሩትም ሥራቸው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

የራያ ዋከና የገበሬዎች ኅብረት ዩኒየን፣ በመጋቢት 1996 ዓ.ም፣ ከአዳባ ወረዳ ሦስት፣ ከዶዶላ ወረዳ ደግሞ ስድስት መሠረታዊ ማኅበራትና 3‚684 አባወራዎችን በመያዝ በ155ሺ ብር መነሻ ካፒታል መቋቋሙን፣ አሁን ሁለት ወረዳዎች ተጨምረው የአራት ወረዳ 65 መሠረታዊ ማኅበራት ማቀፉንና በ2004 ዓ.ም ኦዲት ሪፖርት መሠረት ካፒታሉ 13.2 ሚሊዮን ብር መድረሱን ሥራ አስኪያጁ አቶ መሐመድ ገልፀዋል፡፡ የዩኒየኑ ዓላማ፣ መሠረታዊ ማኀበራት ከአቅማቸው በላይ የሆኑትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር መቅረፍ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት፣ ዩኒየኑ፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ - ተባይና ፀረ - አረም ኬሚካሎችና መርጫ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ አትክልት ዘሮች (ጥቅል ጐመን፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ሽንኩርት…) የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦትና ሽያጭ ያከናውናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒየኑ፣ መሠረታዊ ማኅበራት የሚገለገሉባቸው እያንዳንዳቸው 40 ኩንታል መያዝ የሚችሉ ሁለት ኮምባይነሮች፣ በ3 ሚሊዮን ብር ገዝቶ አቅርቧል፡፡ መሠረታዊ ማኅበራት ምርታቸውን ወደገበያ የሚወስዱበት፣ ከገበያ ደግሞ ማዳበሪያ፣ ኬሚካሎች፣ ምርጥ ዘር፣… በማመላለስ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አይሱዙ መኪናና የዘር ማበጠሪያ አለው፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ መሠረታዊ ማኅበር በየዓመቱ በዩኒየኑ ወጪ ኦዲት ያስደርጋል፣ የመጋዘን አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ምርጥ ዘር እያባዛ በዩኒየኑ ስም አሽጐ ያሰራጫል፡፡

“በዚህ ዓመት ግብርና መሩን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየሠራን ነው፡፡ የዚህ አካባቢ ምርት ስንዴ ነው፡፡ እስካሁን፣ ስንዴውን በጥሬው ነበር የምንሸጠው፡፡ አሁን ግን አስፈጭተንና እሴት ጨምረን ዱቄት ለማቅረብ ወስነናል፡፡ በዚሁ መሠረት ፋብሪካውን የምንተክልበት 6‚600 ካ.ሜ ቦታ ከዶዶላ ከተማ አስተዳደር በኢንቨስትመንት ተረክበናል፡፡ በቀን 800 ኩንታል የሚፈጭ ወፍጮ ለመትከል፣ ከቱርክ ኩባንያ ጋር ውል ተፈራርመን ኤል ሲ (ሌተር ኦፍ ክሬት) እየከፈትን ነው፡፡ ይህም፤ 33 ሚሊዮን ያህል ብር የሚፈጅ ትልቅ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል አቶ መሐመድ፡፡ ቀደም ሲል ዩኒየኑ የአባላትን ምርት የሚሸጠው ለተለያዩ ድርጅቶች ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ለኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት 9ሺ ኩንታል ስንዴ ለማቅረብ ተስማምተውና አብዛኛውን ማለትም 8‚500 ኩንታል አቅርቧል። ቀሪውን 500 ኩንታል ሲያስረክቡ አዲስ ውል እንደሚፈራረሙ ተናግረዋል፡፡ ሌላው አቶ መሐመድ ለዩኒየኑ ትልቅ ስኬት ነው ያሉት፣ ከዩኤስኤ አይዲ የግብርና ንግድ አገልግሎት ፕሮግራም ጋር በግብርና ምርት ግብአት አቅርቦት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት መዋዋላቸውን ነው፡፡ በስምምነቱ መሠረት፤ ዩኤስኤ አይዲ 40ሺ ዶላር ሲያወጣ፣ እኛ ደግሞ ከዚያ በላይ እናወጣለን። እኛ በ750ሺ ብር ያህል የግብአት መሸጫ ማዕከል ሠርተናል፡፡ እነሱ፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎች፣ ኮምፒዩተር፣ ፍሪጅ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ የመድኃኒትና መደርደሪያ ያሟሉ ሲሆን እዚያ ውስጥ ለሚሠሩ አራት ባለሙያዎች የሁለት ዓመት ደሞዝ ይከፍላሉ፡፡

