Monday, 03 February 2014 12:36

“ሎሚ” መጽሔት በአክሱም ዩኒቨርስቲ ተከሰሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“አክሱም ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኘው የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ፎቶ እርሣቸውን አይመስልም” የሚል ዘገባ ለህትመት በማብቃቱ ዩኒቨርስቲው ክስ የመሰረተበት ሎሚ መፅሔት ዋና አዘጋጅ ሰናይ አባተ፣ ረቡዕ ዕለት ማዕከላዊ ቀርቦ ቃሉን ከሰጠ በኋላ በ5ሺ ብር ዋስ መለቀቁን የመፅሄቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ዳንኤል ድርሻ ገለፀ፡፡ ባለፈው ህዳር ወር በመፅሄቱ ላይ የወጣው ፅሁፍ ከአንባቢ የተላከ እንደነበር ያስታወሰው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ ከፎቶው ጋር የተላከው ፅሁፍ፤ “የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶ ቢኖርም ፎቶው ግን እርሳቸውን አይመስልም” የሚል እንደነበር ተናግሯል፡፡ አስተያየቱ የመጣው ከአክሱም አካባቢ እንደሆነና መጽሔቱም የሰዎችን ሃሳብ በማስተናገድ የሚያምን በመሆኑ፣ ፎቶውን ከእነ ፅሁፉ ማስተናገዱን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡

መጽሔቱ ከወጣ በኋላ የአክሱም ዩኒቨርስቲ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ቢኒያም ዳኘው ለመፅሔቱ ዝግጅት ክፍል ደውሎ፤ “እንዲህ ዓይነት ፎቶም ሆነ ሐውልት በዩኒቨርስቲያችን ውስጥ የለም፤ ስህተት ነው” በማለት ማስተባበያ እንዲያወጣ መጠየቁንም ጠቁሟል፡፡ ዩኒቨርስቲው የላከው ማስተባበያ ውስጥ “የክቡር አቶ መለስ ዜናዊም ሆነ የሌሎች ለአገሪቱ ታላላቅ ውለታ የዋሉ ሰማዕታት ሐውልት የለም” የሚል ሃሳብ የሰፈረ ሲሆን፤ ከዚህ ማስተባበያ ውስጥ “ሐውልት” የምትለው ቃል በስህተት ብትዘለልም በሩብ ገፅ አስተናግደነዋል፤ ሆኖም ዩኒቨርስቲው አንዲት ቃል ስለተዘለለች ብቻ ክስ መስርቶብናል ብሏል - ጋዜጠኛ ዳንኤል፡፡

በአሁኑ ወቅት በየአጋጣሚው ፕሬሱን ለማዳከም እየተሰራ መሆኑን የሚያሳየው፣ ሩብ ገጽ ማስተባበያ ወጥቶ በአንዲት ቃል ክስ መመስረቱ ነው” ብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ልጆቻቸው በመቀሌ ማረሚያ ቤት የታሰሩባቸው አቶ አስገደ ገ/ስላሴ የልጆቻቸውን መታሰርና የእስር ቤቱን አያያዝ ጉዳይ በተመለከተ ኩባ ውስጥ ከሚገኘው “ጓንታናሞ” የተባለ የአሜሪካ እስር ቤት ጋር እያመሳሰሉ የፃፉትን ጽሑፍ በማስተናገዱ የትግራይ ፖሊስ በመጽሔቱ ላይ ክስ መመስረቱን ያስታወሰው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ ይህን መሰል ክሶች የሰዎችን የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ህገ-መንግስታዊ መብት የሚፃረር በመሆኑ እንደሚቃወመው ተናግሯል፡፡

Read 2950 times