Monday, 03 February 2014 12:38

ጤፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት እያገኘ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ ኪሎ ጤፍ በአውሮፓ ከ200 ብር በላይ ይቸበቸባል
የአሜሪካ አውሮፓና፣ እስራኤል ገበሬዎች ጤፍ እያመረቱ ነው
ከጤፍ ተፈላጊነት የኢትዮጵያ ገበሬዎች መጠቀም አለባቸው ተባለ “ጤፍ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሱስ ነው” ትላለች - የ”ዘ ጋርዲያን” ዘጋቢዋ ኤሊሳ ጆብሰን፤ ባለፈው ሳምንት ለንባብ ባበቃችው ዘገባ ላይ፡፡ በአገሪቱ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ጤፍ እንደሚያመርቱና ከአገሪቱ የእርሻ መሬት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነውም በጤፍ እንደሚሸፈን ትገልጻለች፡፡ በአገሪቱ ለምግብነት ከሚውሉ የሰብል አይነቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝና እንጀራም ብሄራዊ ምግብ እስከመሆን መድረሱን በዘገባዋ ጠቁማለች፡፡ ጤፍ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋል አልፎ በእንጀራ መልክ ባህር ተሻግሮ በተለይ በምዕራባውያን አገራት በሚገኙ ዲያስፖራዎች መበላት ከጀመረ አስርት አመታት እንዳለፈው የምታስታውሰው ዘጋቢዋ፤ አሁን አሁን ደግሞ የጤፍ ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ትናገራለች፡፡

የኢትዮጵያ ጤፍ በአለም ገበያ ቀጣዩ ተፈላጊ ሰብል ለመሆን እንደሚችል በመግለጽ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ለአለም የምታበረክተው ሁለተኛው ስጦታ ጤፍ መሆኑ እንደማይቀር ትናገራለች፡፡ በውስጡ ካልሺየም፣ አይረን፣ ፕሮቲንና ሌሎች ንጥረነገሮችን የያዘውና ለጤና ተስማሚ የሆነው ጤፍ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ነው ዘ ጋርዲያን ከሰሞኑ ያስነበበው ዘገባ የሚያስረዳው፡፡ “ጤፍ በውስጡ የያዘውን ንጥረ ነገር ባወቅሁ ጊዜ እጅግ ነበር የተገረምኩት፡፡ በህይወት ዘመኔ ሁሉ ስመገበው የኖርኩት ጤፍ፤ እንዲህ ያለ ጠቃሚ ነገር መሆኑን አላውቅም ነበር፤ የሚገርም ነገር ነው!” ያለችው ነዋሪነቷ በለንደን የሆነው ኢትዮጵዊቷ ሶፊ ከበደ ናት፡፡ ሶፊ በጤፍ ተገርማ አላበቃችም፡፡

የግርምት ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጭም መሆን እንደሚችል ገብቷታል፡፡ ለዚህ ነው ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ ለንደን የሆነ ‘ጦቢያ ጤፍ’ የተሰኘ የንግድ ኩባንያ ከባለቤቷ ጋር በማቋቋም፣ ጤፍን ከአምራች አገሮች እየገዛች ወደእንግሊዝ በማስመጣት መሸጥ የጀመረችው፡፡ የዘጋርዲያን ዘገባው እንደሚለው፣ ዛሬ “ፕላኔት ኦርጋኒክን” የመሳሰሉ የለንደን ታላላቅ መደብሮች ጤፍ አሽገው በመቸብቸብ ላይ ናቸው፡፡ በእነዚህ መደብሮች አንድ ኪሎ የጦቢያ ጤፍ ዱቄት 7 ፓውንድ (ከ200 ብር በላይ) ይሸጣል፡፡ በመደብሮቹ በጤፍ ዱቄት የተሰራና የተለያዩ ማጣፈጫዎች የታከሉበት ዳቦም ለገበያ ይቀርባል፡፡ ጤፍ አሁን የአገር ቤትና የአገር ልጅ ምግብ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ምዕራባውያን አገራት ዜጎችም በጤፍ አምሮት መለከፍ ይዘዋል፡፡ ፍላጎቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ “ማማ ፍሬሽ” የተባለው የንግድ ኩባንያ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ለአመታት እንጀራ ሲያቀርብ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅትም ወደ ፊLላንድ፣ ጀርመን፣ ስዊድንና አሜሪካ እየላከ እንደሚገኝ ዘገባው ያሳያል፡፡ ወደ አሜሪካ የሚልከውን ምርት በ2014 በእጥፍ የማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ ያለው ኩባንያው፤ በቅርቡም የጤፍ ፒዛ፣ ዳቦና ብስኩት እያመረተ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር ዘገባው ያስረዳል፡፡