ገበሬው ከዚህ ማዕከል የሚያገኘው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ቀደም ሲል የምርት ግብአቶችን ከተለያዩ አቅራቢዎች ለመግዛት ሲያፈላልግ ብዙ ጊዜ ያባክን ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ የሚገዛው የእርሻ ግብአት ዋጋው ውድና ጊዜው ያለፈበት ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ግብአቶቹን ፍለጋ ሳይንከራተት፣ የሚፈልጋቸውን ግብአቶች፣ በተመጣጣኝ ዋጋ በአንድ ማዕከል ያገኛል፡፡ ምርጥ ዘር፣ ፀረ - አረም፣ ፀረ - ዋግ፣ ፀረ - ተባይ፣ የተለያዩ አትክልት ዘሮች እንዲሁም የእንስሳት መድኃኒቶች ገዝተን እናቀርባለን፡፡ እኛ ቀደም ሲልም የምርት ግብአቶችን እናቀርብ ነበር፡፡ አሁን እነሱ ያቀረቡልን ለየት ያለ ነገር የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ነው፡፡ አሁን ገበሬው ግብአቶቹን መግዛት ብቻ ሳይሆን እንዴት መጠቀም እንዳለበት እንዲሁም ማድረግ ስላለበት ጥንቃቄ እናሰለጥነዋለን፡፡ በተግባርም እናሳየዋለን፡፡ ዩኤስኤአይዲ እያደረገ ያለው መንግሥት፤ በእርሻ ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ ነው እንጂ ይህ የግብርና ንግድ አገልግሎት ፕሮግራም ራሱን ችሎ ብቻውን የሚንቀሳቀስ አይደለም ያሉት ዶ/ር ጂሬኛ፤ በፊት የእርሻ ግብአቶች በተለያዩ የግል ድርጅቶች በችርቻሮ ይቀርብ ነበር። በዚያ አሠራር፣ ግብአቱ ገበሬው እጅ እስኪገባ ድረስ ሰንሰለቱ ረዥም በመሆኑና ብዙ አቀባባይ ነጋዴዎች ስላሉ ምርቱ ገበሬው ጋ ሲደርስ ዋጋው በጣም ይወደድ ነበር፡፡ የሲ ኤፍ ኤስ ፒ ጥረት ይህን ሰንሰለት አስቀርቶ፤ ግብአቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ፀረ - ተባይ በአጠቃላይ መርዝ ነው፡፡ ገበሬው የእነዚህን ኬሚካሎች አጠቃቀምና የአያያዝ ጥንቃቄ ስለማያውቅ፣ ገዝቶ ቤቱ ከደረሰ በኋላ የተወሰነውን በእጁ በጥብጦ በለበሰው ልብስ ይረጫል፤ የተወሰነውን ቤቱ ላይ አንጠልጥሎ ያስቀምጣል፣ ዛሬ የገዛውን እያስቀመጠ ለዓመታት ይጠቀማል። ይህ ሁኔታ ያስከተለው ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ አልተጠናም፡፡

