Monday, 03 February 2014 12:46

ጥንታዊው የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም ተፈታ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

         ገዳሙ ጨርሶ ሳይጠፋ ጉዳያቸው በሲኖዶሱ እንዲታይ መናንያኑ ጠይቀዋል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ አንድነት ገዳም ተፈትቶ፣ መናንያኑና መነኰሳቱ መበተናቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡ ጥንታዊውን ገዳም ለመፈታት፣ ማኅበረ መነኰሳቱንም ለመበተን ያበቃቸው በአካባቢ ተወላጅነት የገዳሙን መሬት በተለያዩ ጊዜያት ተቆጣጥረው ለግላቸው ይጠቀሙ ከነበሩ ግለሰቦች ጋር ተፈጥሮ የቆየውና በተለያዩ ምክንያቶች እየተካረረ የመጣው አለመግባባት መኾኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ በኅዳር ወር 2006 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ገዳሙን ለቀው የወጡት በቁጥር ከ50 - 80 የሚገመቱ መነኰሳት፣ መነኰሳዪያትና መናንያን ከተለያዩ አህጉረ ስብከትና ክልሎች የተሰባሰቡ ሲኾኑ በሀገረ ስብከቱ ውሳኔ ከአስተዳዳሪነት የተነሡትን አበምኔቱን መ/ር አባ ተክለ ብርሃን ሰሎሞንን ጨምሮ ከፊሎቹ በአሁኑ ወቅት በደነባ በኣታ ለማርያም ገዳም ተጠልለው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የወረዳው መንግሥታዊ አስተዳደር፣ ከእነዋሪና ደነባ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ገዳማውያኑንና ግለሰቦቹን በተለያየ ጊዜ በማገናኘት ለአለመግባባቱ የመፍትሔ ሐሳብ ሲሰጡና ውሳኔ ሲያሳልፉ እንደቆዩ ያስታወሱት መነኰሳቱ፤ ‹‹ተሰዳጅና መጤ›› ከሚል በቀር ግለሰቦቹ የሚያቀርቡባቸው ክሦች መሠረተ ቢስ እንደኾኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ የገዳሙን ሥርዐተ ማኅበር በመጣስ የመሬት ይዞታውን፣ ቅርሱንና የልማት ቦታውን ለመከፋፈል የሚሹ ግለሰቦች በሥነ ምግባር ጉድለት ርምጃ ከተወሰደባቸው የስም መናንያን ጋራ በማበር ያቀረቡትን አቤቱታ ብቻ በመቀበል በፓትርያርክ የሚሾሙት አበምኔት በሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ከሓላፊነት መነሣታቸውን ያስረዱት ማኅበረ መነኰሳቱ፣ አንዳንድ የሀ/ስብከቱን ሓላፊዎች በስም በመጥቀስ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የገዳሙን መሬት ይዘው ከገዳማውያኑ ጋራ ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩትን የአካባቢውን አርሶ አደሮች ትክ መሬት እንዲያገኙና ለንብረታቸውም ካሳ እንዲሰጣቸው በማድረግና ጣልቃ ገብነትን በመከላከል የገዳሙን ይዞታና ሥርዐተ ማኅበሩን ያስከበሩትን፤ በግብርናና በሽመና ሥራዎች፣ በሙዓለ ሕፃናት፣ በኪራይ ቤቶች ግንባታ የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት ልመናን ያስቀሩትን አበምኔት አላግባብ ከሓላፊነት ማንሣት÷ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ኤፍሬም ስለ አበምኔቱ የአስተዳደርና ትምህርት ብቃት እንዲሁም ልማታዊነት ሲሰጡ የቆዩትን ምስክርነት የሚያስተባብልና የገዳሙን መተዳደርያ ደንብ የሚጥስ ከመኾኑም በላይ በሀ/ስብከቱ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር አስከፊ መገለጫ ነው ብለዋል ማኅበረ መነኰሳቱ፡፡

ከገዳማቸው የተፈናቀሉት ማኅበረ መነኰሳቱ ሥርዐተ ማኅበራቸውን ጠብቀው በገዳሙ የጀመሩትን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎት ለመቀጠል እንዲችሉ፤ የገዳሙ ቅርሶች፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲጠበቁ፣ በገዳሙ ያለጧሪ የቀሩት ድኩማን አረጋውያን ደኅንነትም እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የደብረ ብሥራት ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር በኾኑት አቡነ ዜና ማርቆስ የተመሠረተ የዐሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገዳም መኾኑን የገዳሙ ታሪክ ይገልጻል። ገዳምነቱን ሳይለቅ እስከ 8000 መናንያንን እያስተዳደረ በሥርዐተ ማኅበር በቆየው ገዳም፣ ሰበካ ጉባኤ በማቋቋም ወደ ደብርነት እንዲቀየርና በቃለ ዐዋዲ እንዲመራ ለማድረግ ተሞክሮ እንደነበር የገለጹት የዜናው ምንጮች÷ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገዳማት አስተዳደር መምሪያና የቅርስ ጥበቃ የሚመለከታቸው አካላት ኹሉ ከጻድቁ የእጅና የመጾር መስቀሎች ጀምሮ በርካታ ቅርሶች የሚገኙበትን የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሥርዐተ ምንኵስናና የትምህርት ማዕከል ጨርሶ ሳይጠፋ መታደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

Read 4206 times