Monday, 03 February 2014 12:39

አፍሪካውያንን ከድህነት ለማውጣት ያለመ ዘመቻ ተጀመረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የአፍሪካ መንግስታት 10 በመቶ ያህል በጀታቸውን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው የበጀት አጠቃቀም በውጤታማ ግብርና ላይ እንዲያውሉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ከ85 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንን ከድህነት ለማውጣት ያለመ ዘመቻ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ተጀምሯል። “ዋን” የተሰኘው አህጉር በቀል ተቋም ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገው ማሣሠቢያ አዘል ሪፖርት፤ ከ400 ሚሊየን በላይ ከሚሆኑት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚዳክሩ አፍሪካውያን መካከል 70 በመቶ ያህሉ ኑሮአቸውን የመሰረቱት ውጤታማ ባልሆነ ግብርና ላይ እንደሆነ ጠቁሞ የእነዚህን ዜጐች ኑሮ ለማሻሻል ከተፈለገ ለግብርና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል፡፡ የአፍሪካ ገበሬዎች ህይወት እንዲሻሻል መንግስታት ሊተገብሩት ይገባል ብሎ ተቋሙ ከጠቆማቸው የመፍትሄ ሃሣቦች መካከልም በግብርና ላይ ያለውን ጾታዊ አድልኦ ማስወገድ፣ የመሬት አስተዳደርና የመሬት ኪራይ መብት ዋስትናን ማጠናከር እንዲሁም ለዘርፉ ጠንካራ በጀት መመደብ ይገኙበታል፡፡

ተቋሙ በሪፖርቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ከበጀታቸው 10 በመቶውን ለግብርና በማዋላቸው ውጤታማ እየሆኑ ነው ብሏል። በግብርና ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን የሚያካሂደው “ዋን”፤ ከቤኒኑ ኘሬዚዳንት ያዬ ቦኒ፣ ከናይጄሪያዊው ዘፋኝ ጂባንጂ እንዲሁም ከኮትዲቫራዊው እግር ኳስ ተጫዋች ያያ ቶሬ ጋር በመሆን በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ “ዲ አፍሪክ” የተሰኘ አዲስ ዘመቻ በይፋ ያስጀመረ ሲሆን ዘመቻው በግብርና ላይ በቀጥታ ያተኮረ የኢንቨስትመንት ፈሰስ በማድረግና በተሻሻለው ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ የግብርና ልማት ኘሮግራም ፖሊሲዎች አማካኝነት ከ85 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንን ከድህነት ለማውጣት ያለመ እንቅስቃሴ ነው ተብሏል፡፡

Read 1411 times