የተፈለገው ምርታማነት ግን ሲቀንስ እንጂ ሲጨምር አይታይም፡፡ ገበሬው በብዙ ቦታ ፀረ ተባይ መያዣዎችን ውሃ ይጠጣበታል፡፡ ዘይት ይገዛበታል፣ ለተለያየ አገልግሎት ይጠቀምበታል፡፡ የጥንቃቄ አያያዝና አጠቃቀሙን አያውቅበትም፡፡ ይህ ፕሮግራም መደረግ ያለበትን አጠቃቀም አያያዝና አወጋገድ ያስተምራል፤ ያሰለጥናል፡፡ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ፀረ - ተባይ ኬሚካሎች፣ በተለያዩ ምድቦች በመክፈል “እነዚህን ገበሬው በቀላሉ ሊጠቀም ይችላል፣ እነዚህን ደግሞ መከላከያ ሳያደርግ ገበሬው እንዳይጠቀም፣ መጠቀም ካለበት ደግሞ ራሱንና አካባቢውን ከጉዳት ለመጠበቅ ቅድመ ዝግጅት ያድርግ፡፡ ያ ካልሆነ በጣም መርዛማ የሆነ ፀረ - ተባይ፣ ገበሬ እጅ እንዳይገባ ሙከራ እያደረግን ነው። ለሙከራ በመረጥናቸው ማዕከላት ለምሳሌ በዶዶላ አካባቢ፣ ማንበብና መረዳት የሚችሉ ሰዎችን መርጠን፣ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ እነዚህ ሰዎች መርዛማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ፣ በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ፀረ - ተባይ እና ፀረ - አረም ኬሚካሎችን እነሱ ብቻ ለገበሬው እንዲረጩ፣ ከረጩም በኋላ መያዣዎቹን ወደ ማዕከሉ መልሰው እንዲያቃጥሉ ማዕከሉ ያስተምራል፣ ያሰለጥናል፡፡ በዶዶላ ማዕከል የሚመረቱ ምርጥ ዘሮችን ወደ አምቦ፣ ከዚያ ደግሞ ወደዚህ እንዲለዋወጡ እናደርጋለን፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርታቸውን የሚሸጡት ማዕከላት፣ በውጭ አገራት በውድ ዋጋ የሚሸጡትን ኬሚካሎች መግዛት አይችሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ማዕከላት ተደራጅተውና የራሳቸው ኮኦፕሬቲቭ ፈጥረው የግል አትራፊ ድርጅቶች ሳይገቡበት ፀረ - ተባይ፣ ፀረ - አረም ኬሚካል፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከውጭ ማስመጣት ሲችሉ ዋጋው ይቀንሳል፡፡

ማዕከላቱን ከከፈትን በኋላ በቀጣይ ራሳቸው አስመጪ እንዲሆኑ እየጣርን ነው፤ የግብርና ንግድ አገልግሎት ፕሮግራምም ለዚህ በጀት የመደበ ስለሆነ እንሠራበታለን በማለት ዶ/ር ጂሬኛ ግንደባ፤ ስለ ግብርና ምርት ግብአት አቅርቦት ዓላማና አሠራር አስረድተዋል፡፡ የዶዶላው የግብርና ምርት ግብአት አቅርቦት ማዕከል ሲመረቅ፣ የዩኤስኤአይዲ ተወካይ አቶ ፋሲካ ጅፋር፤ አርሶ አደሮች ምርት የሚያሳድጉባቸው እንደምርጥ ዘር ማዳበሪያ፣ የፀረ ተባይ መከላከያ፣ የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት፣ የዘመናዊ መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ያለመሟላት በግብርናው ዘርፍ ላይ ተጽእኖ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በሙከራ ላይ ያሉት የግብአት አቅርቦት ማዕከላት በሙሉ አቅማቸው መሥራት ሲጀምሩ ከፍተኛ ጥራትና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የምርት ግብአቶች እንደሚያቀረቡ፣ ስልጠናና ሙያዊ ምክር በመስጠትና የገበያ ትስስር በመፍጠር 30ሺ ያህል አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። ይህ የሙከራ ፕሮጀክት ውጤታማ ከሆነ፣ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል፡፡

Read 2373 times