ዘጋቢዋ እንደምትለው፤ “ጥያቄው ኢትዮጵያ እና አርሶ አደሮቿ ከዚህ አለማቀፍ ገበያ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለው ነው፡፡ ለመሰል የተወሰኑ አገራት ምርት ብቻ የሆኑ በንጥረነገር ለበለጸጉ የምግብ እህል ሰብሎች እያደገ የመጣው አለማቀፍ ፍላጎት፣ በድህነት የሚማቅቁ የአምራች አገራትን ማህበረሰቦች ጎጂ ሲሆኑ ይታያሉ ትላለች ዘጋቢዋ፡፡ ይህን እውነታ ለማስረዳት የቦሊቪያና የፔሩን ተሞክሮ በአብነት የምትጠቅሰው ዘጋቢዋ፣ በእነዚህ አገራት የሚመረተው “ኪየኑአ” የተሰኘ የሰብል አይነት በብዛት ወደ ውጭ አገራት መላኩ፣ በአገሪቱ የምግብ እጥረት ማስከተሉን እንዲሁም ሰብሉን አምርቶ በብዛት በመሸጥ የምዕራባውያኑን ፍላጎት ለማሟላት በሚል በአርሶአደሮች ዘንድ የመሬት ሽሚያና ግጭት መፈጠሩን ትገልጻለች፡፡ “በኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ለጤፍ ያላቸው ፍላጎት እያደገ ነው፡፡ በአገሪቱ የጤፍ ዋጋ ባለፉት አስርት አመታት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም ድሃ ዜጎች ጤፍ መግዛት የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ አምራቾችም ምርታቸውን ወደ ከተማ እያወጡ በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡” ያለችው ዘጋቢዋ፤ የመንግስትን መረጃ ጠቅሳ እንደጻፈችው፣ በከተማ የሚኖሩ ዜጎች በአመት በአማካይ 61 ኪሎግራም ጤፍ እንደሚመገቡ ይገመታል፡፡

በገጠር የሚኖሩት ደግሞ 20 ኪሎግራም፡፡ የአገሪቱ መንግስት አመታዊ የጤፍ ምርቱን በ2015 በእጥፍ የማሳደግ እቅድ አለው፡፡ ይህም የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ አቅርቦቱን ለማሳደግ ያስችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት፣ የንግድና ገበያ ዳይሬክተር ዴቪድ ሃላም እንደሚሉት፣ አገር በቀል የሰብል ምርቶችን ለአዳዲስ አለማቀፍ ገበያዎች በማቅረብ ጥሩ ገቢ ማግኘት መቻሉ እንዳለ ሆኖ፣ መንግስታት አነስተኛ ሰብል አምራቾች ከእነዚህ ገበያዎች የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባዮ ዳይቨርሲቲ ተቋም የቀድሞ ሃላፊ የነበሩት የግብርና ተመራማሪው አቶ ረጋሳ ፈይሳ በበኩላቸው፣ ጤፍን በከፍተኛ መጠን እያመረቱ ለውጭ ገበያ የማቅረቡ አካሄድ በአግባቡ ካልታቀደና ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደጋ አለው ማለታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ አካሄድ፣ አርሶ አደሮች ለሌሎች ምርቶች ትኩረት እንዳይሰጡ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በብዛት አምርቶ ለገበያ የማቅረቡ አካሄድ አነስተኛ ገበሬዎችን ተጠቃሚ በማያደርግ መልኩ ለጥቂት አትራፊዎች ሲሳይ ሊሆን ይችላል፡፡ በአለማቀፍ ገበያ ላይ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ጤፍ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ የአሜሪካ ገበሬዎች ጤፍ ማምረት መጀመራቸውን የገለጸው ዘገባው፤ የአውሮፓ፣ የእስራኤልና የአውስትራሊያ ገበሬዎችም በሙከራ ደረጃ ጤፍ ወደማምረት መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡

የ “ጦቢያ ጤፍ” ኩባንያ ባለቤት የሆነችው ሶፊ ከበደ፤ በለንደን ለገበያ የምታቀርበውን ጤፍ፣ ከአገር ቤት ሳይሆን ከደቡባዊ አውሮፓ አገራት ገበሬዎች እንደምትገዛ ገልጻለች፡፡ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች የሚያመርቱትን ማኛ ጤፍ ለእንግሊዝ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላትና የአገሯ ገበሬዎች ምርታቸውን ለአለማቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን የማይችሉበት መንገድ እንደሌለም ለ “ዘጋርዲያን” ተናግራለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 የኢትዮጵያ መንግስት ጤፍን በእንጀራ መልኩ ካልሆነ በቀር በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚከለክል ህግ ማውጣቱን የወሳው ዘገባው፤ ይሄም ሆኖ ግን እገዳው ዘላቂ እንደማይሆን ገልጿል፡፡ ምክንያቱም የመንግስት ስትራቴጂ ያስቀመጠው ግብ ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ የሚውል በቂ የጤፍ ምርት ማምረት ነውና፡፡

Read 4818 times